Connect with us

ወረኢሉ ባለህ እኩል የምትበላባት ከተማ፡፡

ወረኢሉ ባለህ እኩል የምትበላባት ከተማ፡፡
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ወረኢሉ ባለህ እኩል የምትበላባት ከተማ፡፡

ወረኢሉ ባለህ እኩል የምትበላባት ከተማ፡፡

ሚዛን ጠል ቸር ሉካንዳዎች

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ወረኢሉ ተጉዞ ከአድዋ ድል ታሪክ ጋር ትልቅ ቁርኝት ያላትን ስፍራ እያስተዋወቀን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ በጥንታዊቷ ከተማ የቀደመ አሻራዎችና ያለ ሚዛን ስጋ በሚሸጡ ልካንዳዎቿ የታዘበውን ያጋራናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ አልቀረንም፤ የአድዋን አሻራዎች ፍለጋ እንሄዳለን፡፡ ግን ባዶ ሆዳችሁን አልወስዳችሁም፡፡ እንዴት ተደርጎ? ወረአሉማ ደረሰ ይሄን ማየት አለበት፡፡ የት መሰላችሁ ያለሁት፣ ደቡብ ወሎ፤ ወረኢሉ፡፡ 

አሮጌው የከተማዋ ጎዳና ሰው ይተራመስበታል፡፡ በየደጃፉ ላይ ቆዳ ወድቋል፡፡ ያ ትናንት የቆመው በሬ ዛሬ ልብሱ ሜዳ ተዘርግቶ ሰው ይራመድበታል፡፡ ወረኢሉ ነገ ይሄንን አርዳለሁ ይላል፡፡ ማታ ያዩትን በሬ ጠዋት አይረሱትም እዚያው ስጋ ቤቱ ደጃፍ ቆዳው ተንጥፎ እንደ ሬድ ካርፔት እንግዳ ይቀበላል፡፡

ስጋ ቤቶቿ ቸር ናቸው፡፡ ውዬ ሳድር ወረኢሉ ምን ፍለጋ የክተት አዋጁ መነሻ እንደሆነች እየገባኝ ነው፡፡ ጓዳዋ አይነጥፍም፤ ሌማቷ አይራቆትም፡፡ በረቷ ወና አይሆንም፡፡ አቤት የስጋ ቤቱ ብዛት፤ ደግሞ የስጋው ውበት፡፡

የወረኡሉ ሉካንዳ መቶ-መቶ ሻማ አምፖል እያንቦገቦገ ስጋውን አያስለቅሰውም፤ ጮማው እንዲሁ በጨለማ ያበራል፡፡ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እዚህ ትናንት ተወልዶ ዛሬ ሰጋ የሆነ ከብት የለም፡፡ ተፈጥሮ በሰራችው ወደ ተሰራ ሰንጋ ጣዕም ገባሁ፡፡

ሚዛን ብሎ ነገር የለም፡፡ ሚዛን ልክ የመሆን ብቻ ሳይሆን የስስትም ምክንያት እንደሆነ አየሁ፡፡ ሚዛን ምን ሊያድርግ፡፡ ይገመታል፤ ይመዘናል፡፡ እዚህ ሰው ባለው ስጋ ይበላል፡፡ ሁሉም ስጋ ቤት ለሁሉም ሰው እንዲሆን የተከፈተ ነው፡፡ የእከሌ በሬ ጥሩ ነው ብሎ በበሬ ስም የሰው ስጋ የማይበላባት መዲና ወረኢሉ፡፡

ያለህን ይዘህ ስጋ የምትበላባት ከተማ ሲል መታሰቢያ ያወድሳታል፡፡ መታሰቢያ አሮጌዋን የቀድሞ ከተማ መንደሮች እያስጎበኘን ነው፡፡ የታሪክ መምህሩም አብሮ አለ፡፡ ታሪካዊቷ ከተማ ታድሜያለሁ፡፡ 

ስጋን መመዘን ቀድሞውኑ ስስት ነው፡፡ እዚህ ሰው እንጂ ስጋ ብርቅ አይደለም፡፡ ቅመሰው የሚባለው ሌላው ቦታ ግማሽ ኪሎ ተብሎ ሚዛን የሚተፋው ነው፡፡ ስጋው ልዩ ጣዕም አለው፡፡ ሰላሳ ብር ስጋ ሲያበላ ያየሁ ምስክር ነኝ፡፡ አንድ ቀን ወረኢሉ እንደ ሀገሯ ከተሞች አብዳ ይሄንን ጠባይዋን ብትቀይር እወቅሳታለሁ፡፡ የደግነቷንና የደሃ አቀፍነቷን ልክ አይቻለሁና፡፡

ተጋበዝሁ፡፡ አሁን ደግሞ መንፈሴን ልሞላ ነው፡፡ ጉዞ ወደ ደብረ ሰላም ወረኢሉ ጊዮርጊስ፤

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top