Connect with us

ወረኢሉ፤ የድሉ መነሻ፡፡

ወረኢሉ፤ የድሉ መነሻ፡፡
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

ወረኢሉ፤ የድሉ መነሻ፡፡

ወረኢሉ፤ የድሉ መነሻ፡፡

ተፈጥሮ! ቅርስ! ታሪክ – የኢትዮጵያዊነት ሞገሷ፡፡

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ደቡብ ወሎ ተጉዟል፡፡ ወረኢሉ የድሉ መነሻ ሲል እስከ ጥቅምት እኩሌታ ሀገር የተቀጣጠረባትን የአድዋ ድል ቀዳሚ ምዕራፍ ከታሪክ አሻራዎቿ ጋር እየፈተሸ ቆይታውን እንዲህ ያካፍለናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ወረ ኢሉ ነኝ፡፡ እንኳን መጣሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ነው የመጣሁት፡፡ በጥቅምት እኩሌታ ሀገር መጥቶ ዓለም ወደ አገነነው ድል መነሻ፡፡ ከምኑ ልጀምርላችሁ፡፡ ከሚናገረው ተፈጥሮ፣ ከወል ግዙፍ ሞገስ፣ ከሰኞ ገበያ ስስት፣ ከከሬ ማርያም ቸርነት፤ እኮ ከምኑ?

ቅርብ ሆና ለሀገር ወደ ራቀች የሀገር መልክ መጥቻለሁ፡፡ ደሴ ስትደርሱ 92 ኪሎ ሜትር ተጉዛችሁ ያለሁበት ትቆማላችሁ፡፡ የመርሐቤቴን ውብ ተፈጥሮ እያየ በመራኛ ለሚዘልቅ ደግሞ ከአዲስ አበባ መጓዝ የሚጠበቅበት 300 ያልሞላ ኪሎ ሜትር ነው፡፡

የልብነ ድንግል ማተም፣ የዑላማዎቹ በረከት፣ የገላውዴዎስ እልፍኝ፤ የምኒልክ ስስቱ፣ እኮ እንዴት ትገለጻለች? የዐፄ ናኦድ ምኞት፣ የንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ የእትብት መቀበሪያ፣ የታላቋ ወይዘሮ የባፈና ቀዬ፣ የናአኩቶ ለአብ የጽድቅ ስራ እኮ እንዴት?

እዚህ ነኛ፤ አድዋን ፍለጋ መጣሁ፡፡ የድሉን መነሻ ለማሰስ፣ የተደበቀችዋን ግዙፍ ስፍራ ለመፈለግ፤ አልጠፋችም፡፡ ሲደርሱ ከነክብሯ አለች፡፡ ሲመጡ የምትቀበል ደግ፣ በስሜን ደሴ ዙሪያን ያጠረች፣ ደቡቧን ከጃማ የምትጋራ፣ ምስራቋ ሸዋን ከአልብኮ ያጋመደ፣ ምዕራቧ ከለጋቦ ለጋሂዳ የተዘረጋ፤ ትልቋ ወረኢሉ፤

የተቀበለኝ የጥንቷ መንደር ነው፡፡ ቤቶቿ እድሜያቸውን ይናገራሉ፡፡ ሠፈሩ ደርባባ ነው፡፡ ፒያሳዋ ሞቅ ይላል፡፡ ነገ ማልጄ ተነስቼ ጊዮርጊስን እጎበኛለሁ፡፡ ደብረ ሰላምን፡፡ የሰላሟ ስፍራ ሰላማዊ እንቅልፍ አድራለሁ፡፡

አድዋ ያለ ወራኢሉ ምንድን ናት? ድሉ እዚህ ተበሰረ፡፡ የጦርነቱ ድልስ ቀድውኑ በስንቁ ብዛት፣ በሸኚው ስስት፣ በትጥቁ ዝግጅት ይወሰን የለ፡፡

ምን ፍለጋ ጥቅምት እኩሌታ እዚህ እንደተመጣ ስመጣ ያለው መንገድ ነግሮኛል፡፡ ወረኢሉ አምራች ናት፡፡ ለሺህ አመት የተፈተነው መሬት ዛሬም ይመረትበታል፡፡ እዚህም እዚያም ክምር አያለሁ፡፡ ምርቱን የሚወቃውን “ምርት ያውርድ” እያልኩኝ ለምድሩ የወረደውን ጸጋ እመለከታለሁ፡፡

ገና እንሄዳለን፡፡ ይንጋ ብቻ፡፡ ደብረ ሰላም ጊዮርጊስ የአድዋውን ዘማች እናየዋለን፡፡ እንደ ጋርዱላ ጊዮርጊስ፣ እንደ አራዳ ጊዮርጊስ ምኒልክ እንደ አባቶቹ አበራ ጊዮርጊስን ይዘው ድል እንዳደረጉት በሰማይ ያሰለፈውን ፈረሰኛ ደጃፍ እንረግጣለን፡፡

ሄኖክ ማስረሻ አንተ እዚህ ለመድረሴ ምክንያት ነህ፡፡ መታሰቢያ ደምሴ አንተ ባትኖር ኖር የሚጎድልብኝን የማውቀው እኔ ነኝ፡፡ የባህል ቱሪዝሞቹ ሄኖክስና መሐመድ፣ የከሬ ሞላ ብቻ ምስጋናዬ ወደር የለውም፡፡ ሲነጋ ወደዚያ ተአምረኛ የወራኢሉ ስጋ ቤቶች አብረን እንሄዳለን፡፡

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top