Connect with us

ኢዜማ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ችግርን የሚመጥን ትኩረት በመንግስት አልተሰጠውም አለ

#የኢዜማ_መግለጫ
ኢዜማ

ዜና

ኢዜማ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ችግርን የሚመጥን ትኩረት በመንግስት አልተሰጠውም አለ

ኢዜማ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ችግርን የሚመጥን ትኩረት በመንግስት አልተሰጠውም አለ

~ በምርጫ፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወጣው መግለጫ እነሆ

ኢዜማ እንደሀገር ያለንበት ሁኔታ እና መጪው ሀገራዊ ምርጫ የሁሉንም ባለድርሻ አካለት በኃላፊነት መንቀሳቀስ እና ሀገራችንን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ የምንቀይርበት ሊሆን ይገባል ብሎ ያምናል። በዚህ መግለጫ ምርጫ 2013 ያለው ፋይዳ፣ የሀገራችንን የፀጥታ ሁኔታ እና ሀገራዊ ምርጫው ላይ የሚኖረው ተፅእኖ፣ አመራሮቻቸው በእስር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንቅስቃሴ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያለው ተፅዕኖ እና በኢዜማ የምርጫ ዝግጅት ላይ ማብራሪያ እናቀርባለን።

ምርጫ 2013

የ2013 ሀገራዊ ምርጫ አሁን ሀገራችን ያለችበትን አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታ ወደ የተሻለ የተረጋጋ ሀገራዊ ሁኔታ የመቀየርና በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሞከረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በጠንካራ መሰረት ላይ ቆሞ እንዲቀጥል ማድረግ የሚቻልበትን መልካም አጋጣሚ ከመፍጠር አንጻር፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊና ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው እናምናለን።

ምርጫው የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ ከሚከተሉት ምክንያቶች የመነጨ ነው፤

  • የ2013 ምርጫ ተቀባይነት ባለው ሂደትና ውጤት ሊጠናቀቅ የሚችልበት እድል መኖሩ፣
  • በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ የምርጫ ፍላጎት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት እድል መኖሩ፣
  • በሀገራችን የሚገኙ ሀገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች፣ ከሕዝብ ሊኖራቸው የሚችለውን ድጋፍ በሠለጠነ የምርጫ ሂደት ውጤት ማወቅ የሚችሉበት ጥሩ ታሪካዊ አጋጣሚ ሊሆን ስለሚችል፣ 
  • ለወደፊት ለሚደረጉ ምርጫዎች ተጨባጭ ልምዶች ማግኘትና ልምዶቹን በመጠቀም የተሻለ ምርጫ ማድረግ የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ መሆኑ፣
  • በምርጫ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ድርጅት ከዚህ በፊት በታሪካችን ከነበሩት መንግሥታት በሙሉ ሕጋዊ ቅቡልነት ያለው አካል ሊሆን የሚችልበትም አጋጣሚ መፍጠሩ፣ 
  • ተቀባይነት ያለው የምርጫ ሂደትና ውጤት መሰረት አደርጎ የሚቋቋመው መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ጥቅምና ደህንነትን በሚመለከት ከማናቸውም ሦስተኛ አካል ጋር የሚያደርገውን ስምምነትም ሆነ ውል፣ ከሕጋዊ ቅቡልነት የሚመነጭ፣ ጠንካራ አቅም ሊያገኝ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር መቻሉ ናቸው።

ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ ኢዜማ ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለን እናምናለን።

የኢዜማ የምርጫ ዝግጅት

ኢዜማ ካስቀመጣቸው አራት ስትራቴጂያዊ ግቦች አንዱ በምርጫ አሸንፎ መንግሥት መሆን የሚል ነው። ይሄንን ስትራቴጂያዊ ግብ እና የፓርቲ ውስጠ ዴሞክራሲን ያሳካል ብለን ያመንበትን አደረጃጀት ስንዘረጋ መቆየታችን ይታወቃል። የኢዜማ የምርጫ ዘመቻ በብሔራዊ፣ በክልል እና በወረዳ ደረጃ በሶስት ክፍል የተከፈለ ሲሆን በብሔራዊ ደረጃ ለምርጫ ዘመቻ የሚረዳ የምርጫ ስትራቴጂ ማኔጅመንት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ ኮሚቴ በዕጩ ምልመላ እና ድጋፍ፣ በፖሊሲ እና ማኒፌስቶ ዝግጅት፣ በድርጅት አቅም ግንባታ እንዲሁም በሐብት አሰባሰብ ዙሪያ በስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ በክልል እና በምርጫ ወረዳ ላይ ያሉ የዘመቻ ክፍሎች በመዋቀር ላይ ይገኛሉ።

ከጥር 1 ቀን ጀምሮ የምርጫ ወረዳዎች ጉባዔ በማድረግ ቀደም ብሎ በተዘጋጀ የዕጩ መለያ መመዘኛ መሰረት ኢዜማን ወክለው በምርጫ ለመወዳደር ፍላጎት ኖሯቸው ካመለከቱ አባላት ምዘናውን በከፍተኛ ውጤት ያሟሉትን የመጨረሻ ውድድር በማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወክሏቸውን ዕጩዎች እየመረጡ ይገኛሉ። እስከ ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ሁሉም ኢዜማን የሚወክሉ ዕጩዎች በየምርጫ ወረዳው ተመርጠው ይታወቃሉ። ይህ ሂደት በፓርቲ ውስጠ ዴሞክራሲያዊ ባሕልን ለመገንባት እና የዴሞክራሲ ባሕል ልምምድ በሀገር ደረጃ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለን እናምናለን።

ከመጪው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ኢዜማ ከፍተኛ ዝግጅት ያደረገበት የፖሊሲ አማራጭ ዝግጅት ሌላኛው መስክ ነው፡፡ ፖሊሲዎቻችን የኅብረተሰቡን ቁልፍ ችግር በሚፈቱ ዘርፎች በሙያው የላቀ ብቃት እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተቀረጹ ሲሆኑ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እና በየዘርፉ ላይ ሙያተኛ የሆኑ የፓርቲው አባል ላልሆኑ ኢትዮጵያውያን ጭምር አቅርበን ያገኘነውን ግብረመልስ በመጠቀም በማዳበር ላይ እንገኛለን፡፡ እስከአሁን በ18 የፖሊሲ ሰነዶች ላይ ምክክር ያደረግን ሲሆን በቀጣይ ቀናት የቀሩትን የፖሊሲ ሰነዶች ለውይይት የምናቀርብ ይሆናል። ጎን ለጎን የምርጫ 2013 ማኒፌስቶ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በተለያየ ዘርፍ የተዘጋጁትን ፖሊሲዎች እና ተመርጠን ሥልጣን ብንይዝ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ልንተገብራቸው ቃል የምንገባውን ተግባሮች ዝርዝር የያዘ ማኒፌስቶ ከምርጫው በፊት ለሕዝብ በስፋት የምናስተዋውቅ ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢዜማ ለመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ሊሆን ከሚችሉት ሥራዎች አንዱ በቅርብ ይፋ ያደረገው የሥነ-ምግባር ደንብ ነው። ኢዜማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ቃልኪዳን ሰነድን በመፈረም እና ለአባለት በማሠልጠን ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ የ2013 ምርጫ የሥነ ምግባር መመርያን በማዘጋጀት ለአመራሩ፣ ለአባላት፣ ለእጩዎች እና ለደጋፊዎች እንዲደርስ ይፋ አድረጓል።

የምርጫ ዝግጅት በውስጠ ፓርቲ ሥርዓት ብቻ የሚገመገም ባለመሆኑ በሀገራችን የሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነት እና ብቃት ጉዳይ፣ በምርጫ ሕግጋት መከበር ዙሪያ ኢዜማ አባላቱን እያሰለጠነ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በላይ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ሰፊ የኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠበቅ በመሆኑ ሕዝቡም በነቂስ በሒደቱ ሁሉ እንዲሳተፍ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ተፎካከሪ ፓርቲዎች ምርጫ 2013

በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተለይተው ይፋ መሆናቸው ይታወቃል። ይሄን እና የምርጫ ቦርድ የግዜ ሰሌዳ ከወጣ ጀምሮ አብዛኞቹ የምርጫ ዝግጅት እንደጀመሩ ከተለያዩ ሚድያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ መረዳት ችለናል። ሆኖም የተወሰኑ ፓርቲዎች መሪዎቻቸው እና አባሎቻቸው በሕግ ጥላ ስር ከመሆናቸው የተነሳ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ሊሳተፉ እንደማይችሉ እየገለፁ ይገኛል።

ኢዜማ የነዚህ ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ አለመሳትፍ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው የመጪውን ምርጫ ልዩ ከሚያደርኩት ምክንያቶች አንዱ የሆነውን የሁሉንም ዓይነት አስተሳሰቦች በምርጫው ለውድድር የመቅረባቸውን ዕድል ስለሚቀንስ ምርጫው ያለው አጠቃላይ ፋይዳ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለን እንሰጋለን።

ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲፈቱ የተጀመረው እንቅስቃሴ በሁሉም ክልሎች በአስቸኳይ ወደተግባራዊ ሥራ እንዲገባ እና በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙ የፓርቲ አመራሮች የሁሉም ዜጋ ሕገ መንግሥታዊ መብት የሆነውን የተፋጠነ ፍትህ ሊያገኙ ይገባል ብለን እናምናለን።

እንዲሁም ሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምርጫ በምናደርገው ዝግጅት በፓርቲዎች የተፈረመውን የጋራ የቃል ኪዳን ሰንድ በማክበር፤ የምርጫ ቦርድ ተአማኒ እና ህግ የሚከበርበት ምርጫ እንዲከናወን የበኩሉን እንቅስቃሴ በማድረግ፤ መንግሥትም ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕግን አክብረው እስከተንቀሳቀስን ድረስ ከውክቢያ ነጻ ሆነን በነጻነት የምርጫ እንቅስቃሴአቸውን እንዲያደርጉ ግዴታውን በመወጣት፤ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና መገናኛ ብዙኃን ከጥላቻ ስብከት የወጣ በእውነት ላይ

ብቻ የተመሰረተ ዘገባና ትንታኔ በማቅረብ፤ በአጠቃለይ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የተመኘነውን ዴሞክራሲዊ ሥርዓት በጋራ እንድናዋልድ ኢዜማ ከአደራ ጭምር ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የሀገራችን የፀጥታ ሁኔታ

በሕዝብ ይሁንታ የቆመ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በየጊዜው የሚደረግ ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት የሚያሳትፍ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማደረግ ወሳኝ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ለእንዲህ ያለ ክንውኖች ካለን ያልዳበረ ልምምድ እንዲሁም ከተቋማት የማስፈፀም ውስንነት በተጨማሪ የሀገራችን ውቅታዊ ሁኔታ በመጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንገነዘባለን፡፡

በትግራይ ክልል ሕወሃት መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት በማድረስ የሀገራችን አንድነት ላይ የጋረጠውን አደጋ ምክንያት መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የተፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል፤ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የዜጎች ሞትና መፈናቀል፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ሁነኛ መፍተሄ ያልተገኘለት የሰላም መደፈረስና በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ የሚገኘው እንግልት እና ሞት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣንን ወደ ዜጎች በማቅረብ፤ እውነተኛና ዘላቂ የሆነ የሕዝብ አስተዳደር፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን የሞላበት የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓትን እና ባህል ለመፍጠር መሰረት የሚጣልበትን ቀጣዩ ምርጫ ላይ ጥላ ያጠሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በሀገራችን ሊመሰረት ያለውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማደናቀፍ ዓላማም ጭምር እንዳላቸው እንረዳለን፡፡

በትግራይ ክልል የተወሰደውን የሀገር አንድነትን እና ሰላምን የማስጠበቅ እንዲሁም ሕግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ እየተከሰቱ የሚገኙ ሥርዓት አልበኝነቶችን ለመቆጣጠር የፌደራል መንግሥት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በፍጥነት የፀጥታ መዋቅር ማቋቋም እና አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ማድረግ ይገባቸዋል።

የትግራይ ክልል ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራንም የክልሉ ሰላም እንዲጠበቅ፣ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እና ነዋሪዎች ወደመደበኛ ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲመለሱ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። በክልሉ ዜጎች ላይ የደረሱ ዘረፋዎች፣ የሴቶች መደፈር፣ የንብረት ውድመት እና ግድያዎችን ገለልተኛ በሆነ አካል ባስቸኳይ እንዲጣራ፣ ሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ እንዲሁም የመገናኛ ዘዴዎች መልሶ አገልግሎት እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ እንጠይቃለን። መንግሥት በክልሉ ከወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የሌላ ሀገር ወታደሮች ጣልቃ ገብነት ከነበረ ይህንኑ በግልፅ እንዲያስረዳ እና እነዚህ ወታደሮች አሁንም በሀገራችን ድንበር ክልል ውስጥ የሚገኙ ከሆነ መቼ እንደሚወጡ ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን።

በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ማንነትን ማዕከል ያደረግ ጥቃት አሰቃቂነት እና ተደጋጋሚነት ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ለጉዳዩ የሚመጥን ትኩረት ከፌደራል መንግሥት እና ከፀጥታ መዋቅሮች እንዲሰጥ እና ንፁሃን ላይ የሚደርሰው ግፍን እንዲያስቆሙ ለማሳሰብ እንወዳለን። በምእራብ ወለጋ በየጊዜው ታጣቂዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ እያደረሱት ያለው ተደጋጋሚና አሰቃቂ ጥቃት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ኢዜማ ያምናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ቡድን ችግር ወደተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሚልክ ሲሆን በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በመመርመር እና ነዋሪዎችን በማረጋገር ችግሮቹን በተመለከተ የሚደርስበትን ድምዳሜ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል።

በአጠቃላይ በእነዚህና በሌሎችም የሰላም መደፈረስ በሚታይባቸው የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች በነፃነት በመደራጀት፣ በመሰብሰብና በመንቀሳቀስ እንዲሁም ሀገራዊ፣ ክልላዊና አካባቢዊ መረጃዎችን በመለዋወጥ፤ ፖለቲካዊ አሳባቸውንና አቋማቸውን በማሰማት እውነተኛ ወኪሎቻቸውን በነፃነት የመምረጥን ዕድል አለማግኝታቸው ያሳስበናል። መንግሥት የጀመረውን የሕግ ማስከበር ተልዕኮ በማፋጠን በእነዚህና በሌሎችም አካባቢዎች ዜጎች ከፍርሃትና ከተስፋ ማጣት ተላቀው እውነተኛ ወኪሎቻቸውን በነፃነት በመምረጥ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተሳታፊነታቸው ሊያረጋገጥላቸው

ይገባል፡፡ ከየትኛውም ጉዳይ በፊት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት መጠበቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።

ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top