Connect with us

የፓርላማ አባላት የፕረሱን ችግር ለምን አልተረዱትም?

የፓርላማ አባላት የፕረሱን ችግር ለምን አልተረዱትም?
ፎርቹን

ነፃ ሃሳብ

የፓርላማ አባላት የፕረሱን ችግር ለምን አልተረዱትም?

የፓርላማ አባላት የፕረሱን ችግር ለምን አልተረዱትም?

(ፍሬው አበበ)

የመገናኛ ብዙሀን አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሚመለከተው ቋሚ ኮምቴ ለውይይት በቀረበበት ወቅት የስም ማጥፋት በፍትሐብሔር የመደንገጉን ጉዳይ መቃወማቸውን ስሰማ ክፍት እንዳለኝ መደበቅ አልችልም፡፡ የፓርላማ አባላቱ ለምን ሳይረዱን ቀሩ የሚል ሀሳብም በውስጤ ተቀጣጥሏል፡፡ የዚህ አጭር መጣጥፍ መነሻም ይኸው ነው፡፡

አዲሱ ረቀቅ አዋጅ ካካተታቸው መልካም አንቀጾች አንዱ እስከዛሬ እንደወንጀል ድርጊት ይታይ የነበረውን የስም ማጥፋት ተግባር በፍትሐብሄር እንዲታይ የሚደነግግ መሆኑ ነው፡፡ እስከዛሬ በወንጀል መታየቱ ምን ችግር አስከትሎ ነበር? የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ የራሱን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ጥቂት ማለት ይወዳል፡፡

እስካሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ መሰረት አንድ ግለሰብ ወይንም ተቋም ስሜ ጠፋ ካለ ጋዜጠኛውይከሰሳል፡፡ ገና ባልተረጋገጠ ጉዳይ ወደቀድሞ ማዕከላዊ ፖሊስ ቀርቦ አሻራ ይሰጣል፣ እንደከባድ ወንጀለኛ ፎቶ ግራፍ ይነሳል፡፡ ክሱ ወደፍርድ ቤት ከተላለፈም ለአመታት ተከራክሮ ወይ ነጻ ይወጣል ወይንም ይፈረድበታል፡፡ 

ይኸ አሰራር በተግባር ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ ተቋማትን ሰዶ ከማሳደድ የዘለለ እርባና አላመጣም፡፡ የፕረስ ነጻነትን በአሰራር ከመጨፍለቅ፣ ከማሸማቀቅ የዘለለ ውጤት አልነበረውም፡፡

አንዳንድ ጊዜ በሚገርም ሁኔታ በሚሊየን ብር የመዘበረ ሙሰኛ በተራ ፖሊስ ጣቢያ ክስ ሲቀርብበት በፕረስ የስም ማጥፋት የተጠረጠረ ጋዜጠኛ ግን በሀገሪቱ ትልቁ የፖሊስ ምርመራ ማዕከል የቀድሞ ማዕከላዊ ቃል እንዲሰጥ መደረጉ ገጠመኝ አልነበረም፡፡ ሆን ተብሎ ፕረሱን ለማሸማቀቅ ሲሰራበት የነበረ ስልት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሕገመንግስት ለፕረስ ተገቢውን ጥበቃ ይደረግለታል ይላል፡፡ “ጥበቃ ይደረጋል” ማለት ድንበር በሌለው ስም ማጥፋት ክስ ስም ፕረሱ መስራት እንዳይሳነው መጠበቅንም ይጨምራል፡፡ አንድ ሰው ወይንም ግለሰብ ስሙ ከጠፋ በብዙ ሀገራት እንደሚደረገው የሚጠይቀው ካሳ ነው፡፡ እገሌ የተባለ ጋዜጣ ወይንም ራዲዮ፣ ቴሌቭዥን…ስሜን አጥፍቶቷልና ተገቢው ካሳ ይከፈለኝ ነው” አቤቱታው መሆን ያለበት፡፡ 

ይህ ደግሞ የፍትሐብሄር ጉዳይ ነው፡፡ ፕረሱ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ፍርድቤት የሚጥልበትን ቅጣት ይከፍልና ወደቤቱ ይሄዳል፡፡ ቢያንስ በዚህ መልኩ መቀጣቱ ለቀጣይ በኃላፊነት ስሜት እንዲሰራ በር ይከፍታል፡፡

እናም የተከበራችሁ የፓርላማ አባላት ሆይ፤ በአዲሱ ረቀቂ አዋጅ የስም ማጥፋት ክስ ወደፍትሐብሄር የመቀየሩ ዓላማ ለፕረሱ ተገቢውን ጥበቃ ከማድረግ አንጻር ያለውን ፋይዳ ልትረዱት ይገባል፡፡ ሁልጊዜ ፕረሱ እንደአጥፊ፣ እንደጠላት፣ እንደሀገር አፍራሽ..  የማየት ካለፉት ህወሓት መራሹ ክፉ ዓመታት የተጋባ፣ የተሳሳተ ስነልቦና መላቀቅ ያሻል፤ ለምን ቢሉ እንዳልጠቀመ በሚገባ የታየ ነውና፡፡

አንዳንዱ የመንግስት ሹም ወይንም ግለሰብ ስሙ በሚዲያ በመነሳቱ ወይንም ስለተቋሙ ወይንም ስለራሱ ሙስናና ብልሹ አሰራር በሚዲያ በመተቸቱ ብቻ “በተነካሁ ስሜት” እየተነሳ “ስሜ ጠፋ” በማለት ፕረሱን የሚያጉላላበት የተለመደ አካሄድ እንዲቀጥል የፓርላማ አባላቱ ሊፈቅዱ አይገባም፡፡ አሁን ጊዜው የለውጥ ነው፡፡ 

ለውጡ በትክክለኛ መስመር ሐዲዱን ጠብቆ እንዲጓዝ የፕረሱ ነጻነትና መብት በተግባር መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ ሀገር እንድትለወጥ መንግስት ከፕረሱ ጋር እንደባላንጣ መተያየቱን አቁሞ በመደጋገፍና በመከባበር መንፈስ ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና አዎንታዊ ሚናውን እንዲጫወት ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከፓርላማ አባለቱ ብዙ ይጠበቃል፡፡

ፎቶ፡- ፎርቹን

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top