የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠን ክብር ለበለጠ የግዳጅ አፈፃፀም አነሳስቶናል – ከፍተኛ የጦር መኮንኖች
በኢትዮጵያ ህዝብ የተሰጠን ክብር ለበለጠ የግዳጅ አፈፃፀም እንድንነሳ የሞራል ስንቅ ሆኖናል ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ገለጹ።
“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሆነው ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ዛሬ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በነበረው መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግሰት የስራ ሃላፊዎችና የመከላከያ መኮንኖች ተገኝተው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍና ክብር ገልጸዋል።
ያነጋገርናቸው የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠን ክብር ለበለጠ የግዳጅ አፈፃፀም አነሳስቶናል ብለዋል።
የህዝቡ ፍቅርና አክብሮት አጠቃላይ ለሰራዊቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ በመሆን ለተጀመረው የህግ ማስከበር ተልእኮ ፍጥነትና ውጤታማነት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል መሐመድ ተሰማ እንዳሉት ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ቁጭት የሀገር ክህደት የፈጸመውን የህውሃት ጁንታ ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሰራዊቱ ህዝቡ የሰጠው ፍቅር መልእክቱ ህዝቡ በአገሩ ህልውና ላይ ለሚመጣበት ሁሉ እንደማይደራደርና በጋራ እንደሚቆም ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እያደረጉት ላለው የተለያየ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመከላከያ ሚኒስትር የመረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌቴናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው “ከጀግና ህዝብ የተፈጠረ ጀግና ሰራዊት” ሲሉ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሆነው ለሰራዊቱ ክብር መስጠታቸው ደግሞ ወትሮም ጀግንነት መገለጫው የሆነውን ሰራዊት ይበልጥ ጀግና እንደሚያደርገው ነው የገለጹት።
“የተደረገልን ክብር ግዳጃችንን በብቃትና በፍጥነት ለመወጣት የሞራል ስንቅ ይሆንልናል” ያሉት ደግሞ በመከላከያ ሚኒስትር የውጭ ግንኙነትና ትብብር ሃላፊ ብርጋዴል ጄነራል ቡልቲ ታደሰ ናቸው።
ሰራዊቱ በጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ላለው ህግ የማስከበር እርምጃ ብርታት እንደሚሆንም ገልጸዋል።
“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አስተባባሪነት የሚከናወነው መርሃ-ግብር በቀጣይም ለመከላከያ ድጋፍ የሚሰባሰቡባቸው ሌሎች መርሃ ግብሮች የሚኖሩት ይሆናል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ እና የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።