ትናንት ዛሬን ያስተምራል
አይቀሬውን ስራ ቀድሞ መሰራት ዋጋ ይቀንስ ነበር፡፡ ዘግይቶ መፈፀም ግን ዋጋው ቀላል አይሆንም፡፡ መንግስት መጠኑን ባለፈ ትእግስት አይቀሬውን ስራ በማዘግየቱ አሁን ከባድ ዋጋ እየከፈለ የትናንቱን ስራ ዛሬ እየሰራው ነው፡፡ ከፍ ያለ ዋጋ ቢያስከፍልም ቅሉ አሁን ግን ስራው የግድ ተሰርቶ ማለቅ አለበት፡፡
የህወሃት ወደር የለሽ ዘረኝነት፣ አማራ ጠልነት፣ዘራፊነት፣ አረመኔነትና ስልጣን አፍቃሪነት ከልክ በማለፉ አይቀሬውን ለውጥ አስከትሏል፡፡ ህውሃት ለውጡን ለመቀልበስ የመጨረሻ ጥረት አድርጎ ቢችል ወደ ስልጣን መመለስ፣ ካልሆነ ግን 2ኛ ግቡ አገር ማፍረስ መሆኑ ትናንትም ይታወቃል፡፡
ነገር ግን ይሄንን ዘራፊ ቡድን በቀላሉ እዚሁ አድስ አበባ መቆጣጠር ሲቻል ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ እስቲገባ ዝም ተባለ፡፡ ይህም ሳይበቃ የትግራይን ወጣትና ህዝብ ወራሪ መጣብህ እያለ የዘረፈውን ሀብት በመጠቀም በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ ተጨማሪ እድል ተሰጠው፡፡
እናም የዘረፈውን ሀብት በየክልሉ በማደል ቅጥረኞችን እያሰማራ አማራዎችን በየክልሉ አስጨፈጨፈ፣ አዘረፈ፣ አፈናቀለቀ፡፡የኦነግ ሸኔ ታሪክም የዚሁ ቡድን ውስጠኛው ክፍል ነው፡፡ ኦነግ ሸኔ በለውጡ ዋዜማ አገርህ ግባ ሲባለ እጅ ነስቶ ገባ፡፡
ግና ብዙም ሳይቆይ ኢምንት አቅም ይዞ ሸፈተ፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል የሚለው ብሂላችን ተረስቶ ወይም ተትቶ በትህነግ እየታገዘ እያደገ፣ እያደገ፣ እያደገ መጣና በመቶዎች የሚቆጠሩ አማራዎችን መፍጀትና መንግስትንም መገዳደር ቻለ፡፡፧ የመተከሉም ጥቃት ቢሆን ብዚሁ የትሀነግ ስምሪት ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ህወሃት በዚህ ሳይበቃው ዛሬ ደግሞ አይደፈሬውን የአገር መከላከያ ሰራዊትን ደፈረና አጠቃው፡፡ እንግዲህ እንዲህ ነው ነገሩ እየሆነ የመጣው፡፡
ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ብሎ ነበር ያገሬው ሰው፡፡ ትእግስትና ጦርነት አለመፈለግ በርግጥ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ከወዲያ ያለው ሰው ማንነት ይወስነዋል፡፡ ጁንታው ይሄንን ትልቅ አስተሳሰብ አለመቻልና ፍርሃት አደርገውና እስከናካቴው ወደ ላቀ ጥቃት ደረጃ እያሸጋገረ አመጣው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ በትህነግ የሆነው፡፡
አሁን ግን ፈንጂውን እረገጠው፡፡ ደማሚቱ ፈነዳ፡፡ከዚህ የአፍሪካ የበላይ ጠባቂ ኃይል ማን ሊያድነው ይችላል? ማንም። በትእግስቱ የተቀጣው መንግስት አይቀሬ የነበረውን ስራውን አሁን ተገዶ እየሰራው ነው፡፡ ከእንግዲህማ ወደ ኋላ መመለስ የለም፡፡ የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ መንግስትና ህዝብ ይህንን ዘራፊና አገር አፍራሽ ቡድን መንቀል ለሀገርና ለህዝቦች አንድነት ሲባል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል፡፡
ይሄንን አሜኪላ ቡድን ማስወገድ ለመከላከያና ለአንድ ክልል ልዩ ኃይል የሚተው ጉዳይ ግን አይደለም፡፡ ትህነግ የሁሉም ክልሎችና ህዝቦች ጠንቅ ነው፡፡ የአማራ ልዩ ሀይል የተለየ ድርሻ የለውም፡፡ የየከልል ልዩ ሀይሎች ሊቀላቀሉት ይገባል፡፡
በዚህ ውስጥ የአማራ ልዩ ሀይልም የድርሻውን ያድርግ፡፡ ጉዳዩም ከትህነግ ጋር ነው እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንዳልሆነም በደንብ ይታወቅ፡፡ የትግራይ
ህዝብ ከወገኑ አማራ ህዝብ ጋር ህወሓት ሆን ብሎ ለማቃቃር እየሰራ እንደሆነ አውቆ ከመከላከያ ጎን መቆምም አለበት።
በመጨረሻም አሁንም መንግስት ካለፉት ስህተቶቹ መማር ይኖርበታል። በትእግስት የሚታዩና የማይታዩ ጉዳዮች መለየት አለባቸው። የዜጎች ደም መፍሰስና የሰብአዊ መብት ጥሰት በትእግስት የሚታይ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ትንሽ ዋጋ መክፈልና ትልቅ ዋጋ መክፈልም አንድና ያው አይደሉም፡፡
በሌላ በኩልም ቀድሞ አደጋን አለመከላከልም ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሁንም
በየቦታው ስጋት ከመሆኑም በላይ ራሱንም መከላከያን እያስጠቃው ነውና ከመተማመን ባሻገር እየተስተወለ እየተተነተነ ይሁን፡፡ የሻሸመኔ፣ የመተከል፣ የጉራፈርዳ፣ የምእራብ ወለጋ፣ የመከላከያ ጥቃቶች ሁሉ ቀድሞ ያለመተንተንና ያለመከላከል ውጤቶች ናቸው፡፡ ከጥቃት በኋላ ከሚወሰድ እርምጃ ይልቅ ቀድሞ የመከላከል እርምጃ መውሰድ እጅጉን ዋጋ ያለው ነው፡፡
አሁን የተጀመረው ህግን የማስከበር ስራ ግን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ሰላምና ልማት መመለስ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የፖለቲካ ሀይሎች፣ ምሁራንና የፀጥታ ሀይሎች ሁሉ በመረባረብ ቶሎ በጨርስ ከዚህ ችግር መውጣት ይገባናል፡፡
እናም ትናንት ዛሬን፣ ዛሬም ደግሞ ነገን ያስተምራሉና መማር ተገቢ ነው በማለት በዚሁ ጨረስኩ።
አመሰግናለሁ!
መሠረት ጀማነህ