በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ጆ ባይደን የወቅቱን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን እየመሩ ሲሆን የአለም መገናኛ ብዙሀን የአሸናፊነቱን አክሊል ከወዲሁ ደርበውላቸዋል።
ጆ ባይደን ከሰአታት በፊት ባሰራጩት የቲውተር መልዕክት እስካሁን ባለው መረጃ በታሪክ ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ያገኘ የመጀመርያው ፕሬዝደንት ለመሆን ተቃርበናል ብለዋል።
ወደነጩ ቤተመንግስት ለመግባት የሚያስፈልገው ኤሌክቶራል ድምፅ 270 ሲሆን እስካሁን ጆ ባይደን 264 ሲያስቆጥሩ ፕሬዝደንት ትራምኘ ደግሞ 214 ላይ ናቸው። ትራምኘ እና ደጋፊዎቻቸው የምርጫው ውጤት ገና ተጠቃሎ ሳይታወቅ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ከወዲሁ ስሞታ ማሰማት ጀምረዋል።
ጆ ባይደን በበኩላቸው ለደጋፊዎቻቸው ለድል እየተቃረቡ መሆኑን ባበሰሩበት ንግግራቸው አሸናፊነት የሚገኘው በህዝብ ድምፅ ብቻ ነው በማለት ለተቀናቃኛቸው ትራምኘ አፍ ማዘጊያ ምላሽ ሰጥተዋል።
…….
ለመሆኑ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ጆ ባይደን ማን ናቸው?
ቢቢሲ እንደዘገበው የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።
ደጋፊዎቻቸው ባይደን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አዋቂ ናቸው ይሏቸዋል። በእርጋታቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛ በግል ሕይወታቸው አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፈዋል።
ባይደን የፖለቲካ ሕይወታቸው የጀመረው ከ47 ዓመታት በፊት ነበር። የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ጥረት ማድረግ የጀመሩት ደግሞ ከ33 ዓመታት በፊት እአአ 1987 ላይ።
ከትራምፕ ጋር አንገት ለአንገት የተናነቁበት ይህ የምረጡኝ ዘመቻ ሦስተኛቸው ነው።
ባይደን በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው።
የቀረቡባቸው ክሶች
ከአንድ ዓመት በፊት 8 ሴቶች ባይደን ጾታዊ ትንኮሳ አድርሰውብናል በማለት አደባባይ ወጥተው ነበር። እነዚህ ሴቶች ባይደን ባልተገባ መልኩ ነካክቶናል፣ አቅፎናል አልያም ስሞናል የሚሉ ክሶችን ይዘው ነው የቀረቡት።
ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ባይደን ከዚህ ቀደም በይፋዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ሴቶችን በጣም ተጠግተው ሰላምታ ሲሰጡ የሚያሳዩ ምስሎችን አውጥተው ነበር።
በአንዳንድ ምስሎች ላይ ደግሞ ባይደን ሴቶችን በጣም ተጠግተው ጸጉር የሚያሸቱ የሚመስሉ ምስሎችን አሳይተዋል።
ከወራት በፊትም ረዳታቸው የነበረች ታራ ሬዲ የተባለች ሴት ባይደን ከ30 ዓመታት በፊት ከግደግዳ አጣብቀው ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመውብኛል ብላ ነበር።
ባይደን በበኩላቸው “ይህ በፍጹም አልተከሰተም” በሚል አስተባብለዋል።
ስህተቶችን ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት
ባይደን በዋሽንግተን ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ልምድ አላቸው። 8 ዓመታትን በተወካዮች ምክር ቤት፣ 8 ዓመት ሴናተር በመሆን፣ 8 ዓመት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝደንት በመሆን አገልግለዋል።
ይህ ግን ፕሬዝደንታዊ ምርጫን ለማሸነፍ ሁሌም በቂ አይሆንም።
28 ዓመታትን በሴኔት ውስጥ ያሳለፉት ጆና ኬሪ እንዲሁም 8 ዓመታትን በሴኔት እንዲሁም 8 ዓመታት ቀዳማዊት እመቤት ሆነው ያገለገሉት ሂላሪ ክሊንተር ከነሱ ያነሰ የፖለቲካ ልምድ ባላቸው እጩዎች ተሸንፈዋል።
የባይደን ደጋፊዎች ግን ባይደን ይህ እጣ እንደማይገጥማቸው ተስፋ አድርገዋል።
ረዥም ታሪክ
ባይደን ባለፉት አስርት ዓመታት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ በተላለፉ ቁልፍ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ውስጥ ተሳትፎ አላቸው ወይም ተሳትፎ እንዳላቸው ይነገራል።
ይህ ታዲያ አሜሪካ አሁን ባለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ በጥሩ መልኩ የሚታይ አይደለም።
ለምሳሌ እአአ በ1970ዎቹ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጥቁር እና ነጭ ተማሪዎችን ለማሰባጠር ተማሪዎች ከሚኖሩባቸው ቦታዎች በአውቶብስ በሟጓጓዝ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለመመደብ የተደረገውን ጥረት ተቃውመው ነበር።
በዚህም ዘንድሮ ባካሄዱት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲተቹ ቆይተዋል።
እአአ 1991 ላይ የባህረ ሰላጤውን ጦርነት ተቃውመው እአአ 2003 ላይ አሜሪካ ኢራቅን እንደትወር ደግፈዋል። መልሰው ደግሞ ባይደን አሜሪካ ወደ ኢራቅ መሄዷ ትክክል አልነበረም በማለት ትችት ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል።
አሳዛኝ ክስተቶች
ባይደን ባለቤታቸውን እና ሴት ልጃቸውን በመኪና አደጋ ምክንያት በሞት ተነጥቀዋል።
ባይደን የመጀመሪያ የሴኔት ድላቸውን ተከትሎ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ባለቤታቸው የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው ነበር። ባለቤታቸው እና ሴት ልጃቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ ሃንተር እና ቤኡ የተባሉት ሁለት ወንድ ልጆቻቸው ላይ ጉዳት ደርሷል።
ቤኡ እአአ 2015 ላይ በአእምሮ ኢጢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ስልጣን፣ ሙስና እና ውሸት?
በሕይወት ያለው ቀሪው ልጃቸው ሃንተር ጠበቃ ሆነ። ገንዘብ ግን ሕይወቱን ከቁጥጥር ውጪ አደረገበት።
ከዚያም ሃንተር ከባለቤቱ ጋር ተፋታ። በፍቺው ወረቀት ላይ የሃንተር የቀድሞ ባለቤት ሃንተር አልኮል እና አደንዛዥ እጽ እንደሚጠቀም እንዲሁም የምሽት መዝናኛ ክበቦችን እንደሚያዘወተር ገልጻለች።
ሃንተር በተደረገለት ምርመራ ኮኬይን በሰውነቱ ውስጥ በመገኘቱ ከአሜሪካ ጦር ባህር ኃይል ተጠባባቂነት ተሰርዟል።
ከዛም ሃንተር ባለፈው ዓመት አንድ ሳምንት ብቻ ካወቃት ሴት ጋር ትዳር መስርቷል። ይህም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
የዩክሬኑ ጉዳይ
ሃንተር በዩክሬን ብዙ ገንዘብ የሚያስከፍል ስራ አግኝተው ነበር።
ፕሬዝደንት ትራምፕ፤ ሃንተር በዩክሬን ሙስና ፈጽሟል በሚል ምርመራ እንዲደረግ የዩክሬን መንግሥት ላይ ጫና አሳድረዋል ተብሏል።
ትራምፕ የዩክሬኑ አቻቸው ዜሌኔስኪ ጋር ስልክ ደውለው፤ የጆ ባይደን ልጅ ሙስና ስለመፈጸሙ እንዲያጣሩ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።