የመቀሌን በር ክፍቱን ትቶ ሚሌን ለመቆጣጠር የወጣው አሸባሪ
(አሳዬ ደርቤ – ለድሬ ቲዩብ)
‹‹የውቅያኖስ ውሃን ዥረት አደርገዋለሁ›› በሚል ድንፋታ ሸለቆና ሸንተረሩን አቋርጦ የሚምዘገዘግ ወንዝ ውቅያኖሱ ውስጥ በገባ ቅጽበት ወንዝ መሆኑ ይቀራል፡፡ ድንፋታውም ይቆማል፡፡ ‹‹ጠራርጌ አጠፋዋለሁ›› ብሎ ያሰበውን ውቅያኖስም ሊያጠፋው ቀርቶ መጠኑ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡
ልክ እንደዚሁ ሁሉ ከትንሽ አውራጃ ፈልቆ መላው ኢትዮጵያን ለማስገበር ሕዝባዊ አጎናፍር አስነስቶ ሲንደረደር የከረመው የሽብር ጎርፍም የመጨረሻ እጣው ሕልውናውን አጥቶ መገበር ወይም ደግሞ መቀበር እንጂ ማስገበር ሊሆን አይችልም፡፡ ዓባይ የተወሰኑ ወንዞችን እያስገበረ ከተጓዘ በኋላ ሜዲትራሊያ ባሕር ሲደርስ ሥሙን ጥሎ እንደሚቀልጥ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩም በእስካሁኑ ጉዞው የተወሰኑ ዞኖችን እያስገበረ መጓዝ የቻለው የሽብር ቡድንም ሕይወቱን ቀርቶ ሥሙን ማትረፍ ከማይችልበት የጉዞ መዳረሻ ላይ ደርሷል፡፡ ምንጩ የደረቀበት ወንዝ ወደ ፊት የሚያደርገውን ግስጋሴ አቁሞ በትነት የሚጠፉ ትንንሽ ኩሬዎችን በሸለቆ መሃከል እንደሚፈጥር ሁሉ፣ ህውሓትም ከምንጩ የሚያጓጉዘውን ሠራዊት ጨርሶ በኢትዮጵያ ሠራዊት ወበቅ በመትነን ላይ ይገኛል፡፡
ወደ አዲስ አበባ እንዳይገሰግስ ብርቱ ግንብ አጋጥሞት፣ ወደ መቀሌ እንዳይመለስ መመለሻ መንገዱ በወገን ጦር ተቆርጦበት በወረረው ምድር ላይ የሚወረርበትን ቀን መቁጠር ግዴታው ሆኖበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም የባጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንደሚባለው ጭፍራን እና ሚሌን ለመቆጣጠር ሲያስብ የሽሬን እና የመቀሌን በር ያለ ምንም ጠባቂ ክፍቱን ጥሎት መምጣቱን አስታውሶ ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ወድቋል፡፡ ኢትዮጵያን ሊያስገብር ይቅርና ወደ ኋላ ተመልሶ ክልሉን ዳግም መቆጣጠር እንደማይችል ተረድቷል፡፡
እራሱን ከአማልክት ተርታ ሲያሰልፍ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ከሰውነት ተራ ዝቅ አድርጎ እሱን ለማገልገል እንደተፈጠሩ ባሪያዎች የሚቆጥረው የሽብር ቡድን ከሚሴ ላይ ያልጠበቀውን ቁጣና ተጋድሎ ካስተናገደ በኋላ ሊያጠፋው የሚፈልግ ሕዝብ እንጂ አገር የሚያፈራርሰው ኢትዮጵያዊ አለመኖሩን ተረድቶ ‹‹በወረርኩት መሬት ላይ ተወርሬ ማለቄ ነውና ድረሱልኝ›› እያለ ምዕራባውያኑን መማጸን ጀምሯል፡፡
ከደሴ እስከ ከሚሴ ባለው መንገድ ላይ በርካታ ሠራዊቱንና አዋጊዎቹን ጨርሶ፣ በየስፍራው ያዘመተው ሠራዊት እንደ ተበላሸ ወተት ተበጣጥሶ፣ በእነ ጌታቸው ረዳ አማካኝነት የሚለቅቀውን ፉከራ ጨርሶ፣ ከአምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ምልጃ እና ከCNN የውሸት መረጃ ውጭ ተስፋ የሚያደርግበት ነገር ቸግሮታል፡፡
በሌላ መልኩ ግን በምዕራቡ ዓለም ፍርዴ ገምድልነትና በሚዲያዎቻቸው ወገንተኝነት ተስፋ የቆረጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእራሱ ውጭ አገሩን ሊያድንለት የሚችል ውጫዊ አካል አለመኖሩን ተረድቷል፡፡ እናም ዘመኑን እና ሕልሙን መንጠቁ አልበቃው ብሎ አገሩን ሊነጥቀው የሚሞክረውን አሸባሪ በወረረው መሬት ላይ ቀለበት ውስጥ አስገብቶ እንዲህ እያለ ይደቁሰው ይዟል፡፡
ከማን በልጠህ ነው- ከማን ተሽለህ
ኢትዮጵያ ትውደም- ብለህ የመጣህ
አፋር፣ አማራው ኦሮሞ፣ ደቡብ
ከመጤፍ ቆጥረህ- የኢትዮጵያን ሕዝብ
ልታንበረክክ- ከያዝክ ግብግብ
ይሄን ጠጣና- አንተው አሸልብ፡፡
የእናት አገሬን- ክብሯን የነካ
አይድንምና-
በግብጽ ድጋፍ- በእነ አሜሪካ
እጣ ፈንታህን- ሞትህን እንካ፡፡
ባንዳ አስገብሮት- አገር ከሚናቅ
ባንተ ሕልፈት ላይ
AGOWA ከስሞ- ዓድዋ ይድመቅ፡፡