Connect with us

ሸረኛ የምዕራባውያን ሚዲያዎችን እኛ ዘንድ ያገነናቸው የእኛው ሚዲያ ነው!

social media

ነፃ ሃሳብ

ሸረኛ የምዕራባውያን ሚዲያዎችን እኛ ዘንድ ያገነናቸው የእኛው ሚዲያ ነው!

ሸረኛ የምዕራባውያን ሚዲያዎችን እኛ ዘንድ ያገነናቸው የእኛው ሚዲያ ነው!

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ቢቢሲ ሲኤንኤን እኛ ዘንድ ማን አገዘፋቸው? የእኛው ሚዲያ እኮ ነው፡፡ እውነተኛ እንደሆኑ፣ ተአማኒነት እንደማይጎድላቸው፣ የሚዛናዊነት ልክ ሆነው እንደሚሰሩ ሲነግሩን ኖረው አሳመኑን፡፡ ዛሬ ሸራቸው የሚያስደነግጠን ለዚህ ነው፡፡

እነኚህ ሚዲያዎች ግን ከዓለም ቀውስ ጋር አብረው አሉ፤ ሊቢያ ያን ከመሰለ ሞገስ ስትወርድ የጎተቷት ደበኞች ናቸው፡፡ ደባን ከዜና ጋር ለውሰው ዓለምን ግራ እያጋቡ እጀ ረዥም ለሆነው ፖለቲካቸው ያግዛሉ፡፡

ከሶሪያ ትርምስ ጎን የከባድ መሳሪያ ያህል ሚናቸው ግዙፍ ነው፡፡ ከኢራቅ እንዲህ መሆን ጀርባ ሚዛናዊ የሚመስለው መርዝ ዘገባቸው አለ፡፡ እነሱ አንድም ቀን ለማንም እውነተኛ የመረጃ ምንጭ ሆነው አያውቁም፡፡ ግን የሀገሬ ሚዲያ በእነሱ ይቀናል፡፡ አይኑን ጥሎ ከቴክኖሎጂያቸው ይልቅ የነገሩትን የሙያ ብቁነት ይቀላውጣል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ለመሰልጠን እሴታቸውን አይፈትሹም፡፡ አሻግረው ባህር ማዶ ያያሉ፡፡ ቢቢሲ የዘገበው ሁሉ ልቅም ያለ ሀቅ ይመስላቸዋል፡፡ ሲ ኤን ኤን ካለ እንደፈጣሪ ቃል ይወስዱታል፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ከቢቢሲው ሞጋች ጋር ያደረጉት ቆይታ እየተተነተነ በሀገሬ ሚዲያዎች እልፍ ዜና ተሰርቶበታል፡፡ የትኛውም የማይገኝ እንግዳ ምን ያህል ድንቅ ቆይታ ከዋልታው ስሜነህ ባይፈርስ ጋር ቢኖረው ግን አንዱም ሚዲያ ያን ወስዶ ዜና ማድረግ ሞት ይመስለዋል፡፡ ቢቢሲ የገደለው ሚዲያ ተቋማት ያሉን ዜጎች በመሆናችን የዳበረ ዲሞክራሲ እንዳያብብ ተቸግረናል፡፡

ሌላው ቢቀር ከቢቢሲ አማርኛ አልያም ከቪኦኤ ወይም ከጀርመን ድምጽ ወስዶ መስራት ነውር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በተቃራኒው ከዚያው ጣቢያ እንግሊዘኛ ቋንቋ ዘገባዎች ዜና ይተረጎማል፡፡ ጠቡ የሀገር ልጅን ከማክበር ነው፡፡ ፍቅሩ ሀገርን ለማፍረስ ከሚያደባ ሚዲያ አንሶላ የመጋፈፍ ነው፡፡
ፋና ከዋልታ፣ ዋልታ ከኢቢሲ፣ ኢቢሲ ከኢቢኤስ፣ ኢቢኤስ ከአዲስ ዘመን ወስዶ ዜና መስራት ምንጭ መጥቀስ ነውር ነው፡፡ ከቢቢሲ መቅዳት ስልጣኔ ተደርጎ ኖሯል፡፡ ቀደም ሲል እድሉ ባልነበረበት ዘመን ይሁን አሁን ግን ህንድ እልፍ ሚዲያዎች እያሏት ሁሉም የኢትዮጵያ ሚዲያ ህንድ ተኮር ዜና ከቢቢሲ ይቃርማል፡፡

ከየሀገራቱ የዜና ተቋማት ዜና ወስዶ መስራት ሞት ነው፡፡ የሀገር ቤት ሚዲያዎች ከሀገራቸው አዲስ ዘመን ይልቅ ምናምን ፖስትን ጠቅሰው ዜና መስራት ክብራቸው ነው፡፡ ይሄ ልማድ በትውልድ አእምሮ ሌላ ነገር ቀርጾ አዲስ አበባ እየኖርን አዲስ አበባን ተከበበች እንኳን ብለው ዜና ሲነግሩን ለማመን ዳዳን፡፡
የምናውቀውን እውነት ያስክዱን ጀመር፡፡ ለሀገራችን ጠር ሆነው በክፉ ቆሙ፡፡ እንዲህ ሲሆን የሀገሬ ሰው ግራ ገባው፤ ቀድሞውኑ ሸራቸው አልተነገረውም፡፡ የራሱ ሀገር ሚዲያዎች አምላክ ስለሆኑ አሁን እየሆኑ ያለው እብደት አወዛገበው፡፡
ፎርቹንን የሚያህል ትኩስ መረጃ አቀባይ ጋዜጣ ባለባት ሀገር ላይ ዘ ኢኮኖሚስትን ካልቃረመ ዜናው የሚሳሳበት ሚዲያ አስፋፋን፡፡ ህዝቡ ስነ ልቦናው በምዕራቡ ሚዲያ እንዲጠረነፍ ግብር ከፍሎ ያቆማቸው የራሱ ሀገር ሚዲያዎች መጥፎ ሚና ተጫወቱ፡፡
ፈረንጆቹ ከራሳቸው የችግር ባርነት አልፈው ዓለምን ባሪያ ለማድረግ ሚዲያዎቻቸውን ቀድመው አዘመቱ፤ እኛ የራሳችንን ህዝብ ከብዙ የኋላ ቀርነት ባርነት ማውጣት ያልቻሉ ሚዲያዎቻችን ጭራሽ ለምዕራብ ሚዲያ ባሪያ አደረጉን፡፡
እውነቱ ግን የምዕራባውያን ሚዲያዎች ሸረኛ ናቸው፡፡ ሚዛናዊነት አልዞረባቸውም፡፡ ሀቅ አጠገብ የሉም፡፡ ለሩቅ ዓላማቸው የሚያደቡ መርዞች ናቸው፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top