“ጠላት በመረጠው የውጊያ ስልት ከፍተኛ ኪሳራ እያስተናገደ ይገኛል” የመከላከያ ሕዝብ ግንኙነት
አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከህፃን እስከ አዋቂ ለወረራ በማንቀሳቀስ ያለ የሌለ ኃይሉን በወሎ መርሳ አቅጣጫና በሃራ ጭፍራ በኩል አሰማርቷል።
ሃገር የማፍረስ ህልሙን የገበሬ አዝመራን አጭዶ ከመውሰድና ንብረት ከመዝረፍ እንዲሁም ከማውደም በተጨማሪ ፣” ከፍተኛ የሰው ብዛትና የሃገር ሃብት አለበት” ብሎ በመረጠው የሐይቅ አቅጣጫን ተከትሎ ለመግባት በሁሉም ግንባር ኃይሉን አሰባስቦ ውጊያ ከፍቷል።
ጠላት ህዝቡን ያሰለፈው በዋናነት በሶስት አሰላለፍ ከፍሎ ነው። የመጀመሪያው ፣ በግንባር የሚዋጋና በሰው ኃይል የበላይነት ወስዶ ፍላጎቱን ለማሳካት እየጣረ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ፣ የቅርብ ድጋፍ ሰጭ ሆኖ የሚተካ፣ ቁስለኛ የሚያነሳ፣ የህዝብ ሃብት ዘርፎ የሚያሸሽ እና የሚያወድም ሆኖ የተደራጀ ነው። ሶስተኛው ፣ ለቀጣይ ግዳጅ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ አድርጎ ህዝቡን የቡድን ፍላጎቱ ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንዲሆን ወደ ጦርነት ማግዶታል።
የወገን ኃይል ፣ የውጊያ ሂሳብ የሚወራረደው ባሰለፍከው ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሚቀርህ ኃይልም ጭምር መሆኑን አውቆ… የጠላት ኃይል ቀጣይ ጦርነትን ሊሸከም በማይችልበት ሁኔታ እየደመሰሰው ይገኛል። ይህ የጠላት ፍላጎት በከሃዲ መሪዎቹ ቀንም ጭምር ቆርጠው ከዚህ እንገባለን፤ እንዲህ እናደርጋለን ያሉትን ፍላጎት ሰራዊታችን በከፍተኛ ተጋድሎ እያመከነው ይገኛል።
የተለያዩ የክልል የፀጥታ አካላት ተጋድሎ እና የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ፣ ወደ ደሴና ኮምቦልቻ ሰርገው የገቡ 17 ውዥንብር ፈጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
የአማራ እና የአፋር ወጣቶች ከሰራዊታችን ጋር እንደ ክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ግንባር ድረስ በመፋለም ላይ ናቸው።
ጀግናው አየር ኃይላችንም ለምድር ኃይሉ ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ በጥልቀት እየገባ የጠላትን የመሳሪያ ማከማቻ ፣ የጥገና ቦታዎችን ፣ ማሰልጠኛዎችን፣ የማዘዥ ጣቢያዎችን እና የሎጂስቲክ አቅርቦት የሚያቀርቡና ሃብት የሚያሸሹትን ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከባድ መሳሪያዎቻቸውን ማውደም ችሏል።
ይህ በጥንቃቄ ተጠንቶ የተለየ ወታደራዊ ኢላማ በመሆኑ ጠላት የተለመደ ጩኸቱን እንዲያሰማ ያደረገው ስኬታማ ምት ነው።
ወደፊትም ጥቂቶች ለህግ ባለመገዛት በኃይል ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር አብረው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢጥሩም ፣ እኛ ልጆቿ እንዳያፈርሷት እናደርጋቸዋለን። የህዝባችን እንባ ይታበሳል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ መሰዋትነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!
የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት።
ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም