የአሜሪካዊው ዲፕሎማት የቲቦር ናዥ ጥያቄ ውስጥ ያልተካተተው የልሂቃኑ ፍላጎት
(አሳዬ ደርቤ- ለድሬ ቲዩብ)
ህወሓት ወደ ሰሜን እዝ በተኮሰው ጥይት እራሱ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በበጀትም ሆነ በሥጋት ከስሩ ያሰለፋቸው ልሂቃን ነበሩት፡፡ ሕዝባቸውን ሰውተው ድርጅታቸውን ለማዳን የሚጥሩ ብሎም ‹‹ዲጂታል›› በሚል ሥም የሚጠሩ ታማኝ ልሂቃን ነበሩት፡፡
በእብሪት የለኮሰው ጦርነት ግን አራት ኪሎን ከእጁ በማስገባት ፈንታ ያላሰበውን ውጤት አስከትሎ መቀሌን ጥሎ ወደ ቆላ ተንቤን እንዲሸሽ ከማድረጉም በላይ ሐብቱን ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ወሳኝ አመራሮቹንም ጭምር አሳጥቶ ድርጎ ሲሰፍርላቸውና ቸክ ሊስት ሲሰጣቸው ከነበሩ ልሂቃን እጅ እንዲወድቅ አደረገው፡፡
ከዚያን ጊዜ አንስቶም ኢትዮጵያን የማሸነፍ እቅዱ ከእነ ሥዩም መስፍን ጋር ማሸለቡን ቢረዳም ይሄንን ሐቅ መናገር እራሱን እንደማነቅ የሚቆጠር በመሆኑ የልሂቃኑን የማይሳካ ፍላጎት ተሸክሞ የሕዝቡን ሕይወት በመሰዋት ላይ ይገኛል፡፡
የትግራይ ጉዳይም ከህወሓት እጅ ወጥቶ በልሂቃን መዳፍ ስር መውደቁን የተረዱት በኢትዮጵያ አሜሪካዊው ዲፕሎማት ቲቦር ናዥ ‹‹የትግራይ ኤሊት ግን የሚፈልጉት ምን ይሆን?›› በሚል ርዕስ የሚከተሉትን አራት ጥያቄዎች አቀረቡ፡፡
-ነጻ ሀገር መመስረት?
-በህውሓት የምትመራ ትግራይን ማየት?
-የእኛ ነው የሚሉትን መሬት ማስመለስ?
-የአንድ ብሔርን የበላይነት ማምጣት?
በበኩሌ ግን ህወሓትን የሚዘውሩት ልሂቃን ፍላጎቶች ዲፕሎማቱ ጥያቄዎች ውስጥ ተካትተዋል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ፍላጎታቸው ‹‹ለአንተ ከምሰጠው እጥፍ አድርጌ ለጎረቤትህ እንደምሰጠው አውቀህ የምትፈልገውን ጠይቀኝ›› ብሎ ፈጣሪ ሲጠይቀው ‹‹አንድ ዐይኔን አጥፋልኝ›› የሚል ምኞቱን ከተናገረው ግለሰብ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡
በዚህም መሠረት የአምባሳደሩ ጥያቄ ከክልል ወጥቶ ‹‹አገራችሁ ላይ እንዲሆን የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው›› የሚል መሆን ነበረበት፡፡
እርግጥ ከጦርነቱ በፊት ‹‹የህወሓትን የበላይነት ማምጣት›› የሚለው የአምባሳደሩ አራተኛው ጥያቄ የኤሊቱም ሆነ የድርጅቱ ምኞት ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ግን ያለፈው ሃያ ሰባት ዓመት ‹‹ሃያ ስምንት›› ብሎ ሊቀጥልም ሆነ ‹‹አንድ›› ብሎ ሊጀምር እንደማይችል ተገንዝበዋል፡፡ ይሄም ምኞታቸው መክሸፉን ከተረዱበት ጊዜ አንስቶ ‹‹ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን ሕልም ከማውደም ውጭ ሌላ ሕልም የለንም›› የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ በትግል አጀንዳቸው ውስጥ ተሸናፊ እንድትሆን የሚያሤሩባት አገር እንጂ አሸናፊ እንዲሆን የሚፈልጉት ብሔር የላቸውም፡፡ ዋነኛ ግባቸውም አምባሳደሩ እንዳሉት መሬት የማስመለስና አዲስ አገር የመቀለስ ሳይሆን ኢትዮጵያ የተባለችን ጥንታዊ አገር የማፍረስ ነው፡፡
በአጠቃላይ የህውሓትን ድርጎ ሲበሉ የኖሩት እነዚህ ልሂቃን ተብዬዎች…. በህወሓት የምትመራ ትግራይን ከማየት ይልቅ በማንም የማትመራና መንግሥት አልባ የሆነች ኢትዮጵያን ማየት የሚመስጣቸው፣ የእኛ ነው የሚሉትን መሬት ከማስመለስ ይልቅ አፋርና ወሎ ገብቶ ደም ማፍሰስ እርካታ የሚሠጣቸው፤ በርሐብ ለሚንገበገብ ሕዝባቸው ከሚከፋፈል እህል በላይ በኢትዮጵያ ላይ የሚጣል ማዕቀብ የሚያጓጓቸው፣ ክልላቸው ላይ የተቋረጠው መብራት ከሚበራበት ቀን ይልቅ በግብጽ ጀት የአባይ ግድብ የሚደበድብበት እለት የሚናፍቃቸውና ለእዚህም ስኬታማነት ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን የሚሰው ሆነዋል፡፡
ስለሆነም የእነዚህ ጥቂት ልሂቃን ፍላጎት ሚስተር ቲቦር ናዥ እንዳሉት ነጻ ሀገር መመሥረት ሳይሆን ኢትዮጵያን ማጥፋት ነው፡፡ በህወሓት የምትመራ ትግራይን ማየት ሳይሆን በማንም የማትመራ ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማየት ነው፡፡
ስለዚህ አዲፕሎማቱ ‹‹ክልላችሁ›› የሚለውን ቃል ሰርዘው ‹‹አገራቸው ላይ እንዲደረግ የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው?›› በማለት ጥያቄውን አስተካክለውት ቢሆን ኖሮ አስበው አስበው መልስ ያጡለትንና ለእነዚህ ጥቂት ልሂቃን ያቀረቡትን ጥያቄ እራሳቸው ይመልሱት ነበር እላለሁ፡፡