Connect with us

ባሕልን ለማስፋፋት- ዲሽታ ጊናን መመልከት!

Social media

ባህልና ታሪክ

ባሕልን ለማስፋፋት- ዲሽታ ጊናን መመልከት!

ባሕልን ለማስፋፋት- ዲሽታ ጊናን መመልከት!
(አሳዬ ደርቤ ~ድሬ ቲዩብ)

ባለንበት ዘመን የየትኛውንም አካባቢ ባሕላዊም ሆነ ሐይማኖታዊ እሴት ማጥፋት አይቻልም፡፡
የአንድ አካባቢን ሕዝብ መገለጫዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋትና ለማጋራት ግን ጥበብ ያስፈልጋል፡፡

የሆነን ማሕበረሰብ ወይም ደግሞ የሆነን ሕዝብ ሙዚቃ፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት… በሌላ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሌሎችን የሚማርክና የሚስብ ጥበብ መጠቀም ግድ ይላል፡፡

ለምሳሌ ያህል ታሪኩ ካንጋሲ ለአሪ ሕዝብ ዓመታዊ ክብረ በዓል ‹‹ዲሽታጊና›› በሚል ሥም ያቀነቀነውን ሙዚቃ ብንመለከት ከኢትዮጵያን አልፎ በተለያዩ አገራት እንዲወደድ ያደረገው የሙዚቃው ስልት ብቻ ሳይሆን የግጥሙ ጣፋጭነትና አካታችነትም ጭምር ነው፡፡ ሙዚቃውን በእልፍ አእላፍ የሰው ልጆች ልብ ውስጥ ሊሰርጽ የቻለው ሰው ሆኖ ስለ ሰው ልጆች የዘፈነው በመሆኑ ነው፡፡‹‹አዳም ወንድሜ›› ስለሚል ነው፡፡ ‹‹የምድር ሥራ እንጂ የሚያስጠይቅ፣ ከእሱ ፊት ስንቀርብ ዘር አያጸድቅ›› የሚል ስለሆነ ነው፡፡

በመሆኑም ዲሽታ ጊና ሁሉንም አካታች በሆነው ሙዚቃው ያለምንም አስገዳጅ ሁኔታ በእራሱ ቋንቋ አስጨፍሮናል፡፡ በደቡብ ኦሞ ሕዝብ ቋንቋና የሙዚቃ ስልተ ምት ለሁሉም የሚስማማ መልዕክት ይዞ በመምጣት በአንድ ነጠላ ዘፈን ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንን ማስጨፈርና ባሕሉን ማስተዋወቅ ችሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም በታዋቂው ሙዚቀኛ በኤኮን ሳይቀር ሪሚክስ ተደርጎለታል፡፡

በሌላ መልኩ ግን ታሪኩ ካንጋሲ እንደ አገር የምንግባባበትን ቋንቋ የሚጠየፍ ወይም ደግሞ አንዱን አካባቢ ሲያወድስ ሌላውን የሚወቅስ ሙዚቀኛ ቢሆን ኖሮ ዘፈኑ ከአካባቢው ማሕበረሰብ አልፎ ወደ ሌላው ሕዝብ የመተላለፍ አቅም አይኖረውም ነበር፡፡

አርቲስቱ ግን የዘፈን ግጥሙን እንደ አገር በምንግባባበት ቋንቋ ተርጉሞ በማቅረብ በእራሱ ቋንቋ የጻፈውን ግጥም ሳይቀር እንዲሸመደድ ማድረግ ቻለ፡፡

ደቡብ ኦሞ አሪ መንደር ውስጥ ሆኖ ከብት እየጠበቀ መላው የሰው ልጅን ባካተተ መልኩ በቀመረው ሙዚቃው በተለያዩ ዓለማት ሆነው ሙዚቃውን የሰሙትን ሰዎች ወደ ትውልድ መንደሩ (ወደ አሪ) መውሰድ ቻለ፡፡

ልክ እንደዚህ ሁሉ ሃይማኖትንም ሆነ ባሕልን ለማስፋፋት ከጦር ይልቅ ፍቅር ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ ከእምነቱና ከባሕሉ ተከታይ ውጭ የሆነውን ሕዝብ ከማግለል ይልቅ የተለያዩ የጥበብ መንገዶችን በመከተል እንዲቀላቀል መሳብ ትልቅ ሚና አለው፡፡

የእራሱን የእምነት ተከታዮች ሰብስቦ ‹‹ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ወደ ሲዖል የሚያስገቡ የስህተት መንገዶች ናቸው›› ወይም ደግሞ ‹‹ከእናንተ ውጭ የሆነ ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎችን አግሉሏቸው›› እያለ ከሚሰብክ የሃይማኖት አባት ይልቅ ወደ ሌሎች እምነት ተከታዮች ዘንድ ሄዶ የእራሱን እውነትና እምነት የሚናገር መምሕር ሃይማኖቱን የማስፋፋት እድል አለው፡፡

ባሕልንም ቢሆን ለማስፋፋት ከሃይል ይልቅ ሌሎችን የሚስብ የፍቅር ቃል እና አካታች ምሥል ፋይዳው የትየለሌ ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ባሕልንም ሆነ ቋንቋን፣ ሙዚቃንም ሆነ የትኛውንም እሴት ለሌሎች ለማጋራት ‹‹የእራስህን ጥለህ የእኔን ተቀበለኝ›› በሚል አቋም ጦር ከሚሰብቅ ንጉሥ ይልቅ ከፖለቲካ በጸዳ መልኩ ‹‹የአንተንም ባሕል ስጠኝ፤ የእኔም ባሕል ተጋራኝ›› እያለ የሚሰብክ የጥበብ ሰው ትልቅ ጉልበት አለው፡፡

ባሕልህን ሊጋራ የመጣውን ሕዝብ ከማስበርገግ ይልቅም በዓሉ ላይ ያልተገኘውን ሕዝብ ስቦ የሚያመጣ የጥበብ መንገድ መፈለግ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top