[የህወሃት ቁማር]
(ፋሲል የኔዓለም)
የህወሃት የጦር መሪዎች፣ በተለይም ጄ/ል ታደሰ ወረደ እንደተናገሩት፣ የህወሃት የጦርነት አላማ የትግራይን ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጥቃት መከላከል ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ማዳከም ያስፈልጋል።
የትግራይም ህዝብ፣ በወሬ ሳይወናበድ፣ ከህወሃት ጎን ቆሞ በመታገል፣ ለግቡ መሳካት አስተዋጾ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የትግራይ ወጣት ህይወቱን የሚገብረው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት አቅም ለማዳከም ከሆነ፣ ይህን ማሳካት ይቻላል ወይ የሚለውን መጠየቁ ተገቢ ይሆናል። ህወሃት ራሱን ወይም እሱ እንደሚለው የትግራይን ህዝብ ከጥቃት ለመከላከል የሚችለው ቢያንስ ከሶስቱ አንዱን ቅደመ ሁኔታ ማሟላት ሲችል ነው ።
አንደኛው፣ ህወሃት መከላከያ ሰራዊቱን ሙሉ በሙሉ ደምስሶ፣ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ሲችልና ሌላ ተቀናቃኝ ሃይል እንዳይፈጠር አድርጎ መቅረጽ ሲችል ነው ። ህወሃት አሁን ባለው ቁመና እንኳንስ መከላከያ ሰራዊቱን ሙሉ ለመሉ ደምስሶ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ይቅርና፣ ራሱን እንኳን ከጥቃት መከላከል አይችልም።
ሁለተኛው ቅደመ ሁኔታ፣ ከመከላከያ ሰራዊት በሰው ሃይልም ሆነ በጦር መሳሪያ ብዛትና ጥራት እኩል ወይም በልጦ ሲገኝ ነው። ህወሃት ይህን ማድረግ ከቻለ፣ በህወሃት እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል የሃይል ሚዛን (balance of power) እኩልነት ይፈጠራል ማለት ነው።
ይህን እኩልነት ለመፍጠር ግን ህወሃት ከመከላከያ ሰራዊት የተሻለ የሰው ሃይል ምልመላ፣ የጦር መሳሪያ ግዢና ሌሎች እንደ ምግብ፣ ነዳጅ ዘይትና የመሳሰሉትን ነገሮች ግዢ ማካሄድ አለበት። ህወሃት ይህን ለማድረግ አቅሙም መንገዱም የለውም። ቀደም ብሎ በዘረፈው ገንዘብ መግዛት ይችላል ቢባል እንኳ፣ ማስተላለፊያ መንገድ የለውም።
በየትኛውም መመዘኛ ህወሃት ከመከላከያ ሰራዊት የተሻለ ወይም እኩል አቅም በመገንባት የሃይል ሚዛን እኩልነት መፍጠር አይችልም።
ሶስተኛው ቅድመ ሁኔታ ስትራቴጂክ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቅ ሲችል ነው። ለምሳሌ አቶሚክ ቦንብ፣ የተለያዩ ሚሳኤሎችና ድሮኖች። የኒውኪሊየር ሃይል የታጠቀን ትንሽ አገር፣ የኒውክሌር ሃይል የታጠቀም ይሁን ያልታጠቀ ትልቅ አገር፣ ሊደፍረው አይችልም።
ጉዳቱ የሁሉም ነውና። ህወሃት ደግሞ ስትራቴጂክ የሚባሉትን ሶስትና አራት ሚሳኤሎች ባህርዳር፣ ጎንደርና አስመራ ላይ ተኩሶ በቆሎ ጠብሶባቸዋል።
በዚህ መንገድ ስናየው፣ ህወሃት እንኳንስ የትግራይን ህዝብ ከጥቃት ሊከላከል ይቅርና ራሱንም በዘለቄታ የሚያድንበት አቅም የለውም። ለነገሩ የትግራይ ህዝብ አዳኝ አያስፈልገውም። የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ጠላት የለውም። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የመጣ ማንኛውም ጠላት፣ የትግራይ ህዝብም ጠላት ነው፤ በትግራይ ህዝብ ላይ የመጣ ጠላትም፣ እንዲሁ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው።
ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የመጣ ጠላት ነው፣ ስለዚህ ህወሃት የትግራይ ህዝብም ጠላት ነው። ይህ እውነት ዛሬ ላይ ባይገለጥልን እንኳን፣ ነገ እንደሚገለጥልን አምናለሁ።
የትግራይ ህዝብ ወንዝ ለማይሻግረው የህወሃት አላማ፣ የሰው ግብር እየገበረ መቀጠሉን በደንብ ሊያስብበት ይገባል። ህወሃትን እንደ አዳኝ የሚያዩ ሰዎች፣ እውነተኛ ደህንነት የሚገኘው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በፍቅርና በአንድነት በመኖር እንጅ፣ የህወሃትን ጥላቻ በማስተጋባትና ህይወት በመገበር አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።