ይርጋ ዓለም እንደ ስሟ የረጋችው ውብ ምድር፤
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ታሪካዊቷ ይርጋዓለም ጎራ ብሎ ነበር፡፡ እንደ ስሟ የረጋችው ከተማ ምንጮች የከበቧት ውብ ምድር ናት ይለናል፡፡ ታሪካዊቷ ከተማ ስሟ ከኢትዮጵየጣ አርበኝነት ታሪክ ጋርም ይቆራኛል፡፡ ዘገባውን ታነቡት ዘንድ ጋብዘናል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ይርጋ ዓለም መጣሁ፡፡ ሠላም የበዛላት ከተማ፡፡ እንደ ስሟ ናት፡፡ ለምን እንደሁ አላውቅም በሀገሬ አብልጬ ከምወዳቸው ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ድባቧ ደስ ይላል፤ ደርባባነቷን እወድዋለሁ፡፡ እንኳን ከእኔ ጋር መጣችሁ፤ ዳኤ ቡሹ።
በ1923 አበበች፡፡ ገበሬዎቿ እነ ባላምባራስ ዱባለ ሀንካርሶ እና እነ አቶ ቃቃቦ ሁርሶ ናቸው፡፡ ይርጋ ዓለም ስትነሳ ታላቁ ሰው ራስ ደስታ ዳምጠው ከፊት ይጠራሉ፡፡ ወይና ደጋ ናት፤ አየሯ ሞቀኝ ብለው አይከፉም፣ በረደኝ ብለው አይጨመደዱም፡፡ ለሁሉ የምትሆን ሁሉን የምትማርክ ከተማ፤
ደግሞ ወደብ ናት፤ ወደ ታላቁ አቦ ወንሾ ለመሄድ የምታሻገር፣ ደግሞ የተፈጥሮ መዲና ናት፡፡ ወንዞች የከበቧት፣ ምንጮች የሞሉባት፡፡ ይርጋ ዓለም አንድ ከተማ ሆና በብዙ ትጠራለች፤ በብዙ ትገለጻለች፡፡
የሲዳማ ምድር ዓይነተ ብዙነት ማሳያ ናት፡፡ እዚህ ፈዋሹ ፍል ውሃ ስሙ ገኖ ኖሯል፡፡ ትናንት ብቻ እንዳትመስላችሁ ዛሬም አላት፤ አሁንም ታሪክ ይሰራባታል፡፡ የዚህ ትውልድ አሻራ ሊያውም በዋሻ በታነጸ ቤተ ክርስቲያን ተገልጾባታል፡፡ ስትመጡ ዋሻ ማርያም ብላችሁ ጠይቁ፣ እስትንፋሰ ክርስቶስን አሳዩን በሏቸው፡፡
አርበኛ መዲና ናት፡፡ የአምስት አመት እንቢኝ ለሀገሬ በሚል ታላቅ የጦር ተጋድሎ ከተደረገባቸው የሀገራችን ከተሞች አንዷ ይርጋ ዓለም ስትሆን ታሪክ አርበኛዋ ከተማ ይላታል፡፡ የራስ ደስታ ጀግንነት፣ የሲዳማ አባቶች ተጋድሎ ሀገርን የመታደጉ የነጻነት ትግል በይርጋ ዓለም ምድር የተጻፈ ህያው ታሪክ ነው፡፡
እንደ አሊቶ ሄዋኖ ያሉ ታሪክ አንዳች የልካቸውን ያክል ያልነገረላቸው ጀብድ የተሞላ የአርበኝነት ተጋድሎና ለነጻነት የመሞት ውሳኔ የጥንስስ መዲናዋ ይርጋ ዓለም ናት፡፡
እስከ ዶሎ የዘመተው የራስ ደስታ ዳምጠው ትንታግ የሲዳማ አርበኛ ደጀን ሆና መርቃ ሰላም ይመልስህ ያለችው ይህቺ ከተማ ነበረች፡፡ ከራስ ስም ሀገር፣ ከራስ ህይወት የማይሞት ስም የመረጡት እንደ አሊቶ ሄዋኖ ያሉ ጀግኖች ነገ እንዴት ሳንሰማው የሚያስብሉ የጀብድ ታሪኮች የምናደምጥላቸው ናቸው፡፡
ከሸበዲኖ እስከ ይርጋዓለም፣ ከሐዋሳ እስከ አባያ ብዙ ታሪክ በደም ተጽፏል፡፡ እነ ግራዝማች መንግሥቱ ሐሜሶ ዛሬም ከነጻነት ታሪክ ጋራ ስማቸው አብሮ ይነሳል፡፡
ይርጋ ዓለም የዚያን ዘመን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል ነበረች፡፡ ዛሬም በከተማዋ የሚገኝ የራስ ደስታ ዳምጠው ቅርስ ቤት የታሪኳ አንድ ማስታወሻ ሆኖ ይኖራል፡፡
እንደ አረጋሽ ሎጂ ያሉት ብዙ የውጪ ሀገር እንግዶች ከሲዳማ ደጋ ምድር ጋር እንዲተዋወቁና ውቡን የቡና ምድር እንዲጎበኙ ምክንያት የሆኑ የይርጋዓለም ጸጋዎች ናቸው፡፡ እንደ ቅድስት አርሴማ ያሉት ደግሞ የሀገር ውስጥ እንግዳን በማምጣት ከይርጋዓለም መጠሪያዎች መካከል ይገለጻሉ፡፡
በታላቋ ንግሥት በፉራ ስም የተሰየመው የይርጋ ዓለም ልዩ ተቋም የከተማይቱ ሌላ ጌጥ ነው፡፡ ኮሌጅ ነው፡፡ ኮሌጅ ብቻም አይደለም፤ ከጉባኤ ቱሪዝም ከተማይቱን አስመርጧል፡፡
ይርጋ ዓለም በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ የታላላቆቹ እትብት መቀበሪያ ናት፡፡ የእነ ደበበ ሰይፉ፣ የእነ አብረሃም ረታ አለሙ፤ ታሪክ ነጋሪው ገነነ ሊብሮም እትብቱን ይርጋ ዓለም አስቀብሮ የወጣ ነው፡፡
ይርጋ ዓለም የአቦ ወንሾ በራፍ-ኑ እስቲ ወዲያ ልውሰዳችሁ፡፡