Connect with us

ሕሊና ቢስ ሐኪሞቻችንን ምን እናድርጋቸው?

Social media

ነፃ ሃሳብ

ሕሊና ቢስ ሐኪሞቻችንን ምን እናድርጋቸው?

ሕሊና ቢስ ሐኪሞቻችንን ምን እናድርጋቸው?
( ገለታ ገብረወልድ – ድሬቲዩብ )

ሁሉንም የሙያ መስኮችና ሙያተኞቻቸውን በጅምላ ማመስገንም ሆነ መውቀስ አይቻልም ፡፡ በሰዉ ልጆች መካካል ከአፈጣጠራችንና ከአስተዳዳጋችን ጋር በተያያዘ ልዩነት የመኖሩን ያህል በባህሪም ሆነ በተግባር አንዱ ከሌላው የተለያየ ነው ፡፡

ይሁንና የጤናውን ዘርፍ በመሰሉ ሩህሩህነት ፣ረጂነት ፣አጋዥነትና ህይወት አዳኝነት ግድ በሆኑባቸው ሙያዎች ውስጥ የስነምግባ መርሆችና የሙያዉ ህገደንቦችን መተግበር ብቻ ሳይሆን የህሊና ተገዥነት ሙያተኛውን ሊያቀራርበው ይገባል ፣ግድም ነው፡፡ በተለይ የእኛን አገር ለመሰሉ በድህንት ውስጥ ላሉ ግን ለበዙ ህዝቦች ይህን እውነት መመርመር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

በሳለፍናቸው የቅርብ ወራት በርካታ የአገራችን ሀኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ አጋልጠው ብዙዎችን ለመታደግ ሲረባረቡ ታይተዋል ፡፡

ከሙያ ጥረታቸው ባሻገር ደም ለግሰው ፣ ለተቸገሩ ከአነስተኛ ገቢያቸው አዋጥተው ደሆችን እረድተው ፣በግጭት ወቅት ግንባር ድረስ እየዘመቱ ቁስለኛን አክመው፣ የተፈናቀሉትን አይዞችሁ ብለው …ወገንነታቸውንና የህሊና ሰዉ መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ፡፡

በዚያው ልክ የሞራል ዝቅጠቱና ህሊና ቢስነቱ ድንኳን የተከለባቸው ግፈኞች እዚያም እዚህም መታየታቸው አልቀረም ፡፡ ተደጋሞ አንደታየው የመንግሥት ሆስፒታሎችና አነስተኛ ተቋማት የህክምና መሳሪያዎች እየወጡ የግል ክሊኒኮች መጠቀሚያ ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ነው፡፡

እንዲሁም ሰሞኑን ጉለሌ ክፍለከተማ ላይ እንደታየው ለበሽተኞች /ህመምተኞች/ ከታዘዙ መድሐኒቶች ላይ እየተቀነሰ ለግል ፋርማሲዎች /መድሃኒት ቤቶች/ የመስጠት ህሊና ቢስነት ደርቷል ፡፡

.. የግል ክሊኒኮች ህመምተኞችን አስተኝተው ገንዘባቸውን ካሟጠጡ በኋላ ሊሞቱ ሲሉ ወደ መንግስት ሆስፒታል የሚላኩበት አሰራርም አለ አሉ፡፡

በሽተኛውን ሊሞት ሲል ወደመንግስት ሆስፒታል የሚልኩት በእነሱ የግል ክሊኒክ ውስጥ ከሞተ በህግ ከመጠየቃቸውም በላይ የክሊኒኩ ስም ስለሚጠፋና ‹‹እገሌ ክሊኒክ የገባ በሽተኛ ሞቶ ነው እንጂ ድኖ አይወጣም›› ስለሚባል የክሊኒኮቹን ገጽታ ስለሚያጠይምና ደምበኛ /ተገልጋይ/ ስለሚያሳጣ በዚህም የተነሳ ጥቅማቸው ሊቀር /ሊቀንስ/ ስለሚችል እንደሆነ ይነገራል ፡፡

በተለይ ከህዝብ ሰአትና ጉልበት እየሰረቁ ከአንዱ የግል ህክምና ወደ ሌላው በመፈትለክ በሽርፍራፊ ሰከንዶች አስር ሺ ብሮችን በቀን ለማጋበስ በሚጣደፉ ሙያተኞች አሻጥር ማለት ነው፡፡

… የማያስፈልግ የምርመራ አይነት በማዘዝ የድሃውን ታካሚ ኪስ ማራቆት ፣ በአልጋ ፣ በምግብ ፣በማቆያና ምርመራ ፣ሌላው ቀርቶ ነብስ ከወጣ በኋላ በአስከሬን ምርምራና ማንሻ … ወዘተ ታካሚና አሳካሚ የሚያለቅስበት ጊዜ እጅጉን በዝቶ እየታየ ነው፡፡

ፈጣሪ ያሳያችሁ ለበሽተኛ የታዘዘ መድሐኒት እየተቀነሰ የሚሸጥበትና የግል ጥቅም የሚካበትበት አሰራር መኖሩስ ‹‹ህሊናችን የትሄደ? ሰብአዊነታችንስ ወደየት ጠፋ?›› አያሰኝምን? በሽተኛው የታዘዘለትን መድሃኒት በሙሉ ማግኘት እንዳለበት ነጋሪ ያስፈልገናልን?

መንግስትስ እንዲህ አይነቱን ነገር እንዳይከሰት ማድረግ ይችላልን? ከተከሰተ በኋላ እርምጃ ይወስዳል እንጂ… ይከሰታል ብሎ ሲቃዡ ማደርስ እንዴት ይቻላል ፡፡

የራሳችን ህሊና ይህ ነገር ‹‹መጥፎ መሆኑን ካላዘዘን !!
ከኮሮና ሕመም ጥኙ ሕክምና አስፈልጎአቸው ወደመንግስት የህክምና ተቋማት የሚላኩ ሕሙማን ደግሞ ዓይን ያወጣ ዘረፋ እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡

በቦሌ ቡልቡላ ማቆያ የዚሀ ጹሑፍ አቅራቢ የገጠመውን ላንሳ፡፡ ሐኪም ተብዬዎች በጤና ጥበቃ ያልተፈቀዱና ስድስት ፍሬ ኪኒን እስከ አስር ሺ ብር የሚያወጣ መድሃኒት ቤተሰቦች እንዲገዙ ጠይቀዋል፡፡ እስ ብቻ አይደለም፣ በኮንትርባንድ የሚገባው መድሃኒት የትኛው ፈርማሲ እንደሚገኝ ሁሉ ጥቆማ የሚሰጡ ሐኪሞች መፈጠራቸው አስገራሚ ነው፡፡

ቤሰተቦቻችን ይህ ከአቅማችን በላይ ነው ሲሉ “በቃ ተውት” የሚል መልስ ተሰጥቶአቸዋል፡፡ ዋናው ቁምነገር መድሃኒቱ መታዘዙ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ እንኳን ገብቶ ሊያየው ለማይችለው ጽኑ ታማሚ እነዚህ ነጋዴ ባለሙያዎች ያዘዙትን መድሃኒት በትክክል ስለመስጠታቸው እንኳን ማመን አለመቻሉ ነው፡፡

ከኮቪድ ሕሙማን እርዳታ ጋር ተያይዞ በግሉ ዘርፍ ያለው ዘረፋ ተደጋግሞ የተባለበት በመሆኑ አልመለስበትም፡፡
አንዳንዴ እንደ አገር በብዙ ወጣውረዶች ውስጥ ያለፍንና አሁንም በፈታኛ ሁኔታ ውስጥ ያለን ብንሆንም ፣ ነውር የሌለበት ህሊና ለምን አጣን ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ፡፡

በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ሥራ 24፡17 ላይ ‹‹በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ህሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ›› ተብሎ አልተፃፈምን? ኧረ ባካችን ጎበዝ !

መጥፎ ነገር ሁሉ በመንግስት በህዝብና በፈጣሪ ፊት እንደሚያስጠይቀን ህሊናችን አይመሰክርልንምን? በአንደኛ ቆሮንቶስ 1፡12 ላይ ‹‹… ህሊናችን ምስክር ነው›› የተባለውን አልሰማንምን? ነው ወይስ አይሰማም !

ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር በደመወዝ በአበልና በቦነሰ ስም ከአቅማችን ከችሎታችንና ከአበርክቷችን በላይ የሚከፈለን አንሶ፣ የተሰጠንን ኃላፊነት/ ህዝብ ለፍቶ ያስተማረንን ሙያ እንደጐራዴ እየተጠቀምን የሕዝብን አንገት የምንቀነጥሰው እስከመቼ ነው ያስብላል ፡፡

የዛሬ ትኩረቴ የጤናው ዘርፍ ላይ በመሆኑ ትዝብቴ በዛው ላይ ሆነ እንጂ፣ ጉዳዩ እንደሰው ሁላችንንም የሚመለከት ነው ፡፡ እባካችሁ ወገኖቼ በመልካም ህሊና እንኑር … ህሊናችን ደካማ ከሆነ እንረክሳለን… ህሊና የእግዚአብሔር መብራት ነው…

በንፁህ ልብና በበጐ ህሊና እንሥራ… ከሞተ ሥራችንም ህሊናችንን እናጽዳ…ብሎ መቋጨት ይሻላል ፡፡ አሜን!

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top