Connect with us

አዲስ አበባን የሸፈናት ጉም ምንድነው?

አዲስ አበባን የሸፈናት ጉም ምንድነው?
የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት

ነፃ ሃሳብ

አዲስ አበባን የሸፈናት ጉም ምንድነው?

አዲስ አበባን የሸፈናት ጉም ምንድነው?

ዛሬ በጠዋቱ መዲናችን አዲስ አበባ ባልተለመደ መልኩ የተለያዩ ክፍሎቿ በጉም ተሸፍነው በቅርብ ርቀት ያሉ ህንፃዎችን ጭምር ማየት እንዲሳነን ሆነናል፡፡ ታድያ እኛም ይህን ክስተት አስታከን ጥቂት ስለ ጉም ልናጫውታችሁ ወደድን፤ አብራችሁን ሁኑ፡፡

ጉም እንደ ማንኛውም ደመና ሆኖ መሬትን የሚነካ መሆኑ ግን ለየት የሚያደርገው ነው፡፡ ይህ ጉም አንዳንዴ ስስ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወፍራም ሆኖ ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ታድያ ጉሙ ወፈር ብሎ ሲገኝ ነው አሻግሮ ማየትን ባስ ሲልም በቅርብ ርቀት መተያየት እስኪያስቸግር ድረስ እይታን በነጭ መጋረጃ የሚጋርደው፡፡ 

በዚህም ትላልቅ ህንፃዎች፣ ባለ ግርማ ሞገስ ተራሮች እና ሌሎችም ግዙፋን አካላት በቦታው የሌሉ እስኪመስል ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊጋረዱ ይችላሉ፡፡

የጉም አፈጣጠር ተኖ ጋዝ የሆነ ውሃ ወደ ፈሳሽነት በሚለወጥበት ጊዜ (Condensation) ሞለኪውሎቹ ተጣምረው እጅግ ጥቃቅን የሆኑና በዚህም ሳብያ በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ውሃዎችን ሲፈጥሩ ነው፡፡ ጉሙን የምናየውም በነዚህ ጥቃቅን ፈሳሽ ውሃዎች ምክንያት ነው፤ አለበለዚያ የተነነው ውሃ ጋዝ በመሆኑ ላይታየን ይችል ነበር፡፡

ይህ በእዲህ እንዳለ ግን አንድ ጉም ተፈጥሮ ዙርያችንን ለመክበብ የከባቢያችን አየር እጅጉን እርጥበት አዘል መሆንና በፍተኛ መጠን በተነነ ውሃ የተሞላ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም እንደ አቧራ አልያም ሌላ አየሩን የሚበክሉ ጥቃቅን ቁሶችም በአየሩ ውስጥ መገኘት አለባቸው፡፡ በዚህም የተነነው ውሃ በእነዚህ ጥቃቅን ቁሶች ላይ ሆኖ ወደ ፈሳሽነት ይቀየራል፡፡ 

በጨዋማ የውሃ አካላት አካባቢ ደግሞ የተነነው ውሃ በጨው ብናኞች ላይ ሆኖ ሲቀየር የባህር ጉም (Sea Fog) ተብሎ የሚጠራውን ጉም ይፈጥራል፡፡ ታድያ በአየር ላይ ባለው እርጥበት የሚወሰን ቢሆንም ጉሞች በድንገት ሊከሰቱና በዚያው ፍጥነት ሊሰወሩም ይችላሉ፡፡

በምድራችን የተለያዩ አይነት ጉሞች ሲከሰቱ እናያለን፡፡ እነዚህም እንደሚከተለው ቀርበዋል፤

የራዲዬሽን ጉም፤ በምሽት የሚፈጠር ሲሆን መሬት በቀን ውሎዋ ያጠራቀመችውን ሙቀት ወደ አየሩ ስትለቅ የሚከሰት ነው፡፡ ሙቀቱ ከምድር ወደ አየር በሚሸጋገርበት ጊዜ የውሃ ጠብታዎች መፈጠራቸው ለዚህ ምክንያት ይሆናል፡፡

አድቬኬሽን ጉም፤ ይህ ዓይነት ጉም ደግሞ ሞቃታማና እርጥበት አዘል አየር በቀዝቃዛ አካል ላይ ሲያልፍ የሚከሰት ነው፡፡ እርጥበታማ እና ሞቃታማ አየሩ ከቀዝቃዛው የመሬቱ አየር ጋር ሲነካካ የተነነው ውሃ መልኩን ቀይሮ ፈሳሽ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህ ሂደትም በሳይንሳዊ አጠራሩ አድቬክሽን ተብሎ ሲጠራ ብዙውን ጊዜ የትሮፒካል አየር ከቀዝቃዛ የውቅያኖስ ውሃ ጋር ሲነካካ የሚፈጠር ነው፡፡

የሸለቆ ጉም፤ ብዙውን ጊዜ በክረምት ወራቶች ተራራና ሸለቆዎች ውስጥ የሚፈጠር ነው፡፡ አፈጣጠሩም ተራሮች አልያም ሸለቆች ውስጥ የተጠቀጠቀውን አየር እንዳያልፍ አግደው ሲያስቀሩት የሚከሰት ነው፡፡ አንዳንዴ ሁኔታው አደገኛ ሊሆንም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከ90 ዓመታት በፊት በቤልጅየሙ የሚዩስ ሸለቆ ውስጥ የተነነ ውሃ በበካይ የአየር ቁሶች ላይ ሆኖ በመቀየሩ ሳብያ ከ60 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተው ነበር፡፡

የቅዝቃዜ ጉም፤ በተለምዶው ደመና በሸፈናቸው ተራሮች ላይ የሚከተው ይህ ዓይነት ጉም ፈሳሽ የደመና ጠብታዎች በአንድ ቁስ ላይ ቀዝቅዘው ሲቀሩ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ አይነት ቀዝቃዛ ጉም ከአካባቢው ተነስቶ ከሄደ በኋላ ምድሩም ሆነ ዛፎች እና እንደ ሸረሪት ድር ያሉ አካላት ጭምር ስስ የበረዶ ሽፋን ተነስንሶባቸው ልናገኝ እንችላለን፡፡ መሰል ጉሞች ቀዝቃዛና እርጥበታማ አየር ፀባይ ባላቸው እንደ ስካንዲኔቪያ እና አንታርክቲካ ባሉ አካባቢዎች ላይ በብዛት መመልከቱ የተለመደ ነው፡፡

ስለ ጉም ካወራን አይቀር ከጉም ላይ ውሃን ስለመሰብሰብም ጥቂት እንበልዎ፡፡ በተለያዩ ማህበረሰቦች ጉም ሲከሰት ትላልቅ የውሃ ማስቀመጫዎችን ከዛፍ ስር በማስቀመጥ በዛፉ ላይ የሚወርደውን ውሃ በመሰብሰብ ጥቂት ውሃን የማግኘት ባህል ነበር፡፡ አሁን ላይ ታድያ የዘመናችን ባለሙያዎች ውሃን ከጉም ላይ የመሰበሰብ ስልትን በዘመናዊ መንገድ ተግባራዊ አያደረጉ ይገኛል፡፡ 

ታድያ አንዳንድ አካባቢዎችም ዋነኛ የውሃ አቅርቦታቸውን ከጉሞች ላይ በመሰብሰብ እስከማግኘት ደርሰዋል፡፡

ምንጭ፡- ( የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top