Connect with us

ወደ ምስራቅ ተጉዘናል…

ወደ ምስራቅ ተጉዘናል...
ሔኖክ ስዮም

ባህልና ታሪክ

ወደ ምስራቅ ተጉዘናል…

ወደ ምስራቅ ተጉዘናል…

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዮም ለዛሬ ደግሞ ከአዲስ አበባ 461 ኪሎ ሜትር ተጉዞ በምስራቅ ሐረርጌ እንደ እርጎ የሚሳብ አየር ባለበት ምድር ላይ ባረፈችው ታሪካዊቷ ቁልቢ ገብርኤልን ያስጎበኘናል…

(ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)

ታሪካዊው ቁልቢ ገብርኤል፤ ወደ ምስራቅ ተጉዘናል፡፡ ከፈንታሌ እስከ አሰቦት ሙቀት ያስጨነቀን ጎዳና እዚህ ሲደርስ ድራሹ ጠፍቷል፡፡ ደጋማዋ የሐረርጌ ምድር ላይ ነን፤ ከአዲስ አበባ 461 ኪሎ ሜትር ተጉዘን መጥተናል፡፡

ምስራቅ ሐረርጌ እንደ እርጎ የሚሳብ አየር ባለበት ምድር ላይ ባረፈችው ታሪካዊቷ ቁልቢ ነን፡፡ ቁልቢ ገናና ነው፡፡ በአራቱ መዓዘን ያለው የክርስትና አማኝ ወይ ተሳልሞታል፤ ወይ በስሙ ይምላል፤ ወይ የቤተሰብ አባሉን ያክል ስሙ እየተነሳ ሲጠራ አድጓል፡፡ የቅዱስ ገብርኤል በዓል በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው፡፡

በመንፈሳዊ ቱሪዝም በኩልም ብዙዎች ከሀገር ሀገር ለመሳለም የሚንቀሳቀሱበት በዓል በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ይከብራል፡፡ ወደ ደራ ወንቅሸት ገብርኤል፣ ወደ መንዝ ዘብር ገብርኤል፣ ወደ ሐዋሳ ገብርኤል፣ ወደ ጅማ ብቻ ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚጓዘው ተጓዥ ቁጥር የለውም፡፡ ቁልቢ ከእነዚህ አንዱና ቀደምቱ ነው፡፡

ስለ ቁልቢ ታሪክ ከጀመርን ሩቅ ይወስደናል፤ ምናልባትም እስከ አብረሐ ወአጽበሐ አልያም እስከ ዩዲት ዘመነ ስደት፤ እኛ ቁልቢን ከትናንትና ጀምረን እንቃኘዋለን፡፡ ከሚያምር ኪነ ህንጻው ደጃፍ ሆነን ታሪኩን ማውጠንጠን ቀጥለናል፡፡ ይህ ቦታ ቀድሞ ጠፍ ነበር፤ እንደውም በውበቱና በአየሩ መልካምነት ተማርከው አሁን እኔ በቆምኩበት ቦታ ላይ ራስ መኮንን ቤት ሰርተውበት ነበር፡፡

ቁልቢ የእኛ ዘመን ኪነ ህንጻ ቢሆንም ልቅም ተደርጎ ነው የተሰራው፡፡ አሁን የቆምኩበት ቦታ ለመቆም ምናልባትም ከታህሳስ 18 እስከ 20 አልያም ከሐምሌ 18 እስከ 20 ባሉት ቀናት ለመጣ አይሳካለትም፡፡ ቁልቢ በሀገራችን ግዙፉ የመንፈሳዊ ተጓዦች መዳረሻ ነው፡፡ ስዕለት ሰሚ ነው የሚባለው ታቦት ቀድሞ ቡልጋ ይኖር ነበር፤ ጠባቂው አባ ዱባለ ይባሉ ነበር፡፡

ራስ መኮንን ቡልጋ የነበረውን ታቦት አስመጡት፤ ሸንኮራ ድረስ ወርደው ነበር የተቀበሉት፤ ታቦቱ በወርሃ የካቲት 1884 ዓ.ም. ቁልቢ ገባ፤ ውብና ዋናው ህንጻ ታህሳስ 1888 ዓ.ም. ተመረቀ፤ በኢጣሊያ ወረራ በቦንብ ተደበደበ፤ አሁን የቆመው ድንቅ ቤተ ክርስቲያን በአጼ ሐይለ ስላሴ በ1933 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ የተሰራ ነው፡፡

ከዚያም ቁልቢ ከዳር ዳር ዝናው ናኘ፤ ቁልቢ የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር እሴት ማሳያም ነው፡፡ ቁልቢን የጠበቀው ክርስቲያኑ ብቻ አይደለም፡፡ ቁልቢን ያላስደፈረው በዙሪያው የከበበው ሙስሊሙ ህዝብ ነን፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በየአውቶቢሱ ተጭኖ ሀረርጌ ሲከትም ከጭሮ እስከ ድሬደዋ፤ ከላንጌ እስከ ሐረር ምዕመኑን የሚያስተናግደውና ከዓመት ዓመት ወገኑን በስስት የሚጠብቀው ሙስሊሙ ነው፡፡ ቁልቢ እንዲህ ነው፡፡

ሐይማኖት ለምኔ ያለው ኮሚኒስቱ መንግስት እንኳን ጭምር የቁልቢ የስዕለት ኮሚቴ አባል ሆኖ ሰርቷል፡፡ ከድሬደዋ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቁልቢ ኢትዮጵያውያን ተግባቢና ፍቅር ናቸው ያሏቸውን የድሬደዋና ሐረር ነዋሪዎች እንዲተዋወቁ እድል የፈጠረ ነው፡፡ ዛሬ ስለ ምስራቅ ሀገር ሰዎች የዋህነት የሚያወራው የዳር ሀገር ሰው ሁሉ የት አየህ ብትሉት ለቁልቢ ስሄድ ይላችኋል፡፡ (በድጋሜ የቀረበ)

 

Continue Reading
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top