Connect with us

የጠ/ሚኒስትሩን  ንግግር መተቸቴን አስመልክቶ የደረሱኝ መልዕክቶች!!

የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር መተቸቴን አስመልክቶ የደረሱኝ መልዕክቶች!!
ፋሲል የኔዓለም

ነፃ ሃሳብ

የጠ/ሚኒስትሩን  ንግግር መተቸቴን አስመልክቶ የደረሱኝ መልዕክቶች!!

የጠ/ሚኒስትሩን  ንግግር መተቸቴን አስመልክቶ የደረሱኝ መልዕክቶች!!

(ፋሲል የኔዓለም)

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋዜጠኞችን በማስመልከት የተናገሩትን ንግግር ተቃውሜ ለሰጠሁት አስተያየት ብዙ የተቃውሞ አስተያየቶች መሰጠታቸውን ከመሸ፣ ጀርባዬ ሶፋ ሲነካ፣ ከተላኩልኝ መልዕክቶች አነበብኩ። የጠ/ሚኒስትሩ መግለጫ አብዛኛውን ህዝብ እንዳረጋጋው ከአስተያየቶቹ መረዳት ችያለሁ።

ብዙዎቹ  መንግስት ለህዝብ አስቀድሞ መረጃ አለመስጠቱ ለጥንቃቄ ሲል ያደረገው በመሆኑ ሊተች አይገባም ብለውኛል። አንዳንዶች ከመግለጫው በፊት “መንግስት ለምን መግለጫ አይሰጥም? እያሉ ሲጠይቁኝ የነበሩ ናቸው አሁን ሲረጋጉ፣ “መንግስት ፈጣን መግለጫ አለመስጠቱ ትክክል ነው” ብለው የሚሞግቱኝ። ቢሆንም ችግር የለውም። ግን ክርክሩ ለትምህርት እንዲሆነን ነገሩን በሌላ አቅጣጫ ማየቱም ተገቢ ይሆናል።

በመጀመሪያ፣ መንግስት ወታደራዊ ሚስጢሮችን ለህዝብ ወይም ለማይመለከታቸው ሰዎች መግለጽ የለበትም በሚለው እስማማለሁ። ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦች ሲኖሩ፣ መንግስት እራሱ እንኳን ባያደርገው፣ በሚቀርባቸው ሰዎች አማካኝነት ውይይት እንዲደረግበትና ህዝብ አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ማድረግ ይቻል ነበር። 

ለምሳሌ” ከትግራይ ክልል ለቆ መውጣት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?” የሚል ክርክር ትንሽ ቀደም ብሎ በደጋፊዎቹ በኩል ማዘጋጀት ይችል ነበር።

ከትግራይ የመውጣትን አስፈላጊነት አጉልተው ማሳየት የሚችሉ ተናጋሪዎችን አዘጋጅቶ እንዲከራከሩ ማድረግ ወይም አንዱ ባለስልጣን “እስከመቼ ነው እንዲህ እየሆንን የምንቀጥለው” ብሎ በገደምዳሜ እንዲናገር በማድረግ ወይም የጦርነቱን ዋጋ አጉልቶ በማሳየት ህዝብን ማዘጋጀት ይቻል ነበር። ህዝቡ ችግሩን  አስቀድሞ ስለሚረዳው፣ ውሳኔው ድንገተኛ አይሆንበትም። እንዲያውም ውጡ የሚለው ጥያቄ ከራሱም ሊመጣ ይችላል።

ብቻ  እንዲህ አይነት መረጃን የማሽሎኪያና ህዝብን የማዘጋጃ ብዙ መንገዶች አሉ። ከቦታ አንጻር ብዙ ማለት አልችልም።  ግን  በህዝብ ግንኙነት እና የፕሮፓጋንዳ ላይ  የተጻፉ መጽሃፎች ስላሉ ምናልባት እነሱን ማንበቡ ይጠቅም ይሆናል።

ሁለተኛ። የአንድ ውሳኔ ጥቅሙና ጉዳቱ በደንብ የሚታወቀው ውሳኔው መተግበር ከጀመረ በኋላ ነው። እንደታየውም ህዝቡ በውሳኔው ግራ ተጋብቶ ነበር። የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው፣ በንዴት ታመው የተኙ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን እንዳሉም ሰምቻለሁ። የተደናገጠ ፣ የተናደደና የተረበሸ ህዝብ ምን ሊፈጥር ይችላል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው።

ህወሃቶችም ህዝቡ ይበልጥ እንዲደናገር ያካሄዱት የስነ ልቦና ጦርነት ቀላል አልነበረም። መቼም አስቀድመን በመረጃ ያላነቃውን ህዝብ፣ ለምን የስነ ልቦና ጦርነቱ ሰለባ ሆንክ ልንለው አንችልም። ደግነቱ ይህ ነው የሚባል ጉዳት በአገር ላይ አልተፈጠረም። ብዙም ጉዳት ስላልደረሰ ግን አካሄዱ ትክክል ነበር ማለት አይቻልም። የከፋ ጉዳት ቢደርስ ኖሮስ ብለን እናስብ ።

ሶስተኛ፣  ሚስጢር መጠበቅ ለድልም ለሽንፈትም እንደሚዳርግ አምናለሁ። ታዋቂው የህንድ የጦርና የዲፕሎማሲ ሊቅ የነበረው ካውትሊያ “ሚስጢር መጠበቅ የማይችል መሪ ( መንግስት) በውቅያኖስ መሃል እንደተሰበረ ጀልባ ይጠፋል” ይላል። ( The affairs of one, who could not maintain secrecy, . . .undoubtedly perish, like a broken boat in the ocean።)

ችግሩ የሚመጣው ሚስጢሩን ከማን ነው የምትደብቀው የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ላይ  ነው። መንግስት ውሳኔውን ለአሜሪካ ኢምባሲ አሳወቀ።  ኢምባሲውም መረጃውን ለወያኔ አሻገረላቸውና እነሱም ለስነ ልቦና ጦርነት በሚያመቻቸው መልኩ ተጠቀሙበት።

ይህን የምለው መረጃ ስላለኝ ነው። እዚህ ላይ መግለጹ አስፈላጊ ስላልሆነ እዘለዋለሁ።

ወያኔዎች ዞሮ ዞሮ መረጃው ነበራቸው፤ በሚወጣው ሰራዊት ላይ ጥቃት የመሰንዘር አቅም ስላልነበራቸው ግን ጉዳት አላደረሱም።  ለማንኛውም “እያንዳንዱ አምባሳደር  የዲፕሎማቲክ ከለላ የተሰጠው ሰላይ ነው” የሚለውን የካውትሊያን ምክር አንርሳ።

  ረጅም ጽሁፍ ማንበብ ለማትወዱ ሰዎች ስል እዚህ ላይ አቆማለሁ።  ይህ ለክርክር ይሆን ዘንድ ተጻፈ።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top