Connect with us

 “— አንገቴ ይቀላል እንጂ—” 

"--- አንገቴ ይቀላል እንጂ---"
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

 “— አንገቴ ይቀላል እንጂ—” 

 “— አንገቴ ይቀላል እንጂ—” 

(ዶ/ር መሠረት ጀማነህ)

ቀድሞውንም  ቢሆን ኢትዮጵያ ያለመስዋትነት አልተፈጠረችም። እናም ውድ ውድ የሆነ  ዋጋ ተከፍሎባታል። የታላቁ የሀበሻው መሪ የአፄ ቴዎድሮስ ፈተናም ከውጭም ከውስጥም እንድሁ እንደዛሬው  ነበር። ” በአገሬ ከመጡ አንገቴ ይቀላ”  እሳቤ የመይሳው ካሳ ፍልስፍና ነው። ይህ እሳቤ በቴዎድሮስ ትውልድ ሁሉ እየተደገመ የሚሔድ ሆኗል ። 

ካሳ ይህንን  እሳቤ በንደፈ-ሀሳብ ብቻ ሳይሆን  በተግባር ፈፀመው ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መኖር መሠረት ጥለው  አለፉ። ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ መሪዎች ብዙ ጊዜ ግራይጋባሉ። እንግሊዞች ካሳን ቢፈሩትም  ቅሉ ኃያል ስለሆኑ ብቻ ማርከው ወይም ገድለው አገሩን  ለመግዛት ነበር ያሰቡት። ግን ይህን በቀላሉ ሊያሳኩት አልቻሉም። ” ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፣ ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣ ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው?” ተባለ። 

ጣሊያን ግን በደንብ የተሳካ ቅኝ ግዛት ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች። የመጀመሪያው ሙከራም ተደረገ።    መሪዎቹም  እነዚህ አበሾች  አይናቁምና በደንብ መታጠቅ አለብን በማለት  ኃይላቸውን ያለልክ አዘምነው መጡ። ለአፍሪካ ይህን ያህል ዝግጅት? እያሉ ያፌዙም ነበር። በል ይህን ትቢተኛ ንጉስ የፊጥኝ አስረህ  ላክልኝና አገሩን የጣሊያን ግዛት አድርግ ብለው ለጦራቸው አዘዙ ያገሪቱ መሪ። ምኒልክም  ለህዝባቸው” ክፉ ጠላት መጥቶብኛልና ወረኢሉ እንገናኝ” ብለው ቀደሙና ጦርነቱ ተጀመረ። በእቴጌ ጣይቱ ስልት የጣሊያን ጦር መቀሌ  አካባቢ  ውሀ  እንዲጠማው አድርገው ጥይት አጠጡትና ምሽጉን ሰብረው ድል አደረጉት። 

የጣሊያን ጦር የመጨረሻውን አይደፈሬ የአዲግራት   ዋንኛ ምሽጉን ተማምኖ ለድል ቋመጠ። ነገር ግን ምኒልክ ሌላ የጦር ስልት ቀየሱ።  ጣሊያኖቹን በቀኝ በኩል በሩቅ እያዩአቸው በግራ በኩል አልፈው አድዋ ጠበቋቸው።ጣሊያኖች በንዴት ከምሽግ ወጥተው  እየገሰገሱ  አድዋ ደረሱና ፍፃሜያቸውን   አድዋ  ላይ አገኙ። አናም  የጣሊያኑ መሪ በሮም ሽንፈቱን ሲሰማ መርዝ እንደጠጣ ሰው በንደት ተቃጠለ። እናም እዚህም    የአንገቴ ይቀላን  እሳቤ ምኒልክ   በአሸናፊነት  ፈፀሙትና የጥቁር ህዝቦች ፀረ- ኮሎኒያሊዝም ድል አድራጊነት ተረጋገጠ። ከ40 አመት በኃላም ጣሊያን ጦሩን በማዘመን እንደገና  ሞከረና በዚሁ የሀበሻ የአርበኝነት ትግል ኃያልነት ሳይሳካ ቀረ።

ዛሬም አሜሪካኖቹ  ያሁኑም  የኢትዮጵያ መሪ አላማረንም አሉ። እናም ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም በሚል ብሒል በታኙ ወያኔ ሳይጠፉ ኢትዮጵያን እናጥፋ ብለው በመተባበር  ሊበትኑን አስበው  ፈተኑን። በዚህ የተቀናጀ ጦርነት በአማራና በአፋር አያሌ  የኢትዮጵያዊያንን ደም  በግፍ አፈሰሱ፤ ሀብትም አወደመ። በዚህ ጊዜ ነው  ያ “የአንገቴ ይቀላ ኢትዮጽያዊ ፍልስፍና ፈንድቶ  የሳልሳዊ ምኒልክን/አብቹን/ ጤና የነሳው። ” ብዙ ነገር ልታገስ እችል ይሆናል፤ ባገሬ ከመጡ ግን አንገቴ ይቀላል እንጅ አይደረግም ” አሉ ጠ/ሚኒስትሩ   ልክ እንዳባቶቻቸው። 

የአንገቴ ይቀላ ፍልሰፍና የጠላትን ምኞት የሚያመክን  ኃያል ኢትዮጵያዊ ውሳኔ  ነው። ውጤቱም  በከፍተኛ መስዋአትነትም ቢሆን  አገርን ማዳንና ለትውልድ ማስተላለፍ  ነው። እናም ይኸው  ነው አሁን እየሆነ ያለው። ፧

ምዕራባዊያኑ ስለኛ ተነበዩ። አዲስ አበባ ሰሞኑን ቀውጢ ትሆናለች፣  አገሪቱም ትፈርሳለች፣ ጠ/ሚኒስትሩም ወደ ውጭ ሊሸሹ ነውና ዜጎቻችን ሆይ  ቶሎ ውጡ ብለው አስጠነቀቁ። እኛ ደግሞ እንዲህ  አልናቸው። ሸሹም እንዳይሉ  ውጭ አገር አጧቸው፣ አሉም እንዳይሉ በዙፋኑ አጧቸው፣   ጆባይድን ምን አሉ ጦርሜዳ ሲያዩዋቸው?

እነሱ ከታሪክ አይማሩም እንጂ የአበሻ መሪዎች  የተባሉትን ሳይሆን ራሳቸው  ያሉትን ነው የሚፈፅሙት። እናም ጠ/ሚኒስትሩ ጦር  ግንባር እንገናኝ አሉና  ጦር ግንባር  ተገኙ። በቃላቸው መሠረት   ሰውዬውን   ጦር ሜዳ መጠበቅ እንጅ ባህር ማዶ   መጠበቅ ምን ይሉታል? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ማለት ይኸ ነው። እናም ታሪክን ስንገልጥ ቴዎድሮስም፣ ዮሐንስም፣ ምኒልክም፣ መንግስቱም ከቤተ-መንግስታቸው  ወጣ ብለው     ጦር ሜዳ ይውላሉ፣ ይመራሉ፣ ያዋጋሉ ፣ ድል  ያደርጋሉ።ይህ ነበር የመሪዎቻችን ታሪክ። 

ዶ/ር አብይም ይህንኑ አደረጉ፤ በቃ ይኸው ነው።  አዎ! ለሀገሬ  እሰየፋለሁ! መርሆ የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር የኢትዮጵያ ህዝብና  መሪዎቹ ፍልስፍና ነውና ቀቢጠ-ተስፈኞች ይህንን መገንዘብ ነው ያለባቸው። ዶ/ር አብይ ግንባር መገኘት ብቻ ሳይሆን የውጊያውን ባህሪም  በመሠረቱ ቀየሩት።  ባለፈው ፅሁፌ የጠየቅሁት ጥያቄ  አሁን መልሰውልኛልና አመሰግናለሁ። ህብረ-ብሔራዊ ዘመቻው በከፍተኛ የማጥቃትና የመልሶ መቆጣጠር ምዕራፍ ላይ ይገኛል። 

ጠ/ሚኒስትሩ  አትጠራጠሩ እናሸንፋለን ብለዋል። ነገ ጦር ግንባር ነኝ  ብለው በቃላቸው መሠረት  ጦር ግንባር  ከተገኙ  እናሸንፋለን ያሉትን  ማመን  አይከብድም።  አዎ! ቃል ሲሻር እንደሚያሳዝን  ቃል ሲከበር  ያኮራልና ማመስገን አይበዛም።

 ዛሬ ስለመፈራረሳችን  ፅፈው ያልበቃቸው የምዕራቡ ሚድያዎች በቅርብ ጊዜ ጦርነቱን በድል  ቋጭተን በዚሁ ግለት ወደ ልማት በመሸጋገር ሰላምና ብልፅግናን እናረጋግጣለን። እነዚያ ዋሾ የምዕራቡ ሚድያዎች ታዲያ  ሳይወዱ  በግድ ስለ ከፍታችን ሲፅፉም  እናያለን። ምዕራባዊያኑ  በኢትዮጵያ ላይ   የከፈቱት የጣልቃገብነት ዘመቻም  ኢትዮጵያ አሁን በለኮሰችው የኢትዮጵኒዝምና ፓን አፍሪካኒዝም  የዘመኑ ዳግማዊ አድዋ  የነፃነት የትግል ምዕራፉን  የመምራት  ሌላ ኃላፊነት ውስጥ ገብታለችና ይህንኑ ፀረ- የእጅ አዙር ቅኝግዛት ትግል በአፍሪካ ማቀጣጠልና  መምራት አለባት።

ህብረ-ብሔራዊ ዘመቻ ለአንድነት ግብ ይሳካል!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top