መቅደላ በሚያዚያ፤ አምባ ላይ የወደቀው የጀግና ደም ፍሬ አፍርቶ እልፍ ሆኖ አድዋ የበቀለበት፡፡
******
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የሚያዚያን የታሪክ ኩነቶች እየተረከልን ነው፡፡ በዚህ ወር ከሆኑ ጉልክ ክስተቶች አንዱ መቅደላ ነው፡፡ መቅደላ አምባ ጀግና ሞቶ ፍሬው እልፍ ሆኖ አድዋ የበቀለበት ይለናል በተከታዩ ትረካው፡፡)
ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ
መቅደላ አምባ ብቻ አልነበረም፡፡ የምኞት የከፍታ ነጥብም ጭምር እንጂ፡፡ እዚያ ሰው ተሰርቷል፡፡ አድዋን ድል ያደረገ ንጉሥ ከዓለም የተዋወቀበትና ዓለምን ያደመጠበት ነው፡፡ እዚያ ስህተት ታርሟል፡፡ በዝኆን ተጭኖ የመጣ ጥበብ ጦርነትን እንደምን ድል ለማድረግ እንዳገዘ ያወቅንበት፡፡
መቅደላ የምርምር አምባ ነው፡፡ ሀገር በጥበብ ትሰራ ዘንድ ጥበብ የተወጠነበት፡፡ የመቅደላ ታሪካዊ አምባ በደቡብ ወሎ ዞን ከደሴ ከተማ 170 ኪሎ ሜትር ገደማ ይገኛል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ ማርክሃም ስለ መቅደላ ሲጽፍ "በዓለም ካሉ ቦታዎች ሁሉ ጤናማ አየር ያለበት ሥፍራ ነው" እንዳለው ይነግረናል፡፡ ይሄንን ለመረዳት መቅደላ መድረስን አይሻም፡፡ ገና ወደ መቅደላ የተጠጋ ወደ እረፍት ምድር እንደደረሰ ይሰማዋል፡፡ ሌላ አየር ይስባል፡፡ የማይጠገብ፡፡ ሌላ ምድር ይመለከታል ተአምር የሆነ የመሬት አቀማመጥ፡፡ ሄነሪ ሞርተን ክብ የመሰለ፣ ዙሪያውን በሸለቆና እስከ አስር ማይሎች ርቀት ድረስ በሚሸሹ ተራሮች የተከበበ ቦታ የሚለው፡፡ ደግሞ ሌላ ታሪክ ይሰማል፤ ከታላቅ ኢትዮጵያዊ ጥቁር ንጉሥ ጀግንነት ጋር የተቆራኘ፡፡.
በ1859 ወርሃ ነሐሴ ንግስቱን 12 ሺህ ተዋጊ ወታደር፣ 20 በቅሎና ጋማ ከብት፣ 280 መርከቦችንና 44 ዝኆኖችን የጠየቀው ናፒር ከመሪው መልካም ፍቃድን አገኘ፡፡ ባዶ እግራቸውን በተራሮቻቸው ላይ ሆነው ለሚገጥሙት የናፒር ነጭ ወታደሮች ሁለት ሁለት ቦት ጫማ ተሰጥቷቸው ተጫምተው ሊገጥሙ አቢሲኒያ ደረሱ፡፡
ባለ ብረት ቆብ ናቸው፡፡ ባለ ቀበቶ፣ እጃቸው ባለ ሹራብ፣ ህንዳውያኑ የናፒር ወታደሮች ራሱ በወር 5833 ሩፒ ደመወዝተኛ ናቸው፡፡ ናፒር ወደ መቅደላ ሲመጣ ከያዛቸው 13 ሺህ ወታደሮች አራት ሺህዎቹ አውሮጳውያን ናቸው፡፡ ዘጠኝ ሺህው ደግሞ ህንዳውያን፣ ይህ ጦር 19 ሺህ አሽከር አለው፡፡ በአጠቃላይ 32 ሺህ ሠራዊት መቅደላ ሆይ ወዴት ነሽ እያለ ተመመ፡፡ መድፍ የተሸከሙት ዝኆኖች የኢትዮጵያ ተራሮች አልበገሯቸውም፡፡ 55 ሺህ እንስሳት ድምጻቸው ብቻ እንደ ሠራዊት የሚያስገመግም ነበር፡፡ ያኔ ለመሳሪያ ኪራይ ግማሽ ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ተደርጓል፡፡ መድፉ ከያለበት በኪራይ ተሰብስቧል፡፡
ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ እንዲህ ያለ ሠራዊት ከእሳቸው ጋር ሊገጥም መምጣቱን የሰሙት በወርሃ ታህሳስ መጀመሪያ በ1867 ነበር፡፡ በዚህ ሁለት ልብ በሚያደርግ የጦርነት ዋዜማ የሠለጠነና ሥነ-ሥርዓት ያለውን አውሮጳዊ ጦር ለማየት መጓጓታቸውን ለኣላን ሙርሄድ ነገሩት፡፡ እሱም ጻፈው፡፡
የካቲት አዲግራት የደረሰው ናፒየር መጋቢት አሸንጌን ረገጠ፡፡ መጋቢት መጨረሻ ደግሞ ዥጣ ወንዝ ዳርቻ ነበር፡፡ ከመቅደላ አስር ማይል ርቆ፣ በበሽሎ ሸለቆ ውስጥ፤ ከሦስት ጠፍጣፋ አናት ካላቸው ከፍታማ አምባዎች ጋር ተፋጧል፡፡ ነገ ታላቁ ነገር የሆነበት ቀን ነው፡፡ በቀኑ እንዘክረዋለን፡፡