Connect with us

የሚያዚያ የታሪክ ኩነቶች-እስከ መቅደላ መስዋዕትነት

የሚያዚያ የታሪክ ኩነቶች-እስከ መቅደላ መስዋዕትነት
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

የሚያዚያ የታሪክ ኩነቶች-እስከ መቅደላ መስዋዕትነት

የሚያዚያ የታሪክ ኩነቶች-እስከ መቅደላ መስዋዕትነት

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የወርሃ ሚያዚያ ኩነቶችን ከታሪካችን ትዝታዎች እየጨለፈ እስከ መቅደላ ጦርነትና የዳግማዊ ቴዎድሮስ መስዋዕትነት ድረስ እንዲህ ይተርክልናል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ በድሬ ቲዩብ)

ሚያዚያም ኾነ፡፡ ይኽ ወር በታሪካችን ብዙ ክፉም ደግም ክስተቶች አልፈውበታል፡፡ ዘመንን ተከትለን በየዘመኑ ሳይሆን ከዘመን ኩነት አንዳንዱን እየፈተሽን እስከ መቅደላ ጦርነት እንተርካለን፡፡

ሚያዚያ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ስለተመኟት አንዲት ሀገር ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡባት ወር ናት፡፡ በሚያዚያ ብዙ የታሪክ አውራዎችን አጥተናል፡፡ የዛሬ 460 ዓመት ሚያዚያ በሆነ በአስራ አንደኛው ቀን እጨጌ እንባቆም ዘደብረ ሊባኖስ አረፉ፡፡ የመናዊው አረብ፡፡ በርካታ መጻሕፍትን ወደ ግዕዝ የተረጎሙት እጨጌ እምባቆም የአንቀጸ አሚን ደራሲ ናቸው፡፡

ሚያዚያ በሆነ በሦስተኛው ቀን 1903 ዓ.ም. ራስ ቢትወደድ ተሰማ አረፉ፡፡ ራስ ቢትወደድ የሸዋ ተወላጅ ናቸው፡፡ በዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የታመኑ ሰው ነበሩ፡፡ ከደጃዝማችነት ተነስተው እስከ ራስ ቢተወደድነት የዘለቁ ሹም፡፡ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው የልጅ ኢያሱ የአልጋ ወራሽት ሞግዚትም በመሆን ይታወቃሉ፡፡

በ1932 ዓ.ም. ሚያዚያ 27 ቀን ዶክተር መላኩ በያን አረፉ፡፡ መላኩ በያን በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ወደ ውጪ ሀገር ተልከው ከተማሩት ወጣቶች አንዱ ናቸው፡፡ የህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው በመመለስ ኢትዮጵያን ያገለገሉት ዶክተር መላኩ በያን የዲፕሎማሲ የአርበኝነትና የጸሐፊነት ሙያ የነበራቸው ስለኢትዮጵያ የሚሟገቱ የነጻነት ታጋይ ናቸው፡፡

ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ሦስተኛ የተባሉት የንግሥና ዘመናቸው ያበቃው ሚያዚያ በገባ በዘጠነኛው ቀን ነው፡፡ በ1787 ዓ.ም. በተመሳሳይ ዘጠኝ አመታትን የነገሡትና ወይዛዝርት ከሚባሉት የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅጥር ነገሥታት አንዱ የሆኑት ዐፄ ጊጋርም እንዲሁ በዚሁ ወር 1818 ንግስናቸው አበቃ፡፡

በእርግጥ ሚያዚያ የልደትም ወር ነው፡፡ በ1868 ሚያዚያ በተቆጠረ በሃያ ሁለተኛው ቀን ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወረኢሉ አብቹ በያን ቅጥር ተወልደዋልና፡፡

አከራካሪው የውጫሌ ውል እንዲሁ በሚያዚያ ወር 25ኛ ቀን በ1881 ዓ.ም. ነበር የተፈረመው፡፡ የአዲስ አበባው ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ በወርሃ ሚያዚያ የተጀመረ የሚያዚያ ወር የታሪክ አካል ነው፡፡ በ1917 ዓ.ም. ሚያዚያ 19 ቀን ደግሞ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከፈተ፡፡ በአመቱ ሚያዚያ አምስት ቤተ ሳይዳ ሆስፒታል ሥራ ጀመረ፡፡ በ1933 ሚያዚያ 23 ቀን ግርማዊነታው ከስደት ተመልሰው ሀገራቸው ዋና ከተማ ገቡ፡፡ 

ሚያዚያ ሌላው የታሪካችን አካል ተብሎ ከኩነት ጋር የሚነሳው በመቅደላ ጦርነት ነው፡፡ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ጦር እጄን አልሰጥም ብለው ራሳቸውን የገደሉበት ይህ ወር አምስተኛው ቀን ነበር፡፡

የመቅደላ ጦርነት አያሌ ታሪኮች የተሰነዱለት ግዙፍ የታሪካችን ክፍል ነው፡፡ ከቋራ እስከ መቅደላ አምባ የዘለቀው የአንድነት የመሰልጠንና የመታፈር ህልም የሞተ መስሎ እልፍ ፍሬ ያፈራበት፤

ምናልባትም አድዋ ድል ያደረግንበት ሩቅ ተላሚነት የተወጠነበት አምባ፡፡ የንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ታላቁ ዩኒቨርሲቲ፣ መቅደላ፡፡

ማስታወሻችን ይቀጥላል፡፡ በቀኑ የመቅደላን ታሪክ እናነሳለን፡፡ ስለ ንጉሣችን የሀገር ክብር ፍቅር ራስን ለሞት የመስጠት ጀግንነት እንተርካለን፡፡

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top