Connect with us

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እየተሰጠ ይገኛል

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እየተሰጠ ይገኛል
ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

ስፖርት

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እየተሰጠ ይገኛል

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እየተሰጠ ይገኛል

ትላንት ሰኞ መጋቢት 20/2013  ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግቢ ውስጥ ድንኳን በመትከል የተደረገውን ህገወጥ ምርጫ በሚመለከት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ በኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኞች ማህበር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫና የፌዴሬሽኑ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር መግለጫ፣

  1. የኦሎምፒክ ኮሚቴም ሆነ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች የሚመሩበትን መመሪያ ካለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት ዋና ዋና የህግ ምሰሶዎችን በመውሰድ በዋናነት በሃገሪቱ መንግስት በተወከለ የስፖርት ኮሚሽን ከሚያወጣው የስፖርት ማህበራት መመሪያ በመነሳት መሆን ሲገባው መንግስት ሆነ ስፖርት ኮሚሽን አያገባውም በሚል ንቀትና ከአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ህግና ደንብ የሚቃረኑ የህግ አንቀፆችን በመጨመር የተፈፀመ ሲሆን በአንድ ሃገር ውስጥ ያሉ የስፖርት ማህበራት ከሃገሪቱ የልማት ስትራቴጂና ፖሊስ በመነሳት ተጨባጭ ሁኔታዎችን በሚቃኝ መንገድ መሆን ሲገባው የፌደራል ስፖርት ምክር ቤት የሰጠውን አቀጣጫ ወደ ጎን በመተው የተከናወነ ምርጫ በመሆኑ ተገቢ አለመሆኑን እንገልፃለን ይንንም የሃገራችን መንግስት ጉዳዩን በማጣራት አስፈላጊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፤
  2. ታህሳስ 25/2013 ዓ.ም. በሃዋሳ በተካሄደው 45ኛ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ጠቅላላ ጉባኤ ስለ ቀጣይ ምርጫ በኦሎምፒክ ኮሚቴው ፕሬዝዳንት ሞሽን ቀርቦ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ሃሰብ በመስጠት ምርጫ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020 በኋላ እንዲሆንና ያለው ስራ አስፈፃሚ እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. ድረስ እንዲቀጥል በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ምርጫ ማካሄዱ ተገቢነትና ህጋዊነት የለውም እንላለን፤
  3. አንድ የስፖርት ማህበር  (የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ) ጉባዔ ማካሄድ የሚችለው በዓመት አንድ ጊዜ ወይም አስቸኳይ ጉዳይ ሲያጋጥም አንድ አስቸኳይ ጉባዔ ማካሄድ ሲኖርበት ተደጋጋሚ ጉባዓዎችን በማካሄድ የአትሌትንና የህዝብን ገንዘብና የስፖርት ትጥቅ በከፍተኛ ደረጃ ለብክነት የዳረገ በመሆኑ በሚመከተው የመንግስት አካል ሊመረመር ይገባዋል እንላለን፤
  4. ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የቅርጫት ኳስ ፕሬዝዳንትነታቸው በጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ያልተከናወነና ያልፀደቀ በመሆኑ ለኦሎምፒክ ኮሚቴ ለፕሬዝዳንትነት በእጩነት ቀርበው ሊመረጡ ስለማይችሉና ህጋዊነት የሌለው በመሆኑ እንደገና በሚመለከተው አካል ሊፈተሸ ይገባዋል፤ 
  5. በህገወጥ ምርጫው ላይ ከተመረጡ ስራ አስፈፃሚዎች መካከል የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት የስፖርት ማህበራት የሚፈቅደውን አገልግሎት ዘመናቸው ስምንት ዓመት ያለፈ በመሆኑ የተመረጡበት አግባብ ህገወጥ በመሆኑ ሊሰረዝ ይገባዋል፤
  6. የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና የአትሌት ብርሃኔ አደሬ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራርነት መግባታቸው ካደረጉት የሃገርን ሰንደቅ ዓላማ ማስከበር አንፃር ተገቢ ቢሆንም ሊወክላቸው የሚገባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር ወይም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ አትሌቶች ማህበር የተወከሉ ባለመሆናቸው ህጋዊ መስመሩን ያልተከተለ ነው፤
  7. አንድ ሃገራዊ የስፖርት ማህበራት ምርጫ መካሄድ ያለበት በግልፅና የሚዲያ አካላት ባሉበት መሆን ሲገባው በድብቅ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ግቢ ውስጥ በተተከለ ድንኳን መካሄዱ ግልፅነት የጎደለውና ከጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዘ ስለሚያስመስለው እና ህጋዊ መሰረት ስለሌለው የሚመለከተው የሃገራችን መንግስትና ስፖርት ኮሚሽን መርምሮት ምርጫው እንዲሰረዝ ለዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደብዳቤ እንዲፅፍ እንጠይቃለን፡፡

በአጠቃላይ አሁን ባለው የኦሎምፒክ ኮሚቴው አሠራርና አደረጃጀት የምናስበውና የምንጠብቀውን የቶኪዮ 2020 ጨዋታ የሚያደብዝዝና የአትሌቶቻችንን ስነ-ልቦና በመጉዳት ውጤት እንዲበላሽ ስለሚያደርግና ያለን ግንኙነት ከአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሚላኩ የተለያዩ ሰርኰላሮችና ፌዴሬሽኑ የሚልካቸው የምዝገባና ሌሎች መሠል ደብዳቤዎች እየደረሱ ባለመሆኑ በገለልተኛ ኮሚቴ የኦሎምፒክ ኮሚቴው እንዲመራና የአገራችን የኦሎምፒክ ወጤት እንዲቀጥል በጋራ አንጠይቃለን፡፡

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቋም መግለጫ በመቀጠል ከኢትዮጵያ አትሌቲክ አትሌቶች ማህበር የተሰጠ የአቋም መግለጫ፣

መጋቢት 21/2013 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ህገ-ወጥ  ምርጫ ላይ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ አትሌቶች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አትሌቶች ማህበር እየተካሄደ ባለው የአትሌቲክስ ስፖርትን የሚጎዳ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ያላትን ስምና ክብር የሚቀንስ ለተተኪ ትውልድ የምንወርሰው መጥፎ ሁኔታ እልባት ካላገኘ እንዚህ ነገሮች ሊያደርሱብን ይችላሉ፡፡ የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኢትዮጵያን ከኦሎምፒክ ውድድር እንዳያግዳት ስጋት አለን፡፡

በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እየተካሄደ ያለውን ህገወጥ አሰራር እንዲቆም እያስገነዘብን ኮሚቴው እያደረገ የሚገኘውን ህገወጥ እና አላግባብ የሆነ አሰራርን በመቃወም በቶኪዮ 2020 ሃገራችንን በአትሌቲክስ የሚወክሉ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ የቀድሞ አትሌቶች የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሌሎች ሀገር አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽን አመራሮች በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጽ/ቤት በግቢ ውስጥ በመግባት ስርዓት ባለው ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች በተገኙበት በኦሎምፒክ ኮሚቴው አየተካሄደ ያለው ህገ-ወጥ አሠራሮችና አካሄዶች በጽኑ በመቃወም ድርጊቱን በአስቸኳይ እንዲቆምና የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡

እንደሚተወቀው በታህሳስ 25/2013 ዓ.ም በሃዋሳ በተደረገ ጉባዔ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ መስከረም ላይ ከቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ማግስት እንዲደረግ ቢወሰንም ቢሾፍቱ ላይ በተጠራ ጠቅላላ ጉባዔ በባህርዳር ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ ምርጫውን ለማከናወን ቢንቀሳቀስም በባህርዳር ለማካሄድ ሲከለከል በሃዋሳ ለማድረግ ሞክረው የነበረውን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባዔ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን እንዳይካሄድ በፀጥታ ኃይሎች ቢታገድም ለሌቱን ከሃዋሳ የተወሰኑ የክልል ኮሚሽነሮችንና የስፖርት ማኀበራት እንዲሁም አሶሴሽኖችን ይዞ በትናትናው ዕለት በኦሎምፒክ ኮሚቴው ቅጥር ግቢ ድንኳን በመጣል በድብቅና ግልጽ ባልሆነ ሕገ-ወጥ ምርጫ አካሂዷል፡፡

ከዚህ ቀደም 13 የስፖርት ሃገር አቀፍ የስፖርት ፌዴሬቨኖችና አሶሴሽኖች ተቋውሟቸውን ለዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት በጽሁፍ ማሳወቃቸው ይታወቃል፡፡

ስለዚህ ማኀበሩ ይህንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቃወም መሆኑን ለህብረተሰቡ እያሳወቀ መንግስትም ጉዳዮን በትኩረት አይቶ አቅጣጫ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡ 

መላው የኦሎምፒክ ተሳታፊ አትሌቶችና አሰልጣኞች እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አትሌቶች ማኀበር

 

Click to comment

More in ስፖርት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top