አልጣሽ ፓርክን ከሰዎች ሰፈራ መታደግ ተቻለ
የዘርፉ ምሁራን የስነ-ምሕዳር ዘብ ጠባቂና በሕብረ-ቀለማት ያሸበረቀ የውበት መድመቂያ ነው ይሉታል አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክን፡፡ ፓርኩ በያዘው ስነ ተፈጥሮ፣ በተፈጥሯዊ አቀማመጡና ባሉበት ውስብስብ ችግሮች ይታወቃል፡፡ አልጣሽ ከናይጀሪያ እንደተነሱ የሚነገርላቸው ፈላታ የተባሉ አርብቶ አደር ጎሳዎች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የኖሩበት ፓርክ ነው፡፡
ፓርኩ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ውስጥ ይገኛል፡፡ ከ1930ቹ ጀምሮ ጥብቅ ደን ሆኖ ቆይቷል፤ በኋላም የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክን ለማቋቋም በወጣ በደንብ ቁጥር 38/1998 ብሔራዊ ፓርክ ሆኖል፡፡ ብሔራዊ ፓርኩ 2 ሺህ 665 ነጥብ 7 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡
97 በመቶው የፓርኩ አካል ሜዳማ ነው፤ በአሥደናቂ ሥነ-ምህዳራዊ የተፈጥሮ ይዘትም የበለጸገ ነው፡፡ አልጣሽ ከ130 በላይ የዕጽዋት እና 10 የተለያዩ የሣር ዝርያዎች መብቀያም ነው፡፡ በአፍሪካ ብቻ የሚገኝና በመጥፋት ላይ ያለውን ባለ ጥቁር ጋማ አንበሳ የያዘም ነው፡፡
ፓርኩ ዝሆንን ጨምሮ 37 አጥቢ፣ 8 አይነት ተሣቢ እንስሳትን፣ 16 የአይጥ ዝርያዎችን፤ ከ200 በላይ የአዕዋፍ እና ከ16 በላይ የአሳ ዝርያዎችን በውሥጡ አቅፎ የያዘ ነው፡፡
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የአካባቢ ሥነ-ምሕዳርን የሚጠብቅ የሕይወት እሥትንፋስ ነው፤ የአየር ንብረት ለውጥን በመቆጣጠር ሀገሪቱ ካሏት ጥብቅ ሥፍራዎችና ፓርኮች ሁሉ የላቀ ድርሻ አለው፡፡ በተለይ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎችን ከሠሃራ በረሃማነት መሥፋፋት የሚከላከል ዋንኛ የስነ-ምህዳር አካል ነው፡፡ በዚህም አረንጓዴ መቀነት (አረንጓዴ ዘብ) የሚል ስያሜ ተሠጥቶታል፡፡ አልጣሽ የበርሃማነት መሥፋፋትን በመከላከል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሀገራት ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡
ብሔራዊ ፓርኩን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ነው፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራም በንብ ማነብ፣ በአሣ ማሥገር፣ በእጣንና ሙጫ ምርት እንዲሁም በቱሪዝም አገልግሎት ዘርፎች ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚያሥችል ሀብት አለው፡፡
አልጣሽ የበርካታ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች የጉብኝት መዳረሻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱና በተጋረጡበት ውሥብሥብ ችግሮች ምክንያት ተገቢውን ጥቅም መሥጠት ተሥኖት ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ አልጣሽ ሌሎች ጥብቅ ሥፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮች በተጎበኙበት ልክ አልተጎበኘም፡፡
ለዚህም የማሥተዋወቅ ውሥንነት መኖር፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት እና የአገልግሎት ዘርፍ አለመሥፋፋት ሊነሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ትኩረት ተሠጥቶት መሠረተ ልማት ባለመሠራቱ ምክንያት በፓርኩ ውስጥ መጎብኘት ያለባቸው የመሥህብ ሥፍራዎች አልተጎበኙም፡፡
ብሔራዊ ፓርኩ ከተጋረጡበት ውሥብሥብ ችግሮች መካከል ከናይጀሪያ አካባቢ እንደመጡ የሚነገርላቸው ‹ፈላታ› የተባሉ ጎሳዎች ሕገወጥ እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ‹ፈላታዎቹ› በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን የሚገመት የቀንድ ከብት፣ ቁጥራቸው በውል የማይታቅ በግና ፍየል ይዘው በፓርኩ ውስጥ እንደሚኖሩም አብመድ ከዚህ በፊት ዘገባ ሠርቶም ነበር፡፡
በሚያደርጉት ሕገወጥ እንቅሥቃሤም ፓርኩ ለከፍተኛ ልቅ ግጦሽ ተጋልጧል፤ በበጋ ወቅትም ለመኖ የሚሆኑ የዛፍ አይነቶችን እየቆረጡ ለከብቶች ይሠጣሉ፡፡ የፍየል ዝርያ የሚባሉትን እንደ ሠሣ፣ ድኩላ፣ ሚዳቆ፣ ከርከሮ እና የመሣሠሉትን የዱር እንስሳት እያደኑም ለምግብነት ሲጠቀሙ ቆይተዋል፤ ለገበያ የሚሆኑትንም ለሽያጭ አውለዋል፡፡ በዚህም የፓርኩ ተፈጥሯዊ ይዞታ አደጋ ላይ ወድቆ ቆይቷል፡፡
የካቲት/2011 ዓ.ም የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የመንግሥት አካላት በፓርኩ ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ የተከናወኑ ተግባራትን እና የተገኘውን ውጤት አብመድ ጠይቋል፡፡
ከፓርኩ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሣየው ብሔራዊ ፓርኩን በመታደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሣደግ እየተሠራ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የቋራ ወረዳ ሰላምና ደኀንነት፣ሚሊሻና ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች እንዲሁም የፓርኩ ሥካውቶች በጋራ ባደረጉት ፍተሻ የ‹ፈላታ› ጎሣዎች እንዳልተገኙ አሥታውቋል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ኤፍሬም ወንዴ እንዳሉት የፈላታዎች እንቅስቃሴ ወቅታዊ ነው፡፡ መሥከረምና ጥቅምት የሚገቡበት አንደኛው ወቅት ነው፡፡
ይሁን እንጅ ባለፉት ሥድሥት ወራት ‹ፈላታዎች› እንዳልተገኙ አመላክዋል፡፡ ይሕ ማለት ግን ቀጣይ ላለመመለሣቸው ዋሥትና አይሆንም ብለዋል፡፡ ሚያዝያ እና ግንቦት ወደ ፓርኩ የሚገቡበት ሌላኛው ወቅት መሆኑን ያነሱት አቶ ኤፍሬም እንዳይመለሱ ጠንካራ የጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት ተሠርቶ የተገኘውን ውጤት ማስቀጠል እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡
ብሔራዊ ፓርኩ የማኅበረሠቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ እየተሠራ መሆኑንም አንሥተዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡ የጽሕፈት ቤት ኀላፊው እንዳሉት በ2012 ዓ.ም የሀገር ውሥጥ ቱሪዝም ተጀምሯል፤ በእጣንና ሙጫ ዘርፍ ወጣቶች ተደራጅተው 340 ኩንታል ለገበያ አቅርበዋል፡፡ በንብ ማነብ የተደራጁ ማኅበራትም አሉ፡፡
በአሳ ምርት የተደራጁ ሠባት ማኅበራትም ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ማኅበራቱ ጥሩ ገቢ እያገኙ ነው፤ የአንድ ማኅበር አባላት ብቻ እስከ 80 ሺህ ብር ተቀማጭ ገንዘብ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
በቂ መሠረተ ልማት ተሟልቶ ፓርኩ ለቱሪዝም ክፍት ሲሆን የአካባቢው ማኅበረሠብ በአጃቢነት፣ በአስጎብኝነት፣ በምግብ አብሳይነት እና በሌሎች የቱሪዝም ዘርፎች አገልግሎት እንዲጠቀም ይሠራል ብለዋል፡፡
መሠረተ ልማት ማሟላት፣ ዘመናዊ ሪዞርትን ጨምሮ የአገልግሎት ሠጪ ተቋማትን ማሥፋፋት ይገባል ብለዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ትኩረት እንዲሠጡት እየተሠራ መሆኑን አንሥተዋል፡፡ ከመንግሥት ጥረት ባለፈ የባለሀብቶች ተሣትፎ እንደሚያሥፈልግም አሥገንዝበዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ፓርኩን ከሕገወጥ ተግባር መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡(አብመድ)