የዕቁብ መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ይፋ ሆነ
በሀገራችን “ሰውን ሰው ያደረገው እቁብ ነው” እስከሚባል ድረስ ከምጣኔ-ሐብታዊና ማህበራዊ ህይወታችን ጋር በጥብቅ የተሳሰረው ዕቁብ ለብዙዎች የስራ መጀመሪያ፣ ጎጆ መቀለሻና ወደ እድገት መወጣጫ ሆኗል፡፡
አሁን ላይ ታድያ ይህ የኢትዮጵያ ባህላዊ የቁጠባ ዘዴ የሆነው እቁብን ለማዘመን ታልሞ በእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ የተሰራው መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ይፋ ሆኗል፡፡ ከሳምንት በፊት በጉግል አፕ ስቶር ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው መተግበሪያው በእስካሁኑ ቆይታው ከ500 ጊዜ በላይ ዳውንሎድ ለመደረግ በቅቷል፡፡
የእቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስን ከአሌክሳንደር ህዝቂያስ ጋር በመሆን የመሰረተችውና አሁን ላይ በዋና ስራ አስፈፃሚነት የምትመራው ዮሃና ኤርሚያስ እንደምትለው መተግበሪያቸው በአካል ዕቁብ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመስሎና የበለጠ ተጠያቂነት፣ የአጠቃቀም ቅለት እንዲሁም እቁቦቹ በሌሎች ሰዎች ይበልጥ እንዲገኙ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡
በባህላዊው አሰራር ላይ የሚከወኑትን ተግባራት መስሎ ከመስራትም ባሻገር የእቁብ መተግበሪያው እንደ ማስታወሻ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ የክፍያ ስርዓቶች እና የመረጃ ጥንቅሮች ያሉ አዳዲስ ገፅታዎችን በመጨመር ለተጠቃሚ ምቹ ሆኖ የመጣ መሆኑን ዮሃና ትገልፃለች፡፡
እቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ መተግበሪያው ይፋ ከተደረገበት ዕለት አንስቶ ባሉት ቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ 30 ሺህ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ አልሟል፡፡ አሁን ላይ ከባንኮችም ሆነ የክፍያ ስርዓቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የፈጠረ ባይሆንም እቁብ ፔይ የተሰኘ ገፅታን በውስጡ አካቷል፡፡ ይህ ገፅታ ታድያ ተጠቃሚዎች ወቅታዊ መዋጮዋቸውን የሚያመላክት የባንክ መረጃቸውን እንዲያቀርቡና ገንዘቡ ስለ መግባቱ የሚያረጋግጥ ከባንክ የተሰጠ ማረጋገጫ በመከተል እቁቡ መጣሉን እንዲያረጋግጡ ያስችላቸዋል፡፡
መተግበሪያው በእቁብተኞቹ መካከል መተማመን እንዲኖር ለማድረግ ያስችሉኛል ያላቸውን ለየት ያሉ ገፅታዎችንም ይዟል፡፡ አንደኛው መንገድ አሁን ላይ በአካል ያሉ እቁቦችን ወደ መተግበሪያው ማስገባት ነው፡፡ በሌላ መልኩ የመተግበሪያ ተጠቃሚዎች በተለያየ ጊዜ የሚያሳዩትን ምግባር በመከታተል ነጥብ መስጠት እና የእቁብ አስተዳዳሪዎችም ይህን ነጥብ እንዲመለከቱ በማድረግ ወደ እቁባቸው ማን መቀላቀል ይችላል አይችልም የሚለውን ለመወሰን የሚረዳ ገጽታንም ይዟል፡፡
መተግበሪያው እቁቡ ስለተጣለባቸው ዙሮች እንዲሁም እቁቡን ሳይጥሉ ያሳለፉ እቁብተኞች ስለመኖራቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚያቀርብ ስለሆነም ተጠቃሚዎቹ የተሻለ ተዓማኒነት ያላቸውን እቁቦች ለይተው እንዲቀላቀሉ ያስችላል ተብሎለታል፡፡
የእቁብ መተግበሪያ በውጭ ሀገራት ከሚገኘው የዲያስቦራ ማህበረሰብን ዘንድ ተደራሽ ለመሆን ብሎም ከባንክ እና የሞባይል ክፍያ አቅራቢዎች ጋራም ቀጥተኛ የክፍያ ትስስርን ለመፍጠር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ታድያ ድርጅቱ ከዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ገቢ የሚያገኘው መተግበሪያውን የሚጠቀሙ እቁብተኞችን ታላሚ አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች እንደሆነ ከዚህ በፊት መተግበሪያውን አስመልክቶ በሰራነው ዘገባ መግለፃችን ይታወሳል፡፡(የኢት. ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት)