አብንን ከኦነግ ሸኔ ጋር ደምሮ ማቅረብ የበሽተኝነት ምልክት ነው !!
( ኃይሌ ተስፋዬ )
አንዳንዴ ስልጣን ላይ ስለወጣህ ብቻ የተነፈስከው ሁሉ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ካሰብክ ይህ ሞኝነት ነው። ቢሆንም እንኳ ጭፍን ጥላቻህን እና የስልጣን ላይ ብልግናህን ስትገልጥ የሚቀራረብ ሐሳብ ይዘህ ቢሆን ይመረጣል።
ትላንት በሰበታ ከተማ በተካሄደ የብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ ላይ የከተማው ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ “በጨለመባቸዉ በአብን፣ በኦነግ ሸኔና በጽንፈኞች ምክንያት ኢትዮጵያ አትፈርስም” ሲሉ የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስል ያልበሰለና ጨለምተኛ ሐሳባቸውን ለህዝብ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ከንቲባዉ አቶ ብርሃኑ በቀለ የድጋፉ ሠልፍ ላይ “የጁንታዉ ተላላኪ በሆኑት በአብንና በኦነግ ሸኔ ምክንያት የምትፈርስ ሀገር አትኖርም” ካሉ በኋላ አብን የአማራን ህዝብ የማይወክል እንደሆነ በድፍረት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከዚህ ከንቲባ ንግግሮች ብዙ ስሕተቶች ገጠው ቢታዩኝም ከዋናዎቹ አንዱ ግን፥ አብንን የጁንታው ተላላኪ ከማለታቸውም አልፎ ከኦነግ ሸኔ ጋር ደምረው ማቅረባቸው ሲሆን፣ ዋና እና የገነገነው ስህተታቸው ደግሞ ከንቲባው የአማራን ህዝብ ወክለው አብን የአማራን ህዝብ እንደማይወክል በደመ ነፍስ መናገራቸው ነው።
እንግዲህ አቶ ብርሃኑ የብልጽግና አባልና አመራር ናቸውና ይህን ለምን ተናገሩ ማለት አመክንዮታዊ ባይሆንም ቅሉ፥ እርሳቸው የብልጽግና ሰው እንደመሆናቸው መጠን ሥራቸውን በዚህ መንገድ እያደበላለቁም ቢሆን ይሥሩ። ነገር ግን ህዝብ አዋቂ ነው። ህዝብ መልካምና ክፉውን፣ ሌባውንና ቸሩን፣ የስልጣን ጥመኞችንና ህዝባዊ ወገንተኞችን ጠንቅቆ ያውቃል። ይሁንና አብንን ከኦነግ ሸኔ ጋር አብሮ ማቅረብ የበሽተኝነት ምልክት ከመሆን በዘለለ ሌላ ሊሆን አይችልም !!
እኔ ግን ለክቡር ከንቲባ የምለው ክቡር ከንቲባ ሆይ ፦ ዛሬ በንጽጽር ያቀረቡት ይህ ንግግርዎ ክቡር የሆነውን ፖሊስ ከሌባ ጋር በደምሳሳው ቀላቅለው እንደመናገር ይቆጠርበዎታል።
ምክንያቱም የፈለገዎትን መስፈርት ቢያስቀምጡ አብንን ነፍሰ በላ ከሆነው ፣ የሰውን ልጅ እንደ እንስሳ አጋድሞ ከሚያርደው፣ ሠውን ያለ ምክንያት በአደባባይ ዘቅዝቆ ከሚሰቅለው ኦነግ ሸኔ ከተባለው አረመኔያዊ ድርጅት ጋር ጨፍልቀው ሊያወግዙ የሚችሉበት የሞራል ልዕልና የለዎትምና ነው።
ይሁንና ስልጣን አስክሮዎት አብን የኢትዮጵያ ጠላት ነው ማለት ከጀመሩ ይህ ሰው ታመዋል ከማለት ውጭ ምንም ልንልዎት አንችልም ። እግዚሃር ጤናዎን ይመልስልዎት ከማለት ውጭ ።
ክቡር ከንቲባ ሆይ ! ደግሜ እላለሁ እግዚሃር ጤናዎን ይመልስልዎት!!