Connect with us

በበይነ-መረብ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራ ተካሄደ

በበይነ-መረብ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራ ተካሄደ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት

ዜና

በበይነ-መረብ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራ ተካሄደ

በበይነ-መረብ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራ ተካሄደ

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት የወጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ባመቻቸው የበይነ-መረብ ውይይት በየአገሩ የሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም የዳያስፖራው ተወካዮች በተገኙበት ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ራይዚንግ ኢትዮጵያ በሚል ርእስ  ተካሂዷል፡፡

የውይይቱ ዓላማ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ሕጐችና አሠራሮች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት ድጋፍ እንዲሁም በተግባር በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርገው ውጤት ያስመዘገቡ ባለሃብቶችን በራሳቸው አንደበት ያለውን እውነታ በመግለጽ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማበረታታት የሚል ነው፡፡

ይህንኑ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ለሊሴ ለተሳታፊዎች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በገለፃቸውም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን፣ መንግስት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው በሚገኙ በግብርና፣ በማእድን፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይሲቲ እና መሰረተ ልማት በርካታ እድሎች እንዳሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ለሌሲ ነሜ ተናግረዋል፡፡

በነዚህ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና አሰራሩን ቀላል ለማድረግ በርካታ የኢኮኖሚና የህግ ማሻሻያዎች እየተካሄዱ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

በተለይም ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮም ያሉ ትላልቅ ተቋማት ላይ በከፊል እና ሙሉ በሙሉ የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ የሚያስችል የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ባለሃብቶችን እያነቃቃ ነው ፡፡ የኮቪድ ወረርሽኝ በመላው አለም አስቸጋሪ ሁኔታን እየፈጠረ ባለበት ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የማእድንና ነዳጅ ሚኒሰቴር ሚንስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመኝ ውቤ እንደተናገሩት የማእድን ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን ገልፀው ፣ አዲስ የማእድን እና የነዳጅ ዘርፍ ፖሊሲ በመዘጋጀቱ ዘርፉ ስርነቀል ለውጥ በማምጣት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በከፍተኛ ደረጃ የሚስብ ነው ብለዋል ፡፡ 

በዘርፉ ኢንቨስት የሚያደርጉ በእውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በማሳተፍ ከዘርፉ የሚገኘውን ከፍተኛ ሃብት ሥራ ላይ ለማዋል በየአገሩ ያሉ አምባሳደሮችና ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመቀጠል በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው ከዩናይትድ ኪንግደም በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ያላቸው በርካታ ታላላቅ ኩባንያዎች በሀገራችን ኢንቨስት ማድረጋቸውን ገልፀው ሌሎችም በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በውጭ ሀገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ት/ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ ትላልቅና ታዋቂ የሆኑ ኩባንያዎች ወደ አገራችን ገብተው በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የማስተዋወቅ ስራ ከኤምባሲዎቻቸው ጎን በመቆም እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዳያስፖራው በስራና በተለያዩ አጋጣሚዎች አቅም ያላቸውን የውጭ ኢንቨስተሮችን በመድረስና በአገራችን ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እድል ለማስተዋወቅ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ የአገራችንን የወጪ ምርቶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገበያ በማስገባት ረገድ የዳያስፖራው ተሳትፎ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ምርቶቻችንን በማስተዋወቅና በዩናይትድ ኪንግደም ገበያ የሚኖራቸው ተፈላጊነት የበለጠ በሚጨምርበት ላይ ተደጋግፈን መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የራይዚንግ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶ/ር በላቸው ተስፋ እንደተናገሩት አገራችን እምቅ ሀብት ያላት መሆኗን ጠቅሰው ዳያስፖራው ይህን ሀብት በባለቤትነት ለሚኖርበት ሀገር ማህበረሰብ እና ባለሃብቶች ማስተዋወቁ ለኢትዮጵያ እድገት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡  በተመሳሳይ በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሳሳተ መልኩ እየቀረበ ያለውን ገፅታችንን ለመቀየር ይህ ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የኖረዋል ብለዋል ፡፡

በመጨረሻም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አባቢ ደምሴ እንደተናገሩት ይህን የኢንቨስትመንት የማስተዋወቂያ መድረክ በቀጣይነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው በውይይቱ ለተሳተፉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም የዳያስፖራ ተወካዮች የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎችን የማስተዋወቅን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበው በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ት/ኢትዮጵያዊያን የፕሮግራሙ አካል ሆነው አገራቸውን በማስተዋወቅና ገጽታዋን በመገንባት ረገድ የጋራ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ሲል  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት በላከልን መግለጫ አስታውቋል፡፡

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top