የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበርን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ታቅዷል
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር በእንጅባራ ከተማ በደምቀት ተከበሯል፣ ከክብረ በዓሉ በኃላ የበዓሉን ክንውንና በቀጣይ ሊሠሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሲፖዚየም ተካሂዷል። በሲምፖዚየሙ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሀገሪቱ የሚገኙ ብዙኀን መገናኛ ድርጀቶች የህዝብ መሆናቸውን ተረድተው ለህዝባዊ በዓላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ማህበሩ በዩኒስኮ እንዲመዘገብ ለሚደረገው ጥረት ማገዝ እንዳለባቸው ተነስቷል።
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ ክብረ በዓል የአባቶችን ጀግንነት፣ የአካባቢውን ባህል፣ታሪክና የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ 81 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ማህበር እንደሆነም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ደስታ ዓለሙ እንደተናገሩት አባቶቻችን ያቆዩቱን ታሪክ ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፣ለዚህም የማህበሩ ታሪክና ተግባር በዘጋቢ ፕሮግራም ተሠርቶ ጥናት ማድርግ ለሚፈልጉ ምሁራን ተሰንዶ መቀመጥ አለበት ብለዋል።
አርቲስት ብርቱካን መለሰ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊ ስትሆን ብሔረሰብ አስተዳደሩ በውስጡ የሚገኙ እምቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ፀጋዎች ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ መሠራት አለበት ብላለች። የፈረሰኞች ማህበሩም ከአባላቱ በሚሰበሰበው ገንዘብ ራሱን ማደራጀትና የብሔረሰብ አስተዳደሩ የባህል አምባሳደር በመሆን በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠር አለበት ነው ያለችው።
ለተሳታፊዎች ስለሀገር በቀል እውቀትና እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ጥናታዊ ጹሑፍ ያቀረቡት አቶ እሱባለው ክንዴ ማህበሩ በጠንካራ አደረጃጀት እየተመራ 81 ዓመታትን አሳልፏል፣ የበለጠ ለማጠናከር ብዙ ወጣቶችን የማህበሩ አባል ማድርግ ይጠበቃል ብለዋል።
የፈረስ ማህበሩን ገጽታ ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ጠንካራና የተሻሻሉ የፈረስ ዝርያዎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም በጥናታቸው አቅርበዋል። የፈረሰኞችን ማህበር ማዘመንና የገቢ ምንጭ ማድርግ የሚቻለው ሁሉም የድርሻውን በትኩረት መስራት ሲችል ነው ብለዋል።
አቶ ሰውነት ሺፈራው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞችን ማህበር ለቱሪዝም ሳቢና ማራኪ ለማድረግ በዓመት አንድጊዜ ብቻ በዓል ማክበር ሳይሆን በተከታታይነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ሲመሰረትም በማህበረሰቡ ይሁንታ የተመሰረተ ነው፤ ማህበሩም ጠንካራ መሰረት የያዘ ነው ብለዋል። በተለይ ወጣቶች ፈረስንና የፈረስ አልባሳትን አቅርበው በመሸጥ፣ የፈረስ ትርዒት በማሳየት፣ ለአስጎብኚዎች ታሪኩን በማስረዳት እና በሌሎችም ዘርፎች የሚሰማሩበት አሠራር ሊፈጠር ይገባል ብለዋል፡፡
ማህበሩ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ጎልማሶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈ በመሆኑ የሀገር እና የውጭ የቱሪስት መስዕብ በቀላሉ መሆን እንደሚችል አስረድተዋል። ለዚህም ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባዋል ብለዋል።
ሲፖዚየሙን የመሩት ክንዴ ብርሃኑ (ዶክተር) የፈረስ ማህበሩ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ልዩ መገለጫ በመሆኑ ትልቅ የባህል ተቋም ሆኖ ሊያገለግል የሚገባ ነው፣ ለብሔረሰብ አስተዳደሩ፣ ለክልል እና ለኢትዮጵያ ሀብት ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዘውዲቱ ወርቁ የባህል እና ቱሪዝም መመሪያው ከፈረስ ማህበሩ ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል። ማህበሩ በአደረጃጀት እንዲመራ፣ እንዲዘምን፣የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችልና የህዝቡ ሁለንተናዊ መገለጫ እንዲሆን መምሪያው በእቅድ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ለሥራው መሳካት ደግሞ የክልልና የፌዴራል ተቋማት እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
ማህበሩ ቋሚ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲኖረውና በዩኒስኮ እንዲመዘገብ ሰነዶችን የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ኃላፊዋ አስርድተዋል።(አብመድ)
—