Connect with us

#ለጥንቃቄ!!

#ለጥንቃቄ!!
የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

ዜና

#ለጥንቃቄ!!

#ለጥንቃቄ!!

የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እናስገባለን በሚል ሰበብ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦች ስላሉ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተከታዩን ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ከ132 ኪ.ቮ በታች ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ ተቋማት እንዲሁም ለመኖሪያ ቤት ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የመስጠትም ሆነ ቆጣሪ የመግጠም ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው፡፡ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡ ሌሎች ማንኛውም ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጠውም ይህ ተቋም ነው፡፡  

ይሁን እንጂ ከተቋሙ ህጋዊ አሰራር ውጭ የተቋሙ ሠራተኛ ሳይሆኑም ጭምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኛ በመምሰል እኩይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እናስገባለን በሚል በህገ-ወጥ መንገድ ከህብረተሰቡ ገንዘብ የሚቀበሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ተቋሙ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል፡፡

ለአብነትም ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የሆነች አንድ ግለሰብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያውቀው ነገር ግን ከተቋሙ ነው የመጣነው ቆጣሪ እናስገባልሻለን ብለው በማታለል ገንዘብ ተቀብለዋት ህጋዊ ያልሆነ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ገጥመውላታል፡፡ 

ግለሰቧ ለእነዚህ ግለሰቦች በሐሰተኛ እሴት ታክስ ደረሰኝ 12 ሺህ ብር የከፈለቻቸው ቢሆንም ድርጊቱ ከተቋሙ እውቅና ውጪ ነበር፡፡ 

በመጨረሻም በተደረገው ማጣራት የተገጠመው ቆጣሪ ህገወጥና ትክክለኛውን የአሰራር ስርዓት ተከትሎ የተፈፀመ አለመሆኑን ተደርሶበታል፡፡ በዚህ እኩይ ተግባር ግለሰቧ ተገቢ ያልሆነ ገንዘብ ከመክፍሏም በተጨማሪ የተገጠመላት ቆጣሪ አገልግሎት እንዳይሰጥ ተደርጓል፡፡ 

ህብረተሰቡ እንደነዚህ አይነት መሰል እኩይ ድርጊቶች ሊያጋጥመው ስለሚችል አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲወስድ ተቋሙ በአንፅንኦት ያሳስባል፡፡ 

ተቋሙ የአዲስ ቆጣሪ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት የራሱ የሆነ የአሰራር ስርዓት የዘረጋ መሆኑ ታውቆ፤ ህብረተሰቡ መሰል ጥያቄም ሆነ ሌሎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ለሚያቀርበው ማንኛውንም ጥያቄ በአቅራቢያ ወደሚገኘው የተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ በማመልከት መገልገል ይችላል፡፡  

ተቋሙ መሰል ህገ-ወጥ ድርጊቶችን እያከናወኑ የሚገኙ ግለሰቦችም ሆነ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች ከህግ አካላትና ከመላው ህብረተሰብ ጋር በመተባባር ተጠያቂ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነም ይገኛል፡፡

ህብረተሰቡ ከመሰል እኩይ ድርጊቶች ራሱን እንዲያርቅና ከተቋሙ ህጋዊ አሰራር ያፈነገጠ ህገወጥ ድርጊት ሲያጋጥመው ግለሰቦቹ በትክክል የተቋሙ ባልደረባ  መሆናቸውን የሚገልፅ መታወቂያ መያዛቸውን፣ ባጅ ማድረጋቸውንና አገልግሎት ለማግኘትም ህጋዊ ቦታ መሆኑን እንዲሁም ለአገልግሎቱ ለሚፈጽመው ክፍያ ህጋዊ የተቋሙ ገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ መውሰዱን ማረጋገጥ እንደሚገባ እና የሚያጠራጥር ሁኔታ ካለም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ወይም በአካባቢው በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ወይም ለህግ አስከባሪ አካላት በጥቆማ ማሳወቅ እንደሚገባ ተቋሙ ያሳስባል፡፡  

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top