“ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የወሰን ግፊት ማካሄዷ አሳዛኝ እና የማይጠበቅ ተግባር ነው”፡- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ
ሱዳን ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅማ የወሰን ግፊት ማካሄዷ እጅግ አሳዛኝ እና የማይጠበቅ ተግባር መሆኑን በተመድ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለፁ።
አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በአሜሪካ ኒውዮርክ፣ ኬኔቲኬት እና ኒውጀርሲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በዌቢናር ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በወሰን ጉዳይ ላይ የነበራቸው የይገባኛል ጥያቄ ሕጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጋራ የወሰን ኮሚሽን አቋቁመው ሲሰሩ እንደነበር አምባሳደሩ አስታውሰዋል።
ይህን የወሰን ጉዳይ ሁለቱን አገሮች በትብብር ለመሥራት ችግር ሆኖባቸው እንደማያውቅም ለተሳታፊዎች ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን ለተከሰተው የፖለቲካ ችግር በሰላማዊ መንገድ እልባት አግኝቶ በሱዳን ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን፣ በሱዳን በኩል ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የወሰን ግፊት ማካሄዱ እጅግ አሳዛኝ እና የማይጠበቅ ተግባር እንደሆነም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት ቅድሚያ መስጠቱን፣ የድንበር ጉዳይ ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል ባቋቋሙዋቸው የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣ የቴክኒክ ኮሚቴዎች እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ወደ ድርድር መድረክ ለመቅረብ ግን የሱዳን መንግስት በሀይል የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት ወይም ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ የግድ መሆኑን አብራርተዋል።
በውይይቱ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን ሕግን የማስከበር እርምጃ እና የተገኘው ውጤት ተነስቷል።
አምባሳደር ታዬ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው ሕግን የማስከበር እርምጃ ከሕዝብ ሉአላዊነት እና ከአገር አንድነት ጋር ከፍተኛ እና ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የአገሪቱ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በትግራይ ክልል የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ህዝቡ ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለስ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ በመሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን መልሶ የመጠገን ስራ እየተከናወነ ሲሆን በሰላም ማስከበሩ ሂደት የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመርዳትም በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፣ በተ.መ.ድ.፣ ከዓለም ማህበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ የማሰባሰብ እና እርዳታውን የማዳረስ ስራ እየተከናወነ መሆኑ አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ያስከተለው ጉዳትና ጉዳቱን ለመቀነስ በመንግስት እና በሚስዮኑ በኩል ስለተከናወነው ተግባርም በውይይቱ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።
ኮቪድ-19 በተመለከተ “ወገን ለወገን” የተሰኘው ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ሀይል ስላከናወናቸው ተግባራት በማመስገን ወረርሽኙ አሁንም የዓለማችን ብሎም የአገራችን ከባድ የጤና፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ችግር ምንጭ እና ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ገልፀዋል።
የኮቪድ-19 ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ በዓለም ዓቀፍ ንቅናቄ መጀመሩ ይህም ወረርሽኙን ለመግታት ትልቅ ተስፋ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኮቪድ-19 ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ በሚሰራው ዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረክ በአስተባባሪነት መመረጣቸውም ተገልጿል።
በአሜሪካ የሚገኙ የኮሚኒቲው አካላት በህግ ማስከበር ሂደቱ ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ለኮቪድ-19 የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል።(EBC)