‹‹በአማራው ላይ በተቀነባበረ መንገድ የሚፈጸመው ግድያ መቆም አለበት›› የታሪክ መምህሩ ታዬ ቦጋለ
በአማራ ላይ ግድያ፣ ማፈናቀል እና ሌሎች ግፎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ የአማራ ሐጥያቱ፣ ሀገሬን ማለቱ፣ አማራነቱና ኢትዮጵያዊነቱ ነው፡፡ ከምንም በላይ ሀገር ይላል ግን በግፍ ይገዳላል፡፡ ስለ አማራ ሞት የመተከል ምድር፣ ጥሻው፣ ዱሩና ገደሉ ምስክር ነው፡፡ በየቀኑ የግፍ እንባ ሲወርድ ይታያልና፡፡
በባሕርዳር ‹‹የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትና ዲሞክራሲ ለሕዝቦች መተሳሰብና አብሮነት›› በሚል መሪ ሀሳብ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ የምክክር መድረክ የተገኙት የታሪክ መምህሩ ታየ ቦጋለ በመተከል ጉዳይ ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ዜጎች በማንነታቸው ብቻ በጅምላ እየተጨፈጨፉ ነው ብለዋል፡፡ አንዳንዶች የመተከልን ጉዳይ ጥቃት ይሉታል ያሉት መምህር ታየ ቦጋለ ሆድ ውስጥ ያለ ሕጻን በምንድን ነው ጥቃት የሚፈፀምበት? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ጥቃት የሚባለው ተመጣጣኝ የሆነ ቡድን ሲሆን ነው መሳሪያ ያልያዙ ንጹሓን በማንነታቸው ብቻ እየተገደሉ ነው ብለዋል፡፡
በመተከል ለሚደርሰው ሞትና መፈናቀል የመጀመሪያው ተጠያቂ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥትና በየደረጃው ያለው የሥራ ኃላፊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከላይ ያለው የሥራ ኃላፊ ቁርጠኛ ከሆነ ታች ያለውም በዛው ልክ ሥራውን ይከውናል ነው ያሉት፡፡ የመተከሉ ማንነትን መሰረት ያደረገ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ከመንግሥት እውቅና ውጭ ነው ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግሥቱም ተጠያቂ ነው ያሉት የታሪክ መምህሩ ሕወሃትን የሚያክል 80 በመቶ መሳሪያ በእጄ አስገብቻለሁ ያለ፣ ያስታጠቀና ያደራጀን ቡድን በቀናት ያፍረከረከ የጥፋት ኃይሎችን መደምሰስ አያቅተውም ብለዋል፡፡
ጭፍጨፋው በእቅድ የሚመራ ነውም ብለዋል፡፡ በዚህም በእቅድ የማይመራ ቢሆን ኖሮ በተከታታይነት ሞትን እስክንላመደው ድረስና ሰዎች በጀምላ የሚቀበሩበት ደረጃ አይደረስም ነበር፤ ይሔ ያሳዝናል ነው ያሉት፡፡
በመተከል አማራ በመሆናቸው ብቻ የሚገደሉ ንጹሓን ሲታይ ሀዘኑ ከባድ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ሀገራችን ሀገር እንድትሆን ካስፈለገ የመጀመሪያው ምሁራን ምሁር መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ሰው ነን የሚለው መቅደም አለበት ያሉት ምሁሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ 98 በመቶ የሚሆነው አማኝ ነው፣ በታሪካችን ውስጥ አብሮነት፣ በጋራ መስዋዕትነት የመክፈል፣ የጋብቻና ሌሎችም የእርስ በዕርስ ትስሰሩ ከፍተኛ ነው፣ ይሄን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
ለጥቂቶች ሆድ መሙላት፣ ኑሮ መመቻቸት፣ መደላደልና የዘረፉት እንዳይታወቅባቸው ለማድረግ ሲሉ ግጭቶች እንደሚነሱም ገልፀዋል፡፡ የዘረፉት ባለስልጣናት ሀገር ከተረጋጋች ከስልጣናቸው ላይ አይኖሩም፣ ለተጨማሪ ትርፍ በሰው ደም እየነገዱ ነው፤ ይህ ጉዳይ መቆም አለበትም ብለዋል፡፡
‹‹ማንም ሰው ወደዚህ ምድር ሲመጣ እኔን ጠልቶ ብሔሩን መርጦ የመጣ የለም፣ እኔን ወዶ ከእኔ ተመሳሳይ ብሔር የተወለደ የለም›› ይሄ ብቻ በቂ ነው፣ የመንግሥት የመጀመሪያ ሥራው ሕግና ስርዓትን ማስከበር ነው፤ ይሄን ማድረግ ካልቻለ መንግሥት መሆኑ ያቆማልም ብለዋል፡፡
ወያኔ የጠነሰሳቸው የጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ ያደጉ መሪዎች መውረድ መቻል አለባቸውም ብለዋል፡፡ መንግሥት የመግለጫ ጋጋታ ከማውጣት የዘለለ መሬት ላይ የወረደ ለውጥ ማሳየት አለበት ነው ያሉት፡፡
አማራን እየጎዱ የምትመሰረት ሀገር አስቸጋሪ እንደምትሆንም ተናግረዋል፡፡ “በአማራው ላይ በተቀነባበረ የውስጥና የውጭ ፖለቲካ መሪዎች ጭምር የሚደርሰው ጥቃት መቆም አለበት” ነው ያሉት፡፡ ደም የመጠጡ ሽማግሌዎች መደምሰስ መልካም ሆኖ እያለ በመተከል ገና ወደ ምድር ያልመጡ ሕጻናት ሲገደሉ ያማልም ብለዋል፡፡
ሰዎች ነን፣ እምነት አለን፣ የምኖረው በአንድ ሀገር ውስጥ ነው፣ ለጥቂቶች ፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ጉዳት እንዳይደርስ በምክንያት መንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል፡፡
(ታርቆ ክንዴ ~ አብመድ)