Connect with us

ለወሳኝ ጥያቄዎች ~ የምርጫ ቦርድ ማብራሪያ

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያ ዝርዝርን አስመልክቶ ያቀረበው አቤቱታ ላይ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ዜና

ለወሳኝ ጥያቄዎች ~ የምርጫ ቦርድ ማብራሪያ

ለወሳኝ ጥያቄዎች ~ የምርጫ ቦርድ ማብራሪያ

የምርጫ 2013 የጊዜ ሰሌዳን አስመልክቶ የሚነሱ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው

1, የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳደር የድምፅ መስጫ ቀን ለምን በተመሳሳይ ቀን አልሆነም?

ለአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ መስተዳድሮች ምክር ቤቶች የድምፅ መስጫ ቀን ከአገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ አለመሆኑን ቦርዱ አሳውቋል፡፡ ይህም የሆነው ግንቦት 28 ቀን 2013 የሚካሄደው ምርጫ የፌዴራል መቀመጫ የሚመረጥበት የምርጫ ክልል (constituency) እና የአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተሞች መስተዳደር መቀመጫዎች የሚመረጡት የምርጫ ክልል (constituency) በመለያየቱ ነው፡፡ 

የከተማ መስተዳድሮች/ክልሎች የምርጫ ክልሎቻቸው የሚወስኑት በራሳቸው ሲሆን ቦርዱ የክልል/የከተማ መስተዳድሮች ምርጫን የሚያስፈጽመው ክልሎች/ከተማ መስተዳድሮች በወሰኑት የምርጫ ክልል መሰረት ነው። ለምሳሌ በምርጫ 97 የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መቀመጫ የሚመረጥበት የምርጫ ክልል እና ከከተማው ለተወካዮች ምክርቤት ተወካዮች የሚመረጡበት የምርጫ ክልል ተመሳሳይ የነበረ ሲሆን ቆጠራውም በተመሳሳይ የሚቆጠር በመሆኑ ምርጫ አስፈጻሚዎች ውጤት ሲያሳውቁ ለተመሳሳይ የምርጫ ክልል ሪፓርት ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከምርጫ 97 በኋላ በ2000 ዓ.ም በተካሄደው የከተማው መስተዳድር መቀመጫ ምርጫ የከተማ መስተዳድሩ የምርጫ ክልሎቹን በመቀየር ክፍለ ከተሞችን እንደምርጫ ክልል አዋቅሮ ምርጫዎቹም በዚያ መሰረት ሲከናወኑ ቆይተዋል። 

ከዚያ በኋላ የነበሩት ምርጫዎችም የከተማ መስተዳድሩ ምርጫ ከፌደራል ምርጫ ጊዜ በተለየ ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል። የድሬደዋ ከተማ መስተዳድርም ከፌደራል መቀመጫ (2 ብቻ) በተለየ በመስተዳድሩ ስር ያሉትን 47 ቀበሌዎች እንደመስተዳድሩ የምርጫ ክልል ስለሚጠቀምባቸው አንድ ሰው ድምጽ ሲሰጥ ለፌዴራል መቀመጫ ድምጽ የሚሰጥበት እና ለመስተዳድሩ ድምጽ የሚሰጥበት የምርጫ ክልል ይለያያል። ይህም ውጤት ቆጠራን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል። እንደሚታወሰውም የድሬደዋ ከተማ ምርጫም ከፌደራሉ በተለየ ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል። 

ይህ መሆኑ ድምጽ አሰጣጥ እና ቆጠራው በአንድ ቀን ቢደረግ ችግሩ ምንድነው?

  • ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ የሚሰጡበት የምርጫ ክልሎች የተለያዩ በመሆናቸው በድምጽ አሰጣጥ ወቅት መምታታትን ያስከትላል።
  • ምርጫ አስፈጻሚዎች ውጤት ቆጥረው ወደሚመለከተው የምርጫ ክልል የሚልኩ ሲሆን በአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ግን ለሁለት እና ለሶስት ምርጫ ክልሎች ውጤትን አከፋፍለው እንዲልኩ ይገደዳሉ ይህም በውጤቱ ድመራ ላይ መምታታት ሊያመጣ ይችላል፣ የምርጫውን አፈጻጸምም አስቸጋሪ ያደርገዋል።
  • ምርጫ አስፈጻሚዎች ለተለያዩ የምርጫ ክልሎች ውጤትን በታትነው እንዲልኩ የተለየ የቆጠራ እና የውጤት ሪፓርት አደራረግ ስልጠና ማግኘት ይኖርባቸዋል ይህም ተጨማሪ የኦፕሬሽን ጫና ከመሆኑም በላይ ለዚህ የተለየ ህትመቶችን የማዘጋጀት ተጨማሪ ጫና ያስከትላል።

ድምፅ መስጫ ቀን በተለያየ ቀን መሆኑ ምን ጥቅም አለው?

  1. ምርጫ አስፈጻሚዎች ለአንድ ምርጫ ክልል (constituency) ብቻ ደምረው ሪፓርት ያደርጋሉ፣ ይህም የውጤት ስህትት እንዳይፈጠር ያደርጋል።
  2. ድምፅ ሰጪዎች ያለምንም መምታታት ድምፅ መስጠት ይችላሉ።
  3. የምርጫ ታዛቢዎች ጋዜጠኞች እንዲሁም የፓርቲ ወኪሎች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ በመገኘት ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም (የአቅም መበታተን ሳይኖር) የምርጫን ሂደት መከታተል ተአማኒነቱንም ማረጋገጥ ይችላሉ።

ከድጋሚ ድምጽ መስጠት ጋር የተያያዙ ስጋቶች እንዴት ይታያሉ?

አንድ ሰው አንድ ቦታ በመራጭነት ለመመዝገብ በምርጫ ጣቢያው ነዋሪነቱን ተረጋግጦ ሲሆን መስፈርቱን አሟልቶ ለመመዝገቡ ደግሞ የመራጭነት መታወቂያ መያዝ አለበት። በአካባቢው ነዋሪ ያልሆነ መራጭ ተመዝግቧል የሚል ጥርጣሬ ካለ የመራጮች ምዝገባ መዝገብ በየምርጫ ጣቢያው ለ10 ቀን ክፍት የሚሆንበት እና ቅሬታ የሚቀርብበት ስርአት አለ፣ ፓርቲዎች፣ ታዛቢዎች እና ሲቪል ማህበራት ሂደቱን መታዘብ እና ቅሬታን ማቅረብ ይችላሉ። 

በተጨማሪም የመራጮች ዝርዝር ወደ ዳታ ቤዝ የሚገባ በመሆኑ የተደጋጋሚ የመራጭነት ምዝገባን በቴክኖሎጂ ለመለየት የሚቻልበት አሰራርም በቦርዱ በኩል ተዘርግቷል። በመሆኑም የድምጽ መስጫ ቀኖቹ መለያየት የምርጫውን የጥራት ደረጃ የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይሆንም።

  1. የፓለቲካ ፓርቲዎች የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ የሚያቀርቡትን አቤቱታ ቦርዱ ምን ምላሽ ሰጥቶታል?

የጊዜ ሰሌዳው ከመውጣቱ አስቀድሞ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተከታታይ ምክክሮች ማድረጉ ይታወሳል፣ በዚህም መሰረት የተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች ሁለት ሲሆኑ አንደኛው ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ አለብን የሚሉት ችግሮች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች ናቸው። ያንን መሰረት አድርጎ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ አስቀድሞ ቦርዱ ሁለት ዋና ዋና ተግባራትን አከናውኗል። 

አንደኛው በመንግስት በኩል የምርጫ ጸጥታ እቅድ ዝግጅት እንዲኖር እና ቦርዱ ምርጫን የተመለከቱ እቅዱ ቴክኒካዊ መረጃዎችን እና ሁኔታዎችን ያካተተ እንዲሆን በሂደቱ በመሳተፍ ማረጋገጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በየክልሉ ያሉ በፓርቲዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሶስትዮሽ መድረክ ማዘጋጀት ነው፣ በዚህም መሰረት በየክልሎቹ ፓርቲዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሶስትዮሽ ውይይቶች መከናወን ጀምረዋል።

እነዚህ ውይይቶች እስከአሁን ሶስት ክልሎች ላይ የተደረጉ ሲሆን በዚህ ውይይትም ገዥው ፓርቲ፣ በክልሎቹ የሚንቀሳሰቀሱ ፓርቲዎች እንዲሁም ቦርዱ ተገኝተው ዝርዝር አቤቱታዎች ላይ ውይይት በማድረግ መፍትሄዎች ላይ መስማማት ላይ እንዲደርሱ ጥረት እየተደረገ ነው። እነዚህ አሰራሮች ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ይረዳሉ ብሎ ቦርዱ ያምናል።     

  1. የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ለምን ከምርጫው በፊት አልተደረገም?

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ከምርጫው ጋር መደረጉ የህዝበ ውሳኔውን ኦፕሬሽን በጣም ቀላል የሚያደርገው ሲሆን ከፍተኛ ወጪንም የሚቀንስ ይሆናል፡፡ ቦርዱ ለብሔራዊ ምርጫ እየተዘጋጀ ቀድሞ ህዝበ ውሳኔ ለማደራጀት በቂ ጊዜ የማይኖረው ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ ህዝበ ውሳኔን ለብቻው ለማደራጀት የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ እና ዝግጅት ከብሔራዊ ምርጫ ጋር በመደረጉ በግማሽ የሚቀንስ ይሆናል። 

ቦርዱም አስፈጻሚዎችን በሚያሰለጥንበት ወቅት ተጨማሪ የህዝበ ውሳኔ አስተዳደር ስልጠና በመስጠት፣ ተጨማሪ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ወረቀት በማተም በተመሳሳይ መራጮች ምዝገባ ሂደትን በመከተል ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም ቀላል ይሆንለታል።

  1. ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው እጩዎች ፊርማ ማሰባሰብ የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስመልክቶ ቦርዱ ያደረገው ምንድነው?

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች እጩ ለማስመዝገብ ያላቸውን አጭር ጊዜ በመረዳት፣ እንዲሁም በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ ሊኖር የሚችለውን ንክኪ ለመቀነስ ያቀረቡትንም አቤቱታ መሰረት በማድረግ እጩዎች ለማቅረብ የሚጠበቅባቸውን ፊርማ ለ6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ብቻ እንዲታገድ ለተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄውን አቅርቧል። 

አንዳንድ ጠያቂዎች ለፓርቲዎች መስራች ፊርማ የኮቪድ ወረርሽኝን ቦርዱ ለምን ከግምት ውስጥ እንዳላስገባ ሲጠይቁ የነበረ ቢሆንም የመስራች ፊርማ ማሰባሰብ ጊዜ ገደብ የተጠናቀቀው ወረርሽኙ አገራችን ከመግባቱ በፊት በመሆኑ የፓርቲዎች መስራች ፊርማ ማሰባሰብ እና ኮቪድ ወረርሽኝ ግንኙነት እንዳልነበራቸው ማስታወስ ያስፈልጋል።

(የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top