Connect with us

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅ …

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅና ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ይጠበቅበታል ተባለ
Photo: Social media

ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅ …

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅና ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ይጠበቅበታል ተባለ

 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱ ለማስጠበቅና ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ይጠበቅበታል ሲል በኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡ 

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሰሞኑን በአየር መንገዱ በመገኘት በተቋሙ ዕቅድ አፈፃጸም፣ በኮርፖሬት ፋይናንስ አስተዳደር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻፀም፣ በንብረት አያያዝ፣ አጠባበቅና አወጋገድ ዙሪያ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

በምልከታውም የቡድኑ አባላት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እና ከሌሎች የየዘርፉ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድና የአሊያንስ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ቡሴራ አወል የአየር መንገዱን ዕቅድ ለቡድኑ አባላት ያቀረቡ ሲሆን ‹‹በአለም ዓቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ ወረርሽን ሳቢያ አየር መንገዱ ከበረራ ያገኝ የነበረው ገቢ ቢቀንስም የ25 አውሮፕላኖችን ወንበር በማንሳት ከሌሎች የጭነት አውሮፕላኖች ጋር የካርጎ አገልግሎት በመስጠት ከኪሣራ ለመዳን ተችሏል፡፡ በተከሰተው የገበያ መቀዛቀዝም ከመንግስት የገንዘብ ድጋፍ ሳያገኝ አንድም ሰራተኛ ያላባረረ ብቸኛ አየር መንገድ ሊሆንም ችሏል›› ብለዋል፡፡

የዕቅድ አፈጻፀምን በተመለከተም የውጭ በረራ 7.4 ቢሊዮን ለመፈፀም በዕቅድ ተይዞ ክንውኑ 6.3 ቢሊየን ወይም 85% ሲሆን የሀገር ውስጥ በረራ 93.3 ቢሊየን ታቅዶ 97.9 ቢሊየን የእቅዱ 107% መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለማቀፍ ኤርፖርት ተርሚናል 1 እና 2 ማስፋፊያ 96% መዋቅራዊ ስራው በመጠናቀቅ እንዲሁም የስካይ ላይት ሆቴል ማስፋፊያ በግንባታ ላይ ሲሆን የሰባት ኤርፖርቶች (ሮቤ፣ ጅንካ፣ ኮምቦልቻ፣ ሽሬ፣ ደንቢዶሎ፣ ነቀምት እና ጎዴ) የመንገደኞች ማስተናገጃ ግንባታን ለማስጀመር ከኮንትራክተሮች ጋር በድርድር ላይ እንደሚገኝ፣ የሚዛን-አማን፣ ጎሬ-መቱ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ነገሌ ቦረናና ያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በሂደት ላይ መሆኑን በዋናነት አብራርተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላትም የአየር መንገዱን የደንበኛ አገልግሎት፣ የተርሚናል 1፣2 እና የስካይ ላይት ሆቴል ማስፋፊያ ግንባታን፣ የንብረት ማከማቻ መጋዘኖች አያያዝን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በምልከታው ማብቂያ ላይ የኮሚቴው አስተባባሪ የተከበሩ አቶ መስፍን መንገሻ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ግብረ መልስ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም እና ለሌሎች የየዘርፉ ኃላፊዎች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ በአለም ዓቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ሳቢያ ሲጎዳ አየር መንገዱ ከወረርሽኑ ተፅእኖ እና ኪሳራ ራሱን ለማትረፍ የወሰዳቸውን እርምጃዎች፣ ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማጎልበት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በመንደፍና የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮችን በማመቻቸት ዕቅዱን መተግበር መቻሉን፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሰረት መፈጸም መቻላቸውን፣ የተሚናል 1 እና 2 ማስፋፊያ ግንባታ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን በጠንካራ አፈጻፀም ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም አገልግሎት ላይ የሚውሉና የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ንብረቶች በአይነትና በመጠን ተለይተው መቀመጥ መቻላቸውን፣ አጠቃላይ የድርጅቱ የፋይናንስ ስርዓት በዓለማቀፍ የፋይናንስ አስተዳደር ስርኣት የሚመራና በውጪና በውስጥ ኦዲት እየተደረገ መሆኑንም ቡድኑ በጥንካሬ መመልከቱን ነው ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል የ2013 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድና ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አለመድረሱንና የሩብ ዓመቱ የፋይናንስ ሪፖርት እስካሁን ይፋ አለመደረጉን፣ ተቋሙ የሚሰራቸውን ስራዎች ለህዝቡ በሚገባ ማስተዋወቅ አለመቻሉን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ በተለይ የሻንጣ መጥፋትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ጉድለት መጨመሩን፣ የአገልግሎት መስጫ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች አገልግሎት ከሚሰጡ ንብረቶች በቅርበት መቀመጣቸውን በእጥረት አስቀምጠዋል፡፡

በቀጣይ ለአየር መንገዱ የስራ አፈጻፀም አጋዥ እኛ ጫና ሊኖራቸው ይችላሉ ከተባሉ እንደ ጉሙሩክ ኮሚሽን፣ ክልሎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የስጋ፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖርተሮች፣ ከቱሪዝም ሚ/ር ከመሳሰሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡     

በመጨረሻም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ ጠንካራ ሆኖ ሊቀጥል የቻለው ከመንግስት ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ እና ጠንካራ ቦርድ ስላለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ም/ቤቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተገቢና በቀጣይም ለአየር መንገዱ ስራ ውጤታማነት ተግዳሮት የሚሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቋሚ ኮሚቴው ከአየር መንገዱ ስራ ጋር ከሚገናኙ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት በማድረግ ችግሮቹ እንዲፈቱ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡     

(ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ ~ ሕ/ተ/ም/ቤት)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top