Connect with us

የሁለት ጦርነቶች ዳፋ ያጎሳቆለው ማንነት! 

የሁለት ጦርነቶች ዳፋ ያጎሳቆለው ማንነት!
አብመድ

ማህበራዊ

የሁለት ጦርነቶች ዳፋ ያጎሳቆለው ማንነት! 

የሁለት ጦርነቶች ዳፋ ያጎሳቆለው ማንነት! 

ጦርነት አስከፊ ክስተት፤ አውዳሚ ድርጊት ነው፡፡ በዓለም ላይ መጥፎ የሚባል ሰላም ጥሩ የሚባል ጦርነት እስካሁን አልታየም፡፡ ጦርነት የሃገርን ሃብትና ንብረት ያወድማል፤ ዜጎችን ለህልፈትና ስደት ይዳርጋል፡፡ በጦርነት የከበረ ሃገር እና የሰለጠነ ህዝብ የለም፡፡ ጦርነት የእውቀት ማዕድ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን፤ የዕድገት መሰላል የሆኑ መሰረተ ልማቶችን፤ ክቡር የሆኑ የሰው ልጆችን ይቀጥፋል፡፡ 

ዳሩ ከብዙሃኑ መካከል ከጦርነት ትርፍ የሚሻሙ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች ይኖራሉና ጦርነት በየዘመኑ አይቀሬ ክስተት ሲሆን እናስተውላለን፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹በውጭ ሰርሳሪዎች እና በውስጥ መሰሪዎች›› ምክንያት በጦርነት የታጀበ ነው፡፡ ይህ ታሪካችን በዚህ ዘመን እንኳን አለቀን ብሎ ይህው አሁንም ከጦርነት አልወጣንም፡፡

ባለታሪካችን አሃዝ ከበደ ትባላለች፡፡ አሀዝ በደቡባዊ ትግራይ ዞን በሕንጣሎ ወጀራት ወረዳ ፀሃፍት ቀበሌ ገረብ አጎ መንደር ውስጥ ነዋሪ ናት፡፡ የዛ ዘመን ነፃ አውጭ ነኝ ባይ የሆነችው ትህነግ በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአሀዝ የመኖሪያ ቀየ ዙሪያ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ታካሂድ ነበር፡፡ አሀዝ በህፃንነት እድሜዋ ስለትግልም ሆነ ታጋዮቹ የሰላ እውቀት ባይኖራትም ከታጋዮች አካባቢ አዘውትራ ትገኝ እንደነበር አጫውታናለች፡፡ ከእለታት ባንዱ ቀን ‹‹ተጋዳላይ›› የምትላቸው እነዚያ ገንጣይ አስገንጣዮች የፈጠሩት የተኩስ ልውውጥ የአሀዝን የእድሜ ልክ እጣ ፋንታ በአሳዛኝ ሁኔታ ቀየሩት፡፡ ለተወሰነ ጊዜያት ሳይቋረጥ ከተሰሙት ጥይቶች ሁለቱ በአሀዝ ታፋ ተቀበቀቡ፡፡ 

በታፋዋ የገቡት ጥንድ ጥይቶች አዝለፍልፈው የጣሏት አሀዝ የቀሪ እድሜ ዘመኗን ህይዎት የአንካሴ ድጋፍ ምርኮኛ አድርገዋት አለፉ፡፡ ጥይቶቹ በህክምና ከአሀዝ ሰውነት ውስጥ ቢወጡም ሁለቱም እግሮቿ ግን አካሏን መሸከም ተሳናቸው፡፡ ዘላ ያልጠገበችው፣ የህፃንነት አድሜ ዘመኗን በወጉ ያላጣጣመችው እና ሰርታ ያልጠገበችው አሀዝ በክፉ ቀን አካለ ጎደሎ ሆነች፡፡ አሀዝ ራሷን አውላ ለማሳደር የሌላ ወገንን በጎ ፈቃድ የምትጠብቅ ምስኪን ሆነች፡፡ ህይዎትን በዚህ መልኩ መግፋት ከጀመረችም ከ30 ዓመታት በላይ አሳልፋለች፡፡ 

የእኔ የምትላቸው ደግሞ በዙሪያዋ ያሉ ጎረቤቶቿ ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ወልዶ መሳም ዘርቶ መቃም›› ለአሀዝ በአንዲት ጎደሎ ቀን በተፈጠረ ክስተት የተከለከሉ ፀጋዎች ሆነውባታል፡፡

ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ደግሞ ያ መጥፎ የጦርነት ጠባሳ ዳግም በአሀዝ ቀየ አካባቢ ሲያንዣብብ አይታ እንደተረበሸች ነግራናለች፡፡ ማን ከማን ጋር ይግጠም የማታውቀው አሀዝ ስለጦርነት እየሰማች ሰማይ እንደሌማት ተደፍቶባታል፡፡ ትህነግ የጎሰመችው የጦርነት ነጋሪት ቅድመ ዝግጅቱ ከመኪና መንገድ አቅራቢያ ዶሳሳ ጎጆዋ ለተቀየሰችው አሀዝ ስለመጭው ፍንጭ ሰጥቷታል፡፡ የሚጓጓዘው ከባድ የጦር መሳሪያ ፍርሃት የሚመላለሱት የልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት ስጋትን ፈጥረውባታል፡፡ የአካባቢውን ሰው መሸበር ቁጭ ብላ የምታስተውለው አሀዝ ፍዝ አድርጓታል፡፡ 

ዛሬ ላይ ሩጦ ማምለጥ ፈቀቅ ብሎ መሰወር ለአሀዝ የሚቻሉ አይደሉም፡፡ አማራጩ በቤቷ ውስጥ ሆና የሚመጣውን መቀበል ነው፡፡ አይቀሬው ጦርነት በሚያስገመግም የከባድ መሳሪያ ድምፅ በሰማይ ላይ በሚሽከረከር አውሮፕላን ከሩቅ ሲሰማት በህይዎት ከመኖር ይልቅ ላለመኖር ቅርብ መሆኗን አምና ተቀበለች፡፡ ውሎ ሲያድር በሩቅ የሚሰማው የከባድ መሳሪያ ድምፅ እየቀረበ መጣ፡፡ 

ጎረቤቶቿ ቤቶቻቸውን ዘግተው ልጆቻቸውን ይዘው ከአካባቢው እግሬ አውጭኝ ስላሉ አካባቢው መካነ መቃብር ይመስላል፡፡ ከጦርነቱ ማብቃት ሳልስት በኋላ ወደስፍራው ስናቀና እንኳን በአካባቢው ያገኘናቸው በእጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ 

ለተከታታይ ቀናት ርሃብ፣ ፍርሃት እና ብቸኝነት ያንገላቷት አሀዝ ስለከባድ መሳሪያው ድምጽ ስትናገር እምባ ይተናነቃታል፡፡ ከሰው ከተለየች ከሳምንት በኋላ በሰፈሯ የደረሱት የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ፀጉረ ልውጥ ሆኑባት፡፡ ፈርሃት ቢጫናትም ለርሃብ መድሃኒት የሚሆን ኮቸሮ እና ውሃ እንደሰጧት የነገረችን አሀዝ ወታደሮቹ በአቅራቢዋ ለተከታታይ ቀናት መቀመጣቸው የነገን ብርሃን እንድታይ ምክንያት ሁኗታል፡፡ የቀድሞው ጦርነት አካላዊ የሰሞኑ ደግሞ ስነ ልቦናዊ ጫና ፈጥረውባት አልፈዋል፡፡ 

ጎረቤቶቿ ወደቀያቸው እየተመለሱ ነው፡፡ የሰፈሯ ሰዎች በአካባቢው ከመድረሳቸው አሀዝን ደጋግመው ሲጠሯት ይሰማል፡፡ ጦርነት ግን እንደአሀዝ ያሉ እልፎችን በየጊዜው እየጎዱ ያልፋሉ፡፡ ጦርነት በሰው ልጅ ህይዎት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመግለፅ አሀዝን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ አሀዝ የሁለት ጦርነቶችን ዳፋ አልፋ የነገን ብርሃን የማየት እድል አግኝታለች፤ ሌሎችስ የሚለው ጥያቄ ግን ጦርነት እስካልጠፋ ድረስ ወጥ እና አንድ መልስ የሚያገኙ አይመስሉም፡፡ 

ሰላም ለሁሉም!

(ታዘብ አራጋው – ከደቡባዊ ትግራይ ~ አብመድ)

 

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top