የማይካድራ ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ተቋማት መጣራት አለበት
( በሄኖክ ስዩም)
የማይካድራ ጅምላ ጭፍጨፋ ሌላ ስም የለውም ዘር ማጥፋት ነው፡፡ ጉዳዩ ግን በዚህ አላቆመም በተለያዩ ቦታዎች ከአምስትና ከዚያ በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ጅምላ መቃብሮች እየተገኙ መሆናቸውን በሚዲያ አይተናል፡፡
ይህ ዘግናኝ ድርጊት የሀገር ውስጥ ፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ እርግጥ ነው መንግስት በአጣሪ ኮሚሽን ጉዳዩም እየመረመርኩ ነው ብሎናል፡፡ ግን ከዚያም ማለፍ አለበት፡፡
የማይካድራውም አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሆኖ በጅምላ የሚገኙ መቃብሮች ጉዳይ ሰዎች በማንነታቸው ያለቁበት ለመሆኑ ሙግት አያስገባም፡፡ ምናልባት ግን ነገ ከነገ ወዲያ ከወገን አሰቃቂ ሞት ይልቅ የገዳይ ማንነት ዳግም ካነታረከን ከችግሩ አንማርም፤ አለመማር ብቻ ሳይሆን ችግሩን ላለመድገማችን ዋስትና የለንም፡፡
መንግስት ማድረግ ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ ከኢትዮጵያ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች በስፍራው ተገኝተው አሁኑኑ ጉዳዩን መመርመር ይገባቸዋል፡፡ የታዛቢ ኮሚሽን የሚያስፈልገውም ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
ዓለም ሪፖርቱን አይደለም ማየት ያለበት ስፍራው ድረስ ሄዶ ችግሩን መመልከት የሚችልበት እድል ቶሎ መፈጠር አለበት፡፡ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ከአህጉራችን የተውጣጡ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች የድርጊቱን መፈጸምም ሆነ የፈጸመው አካል ላይ እማኝ መሆን ይገባቸዋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ብዙ ችግር ይቀርፋል፡፡ አንደኛ ነገ ከነገ ወዲያ እንዳይረሳና ወንጀለኞቹ ሌላ የትግል ምክንያት ይዘው ዳግም ለሌላ ወንጀል የሚነሱበት እድል እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡ ብዙ አሰቃቂ ዘር ማጥፋትና ጭፍጨፋዎች ውሎ ሲያድር ተደባብሰው ከአንዱም ሳንማር ተግባሩ የተደጋገመውም ለዚሁ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን አለም እጁን መክተት አለበት፡፡
በሌላ በኩል ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን የትም ይግቡ የት አያመልጡም፡፡ ጉዳዩን የዓለም ካደረግነው እንኳን ተግባሩን የፈጸሙ ተግባሩን የደገፉ ከገቡበት የሚለቀሙበት እድል ይሰፋል፡፡ የማንንም ሀገር ፓስፖርት ይዞ የትም በመደበቅ ዓለም ያወቀውንና የመሰከረውን ጥፋት ፈጽሞ መኖር የማይቻልበት እድልም ሰፊ ነው፡፡
ይህ ፖለቲካዊ ድራማ እንዳይመስልና ተግባሩን የፈጸመው አረመኔ ካደረሰው ጥፋት እኩል ዳግም መንግስት በተዝረከረከ ሪፖርት፣ በተለመደ ወቀሳና ፕሮፖጋንዳ ብቻ እንዳያልፈው ለማድረግ ብቸኛው መፍትሔ አንድም መንግስታዊ ያልሆኑ የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎቹ ከሁሉም አካባቢ ተውጣጥተው የሆነውን ይመልከቱ በገለልተኛነት ይዩት ይስሙት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ማኅበረሰብ ጉዳዩን ይስማው ብቻ ሳይሆን ስፍራው ድረስ መጥቶ ያረጋግጥ፡፡ ለሚጠራጠሩም ለሚክዱም ሸፍጥ ለሰሩም እንዲህ ያለው አሰራር የሚያስማማ ሆኖ ችግሩ ያለ ምክንያት የምንግባበት ክስተት ይሆናል፡፡