ይድረስ ለጌታቸው ረዳ… ባለኽበት!
(ዳዊት ከበደ ወየሳ)
በቅድሚያ ባለኸበት ሰላምታዬ ይድረስህ። ሰሞኑን ካለኸበት የድንጋይ ዋሻ ስር ሆነህ፤ ብዙ ነገር ብለህ ስትጨርስ… ዶ/ር አብይ አህመድን ከሮማውያኑ ጨካኝ እና አምባገነን ካሊጉላ ጋር ስታመሳስለው፤ እጅጉን ተገረምኩ። የተገረምኩት በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው ግርምታዬ… ዶ/ር አብይ አህመድን ከካሊጉላ ጋር ማነጻጸርህ ሲሆን፤ ሁለተኛው ግርምቴ ግን ከሃያ ምናምን አመት በፊት በልጅነትህ ያወራሁልህን የካሊጉላ ታሪክ አሁንም አለመርሳትህ ነው።
በነገርህ ላይ… ዶ/ር አብይ አህመድን የተለያዩ ጉዳዮች ን በማንሳት በሃሳብ ልንሞግተው እንችላለን። ለምሳሌ በቤንሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተደረገውን የዘር እና ሃይማኖት ተኮር የሰው ጥፋት በተመለከተ፤ ወይም ደግሞ በግለሰብ ደረጃ፣ የነእስክንድር ነጋ እና የነልደቱ አያሌውን የእስር ክስ በህሊና ሚዛን ላይ በማስቀመጥ፤ የህግ ሂደቱንና ስርአቱን ልንተች እንችላለን።
ምክንያቱም የቀረበባቸው ክስ፤ እንኳንስ ህዝቡን እራሱ ጠቅላይ አቃቤ ህጉን የማያሳምን፤ የህግ ጭብጥ የሌለውና ውሃም የማይቋጥር በመሆኑ በብዙ መንገድ ጠቅላዩን መሞገት ይቻል ነበር።
በዚያ ላይ… አንተ በህግ ማስተርስ ጭምር ስላለህ፤ ነገሮችን ከህግ አንጻር በማየት አሳማኝ ጉዳዮችን ማንሳት ስትችል፤ በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ ያለህን ጭፍን ጥላቻ ብቻ ሳይሆን፤ “አባይ ተሸጠ” ማለትህ ሳይበቃ፤ “አውሮፕላን መትተን ጥለናል” የሚሉ ውሸቶችን ለአደባባይ አበቃህ። በዚህም የህወሃት ሰዎች ለይስሙላ ሲያጨበጭቡልህ፤ ህዝቡ ግን ዳግም አዘነብህ።
ለነገሩ… ልደቱም ሆነ እስክድር ወይም በዘር ተኮር ዘንግ የሚወገረው ህዝብ፤ በድርጅትህ በኩል በጠላትነት የተፈረጁ በመሆናቸው፤ እንኳንስ የነሱን ጉዳይ ልታነሳ ቀርቶ የሚያነሳ ሰውም ሳያበሳጭህ የሚቀር አይመስለንም። እንዲያው ግን… ካሊጉላን ስትጠቅስ የድሮ ወግ አስታወስከን። የዛሬን አያድርገውና… ድሮ ጥሩ አድማጭ ነበርክ።
ከሃያ አመታት በፊት አንተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለህ፤ እኛ ደግሞ በጋዜጠኝነት ሙያችን ህዝብን ስናገለግል፤ መሃል ላይ የምንገናኝባቸው የአውግቸው ተረፈ እና የፀሃዬ ቤት፤ እዚያም የምናወጋቸው የኪነ-ጥበብ እና የአገር ጉዳዮች ሁሌም እንደሚታወሱህ እርግጠኞች ነን።
“ጥሩ አድማጭ ነበርክ” ያልኩትም፤ ከዚህ ሁሉ አመታት በኋላ የካሊጉላን ነገር ሳትረሳ፤. ዳግም ስታነሳው ብሰማ ጊዜ በመገረሜ ነው።
በነገርህ ላይ ድሮ ስለካሊጉላ፣ ስለጁሊየስ እና ስለኔሮ እያነሳን የምንጨዋወተው፤ አምባገነን መሪዎች… አምባገነናዊ ጥፋት ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ለህዝብም ንቀት ያላቸው መሆኑን ለማሳየት ነበር። ብዙ ጊዜ ከሌሎቹ ጋር የምንከራከረውም፤ እነዚህን የቄሳር አምባገነኖች ከኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም እና አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በማነጻጸር ነበር።
ላንተ የሚቀርቡህ ሰዎች፤ ቄሳሮችን ከኮ/ል መንግስቱ ጋር ሲያነጻጽሩ፤ እኔ ደግሞ እነካሊጉላን ከነመለስ ዜናዊ ጋር በማነጻጸር ብዙ ክርክር እናደርግ ነበር። አሁን ደግሞ ያ ሁሉ ጊዜ አለፈና… ከሃያ ምናምን አመታት በኋላ… አንተ ደግሞ በተራህ፤ ካሊጉላን ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ብታነጻጽረው ጊዜ… “ኧረ ተው ጌቾ… ኧረ ተው!” አስባልከኝ።
በነገርህ ላይ ካሊጉላ “ፈረሱን የሮም ምክር ቤት አባል አድርጎት ነበር” ብዬ የነገርኳቹህ፤ እንዲያ ለጨዋታው ድምቀት ያህል እንጂ፤ ካሊጉላ ፈረሱን አባል ለማድረግ ሃሳብ ነው ያቀረበው። ሆኖም ጭካኔና አምባገነናዊነቱ እየበዛ ሲመጣ የሮም ህዝብ አመጸበት፤ እሱም ተገደለ። እንዳልከውም… የጭካኔው ምንጭ የአእምሮ ህመም ነው።
የአእምሮ ህመሙ ምንጭ ደግሞ… ልክ እንደህወሃት ጥልቅ የሆነው ጥላቻ ነው። እናም ህወሃት ሰው ቢሆን ኖሮ… ካሊጉላ ማለት የህወሃት ሌላ የሳንቲም ገጽታ ማለት ነው።
ጌቾ ደብዳቤዬን ከማገባደዴ በፊት ሁለት ነገሮችን ላንሳልህና ልሰናበትህ። አንደኛው የራያ ጉዳይ ሲሆን፤ ከዚያው ጋር አያይዤ ስለህወሃት ትንሽ ነገር ብዬህ እለይሃለሁ። ታስታውስ እንደሆን… ከሃያ አመታት በፊት ስለራያ ታሪክ እንዲህ ብዬህ ነበር። ከግራኝ አህመድ ጦርነት በኋላ፤ ማለትም ከአምስት መቶ አመታት በፊት የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የአገራችን ክፍል ይስፋፉ ጀመር።
ከነዚህም መካከል ከዋናው በርቱማ እና ቦረን ዋና አባቶች ሆነው፤ ከበርቱማ የዘር ሃረግ ሁ’በና እንደሚወለድ፤ የሁ’በና ትውልድ ደግሞ አዋሽን ተሻግሮ፤ ወሎን አልፎ እስከትግራይ መዝለቁን…. ከነዚህም መሃል ቆቦ፣ አዘቦ፣ ራያ እና አሸንጌ ትግራይ ድረስ ገብተው ብዙ ትግል እንዳደረጉ፤ የጄምስ ብሩስን መጽሃፍ ጭምር እያጣቀስኩ አወጋቹህ ነበር።
ከነዚህም የኦሮሞ ተወላጆች ውስጥ፤ የአሸንጌ የልጅ ልጆች ከትግራይ ሰዎች ጋር መጋባታቸውን፤ ሌሎቹ ደግሞ ከአማራው እና ከአፋሩ ህብረተሰብ ጋር ተጋብተው፤ ባህል እና ቋንቋቸው እየተቀየረ መምጣቱን ሳወጋቹህ፤ አንተ በጣም በተመስጦ ስትሰማ ቆይተህ፤ በመገረም የተናገርከውን ቃል እንኳንስ እኔ እነጸሃዬም የሚያስታውሱት ይመስለኛል። ትረካዬን ስጨርስ፤ ከተመሰጥክበት የሃሳብ ባህር ብንን ብለህ…. “ለዚህ ነው ለካ!?” አልከን በመገረም።
“ምኑ?” አልንህ እኛም በመደነቅ።
“ልጆች እያለን የገበያ ቀን… ከአላማጣ ማዶ ከሩቅ ቦታ የሚመጡ፤ ቋንቋቸው አማርኛም ትግርኛም ያልሆነ፤ በኋላ እንደተረዳሁት ግን ኦሮምኛ የሚናገሩ ሰዎች እናይ ነበር።” በማለት… ቋንቋውን እስከ-አንተ እድሜ ድረስ ይናገሩ እንደነበር ነግረኸናል።
እንግዲህ ይህ ሁሉ ወግ ሃያ አመታትን የዘለለ ነው። ከዚያ በኋላ… አላባማ፣ አሜሪካ ማስተርስህን ለመስራት ስትመጣ በስልክ አውርቼሃለሁ። ከአሜሪካ መልስ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ዲን፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ፤ የኮሚዩኒኬሽን ሚንስትር፤ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል… አሁን ደግሞ የደብረጽዮን አማካሪ በመሆን እየሰራህ ነው።
በነዚህ የስራ ሃላፊነቶች ላይ እያለህ አንድም ቀን አግኝቼህ ባላውቅም፤ አንድ ቀን ባገኝህ ልነግርህ የምፈልግ የነበረው፤ “ተው ጌች… እንደድሮህ ሁን። እንደልጅነትህ አድማጭ እና አስተዋይ ሁን። እባክህን ጌቾ… ተወልደህ ስላደክበት ስለአላማጣ እና ስለራያ ህዝብ ብለህ ለአንድ ደቂቃ ባለህበት ቆመህ፤ ስለተሳፈርክበትና እየሰጠመ ስላለው የህወሃት መርከብ እንድታስብበት ላሳስብህ ወደድኩ።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያቴ… በዙሪያህ ያሉት ሰዎች፤ መቃብራቸው የተማሰ፣ መገነዣ ልጣቸው የረሰረሰ ናቸው። ሁሉም እንደጠዋት ጤዛ የሚያልፉ ሰዎች እንጂ፤ ከዚህስ በኋላ ምን ያህል እድሜ አላቸው? አንተንም ቢሆን በራያ ተወላጅነትህ… ራያን በትግራይ ክልል ስር ለማካለል ካላቸው ፍላጎት አንጻር ፈለጉህ እንጂ፤ እንዴት ይወዱኛል? ይቀበሉኛል ብለህ ታስባለህ? እነሱን ለመሆን እና ለማከል… ቢያንስ ከአክሱም፣ ከአድዋ ወይም ከሽሬ መወለድ አለብህ።
የዘር ልጓምህ ከነዚህ ምርጦች ከአንዱ ካልሆነ፤ ህወሃት ለጊዜው ይጠቀምብሃል እንጂ ፈጽሞ አይፈልግህም።
ጌቾ… እኔ የማይህ እንደትግራዋይ ወይም እንደቀድሞ ባለስልጣን ወይም እንደአዛዥ እና ናዛዥ አይደለም። ልጅ ለወላጁ ሁሌም ልጅ እንደሆነ ሁሉ… እኔ የማየው የድሮውን አድማጭ እና አስተዋይ የነበረውን…. ጌታቸው ረዳን ነው። ይገባናል… ከህወሃት ብትለይ፤ ተለይተህም ብትወጣ “ያጠፉኛል” ብለህ ትሰጋ ይሆናል። ደግሞም ከህወሃት ጋር በመሆንህ ጥቅም ስታገኝ እንደነበር ይታወቃል፤ ያ ጊዜ ግን አልፏል።
ጌቾ እውነቱን ልንገርህ… ከህወሃት ጋር በመጣበቅህ የተሻለ ከለላ ያገኘህ መስሎህ ይሆን ይሆናል። ነገር ግን ካለህበት እና ከመሸግክበት ዋሻ ውጪ መሃሪ አምላክ፤ ይቅር ባይ የኢትዮጵያ ህዝብ መኖሩን አትርሳ።
የዘር ጥላቻ መቃብርህን አርቀህ ከምትቆፍር፤ የቤተሰብህን፣ የአላማጣን፣ የራያን፣ የልጆችህንና የኢትዮጵያን ስም ይዘህ ወደ ሲኦል ከምትሄድ፤ ከሄድክም በኋላ በክፉ ከምትነሳ… እባክህን “ይቅር በሉኝ” ብለህ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ታረቅ።
እንደገና ልድገምልህ…. ካለህበት እና ከመሸግክበት ዋሻ ውጪ መሃሪ አምላክ፤ ይቅር ባይ የኢትዮጵያ ህዝብ አለ። እባክህን “ይቅር በሉኝ” ብለህ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ታረቅ። ይህን ማድረግ ከቻልክ ዳግም በአካለ ስጋ ተገናኝተን፤ ስለካሊጉላ እናወራ ይሆናል። ስለራያም ህዝብ ታሪክ ዳግም እንጨዋወታለን።
ይህን ማድረግ ካልቻልክ ግን… ካሊጉላን በሰማየ ሰማያት የሲኦል እሳት ተከቦ ታገኘው ይሆናል። እነሆ የአላማጣና የራያም ህዝብ የወያኔን ሙት-አመት እያከበረ፤ እናንተንም መዝገብ ላይ አኑሮ… ለዘላለም ሲያስታውሳቹህ ይኖራል።
የመጨረሻው ምክሬም አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ጌቾ… እጅህን በሰላም ስጥ። አራት ነጥብ።