ቅዱስ ሲኖዶስ ከኅዳር 1 እስከ 7 በመላው አድባራት እና ገዳማት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ዐወጀ
***
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በዓመት ለኹለት ጊዜያት እንዲኾን፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት፣ የምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ፣ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሒድ ሰንብቶ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን የሚበጁ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚኹ መሠረት፡-
1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቀረበው የጉባኤ መክፈቻ ንግግር፣ የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ ኾኖ እንዲያገለግል ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
2. ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ ውይይት የተካሔደበት፣ የ39ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫን፣ ጉባኤው ተቀብሎ ያጸደቀው በመኾኑ ለሚመለከታቸው ኹሉ ተላልፎ በሥራ እንዲተረጐም ተወስኗል፡፡
3. የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ችግር አስመልክቶ፣ በጉባኤው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲኾን፣ ባለፈው አንድ ዓመት፥ በአገራችን በኢትዮጵያ፣ በቤተ ክርስቲያናችንና በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍ እና መከራ እንዲቆም፤ በየምክንያቱ በክርስቲያንነታቸው ምክንያት የታሰሩ ካህናት እና ምእመናን ጉዳያቸው እየታየ ከታሰሩበት እንዲፈቱ፤ የመንግሥት የበታች ባለሥልጣናትም ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጉባኤው አጥብቆ አሳስቧል፡፡ ከዚኹ ጋራ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ ባለፈው ለደረሰው ጥፋት እና ለወደፊትም የሕግ ክትትል በማድረግ ችግሩን የሚከላከሉ የሕግ ባለሞያዎች ኮሚቴ፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
4. ወቅታዊ አገራዊ ሰላምን በተመለከተ፣ ጉባኤው በሰፊው ተነጋግራል፡፡ በአገራችን ያለው ወቅታዊ የሰላም ዕጦት፣ እየታየ ያለው አለመግባባት፣ ለዜጐች ተረጋግቶ አለመኖርና ለሁከት አልፎ ተርፎም ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየኾነ በመኾኑ፣ በቀጣይም አላስፈላጊ ሁከት ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ እርቅና ሰላም ማምጣት አስፈላጊ እንደኾነ ጉባኤው አምኖበታል፡፡ በመኾኑም፣ የእርቅ እና የሰላም ሒደቱን የሚያስፈጽሙ ብፁዓን አባቶችን በአስታራቂነት ሠይሟል፡፡
5. በአገራችን ኢትዮጵያ የሕዝባችን የዘመናት ድህነት እና የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ፣ ለአገራችን ብልጽግና ኾነ ለሕዝባችን ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አካባቢያዊ ጦርነት እንዲነሣ ያስተላለፉት መልእክት፣ አገራችን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ወይም በሞግዚትነት ለማስተዳደር የተደረገ ሙከራ በመኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ተቃውሞታል፡፡ የዓለም መንግሥታት እና ሕዝቦች፣ እንዲህ ዓይነቱን ትንኮሳ እና የቅኝ ግዛት ፍላጐት እንዲቃወሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
6. በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 50 የሚገኘው፣ በአሁኑ ጊዜ ባለው የሀገረ ስብከቱ አሠራር ላይ አመቺ ኾኖ ስለአልተገኘ፣ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲወጣና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ ተመድቦለት እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ከዚህም ጋራ አሁን እየተሠራበት ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከወቅቱ ጋራ ተገናዝቦ መሻሻል እንዳለበት ስለታመነ፣ ይኸው እየተሠራበት ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን መርምረው እና አጥንተው መሻሻል የሚገባቸውን ነጥቦች አሻሽለው ወደፊት በቋሚ ሲኖዶስ ከሚመረጡ የሕግ ባለሞያዎች ጋራ ሕጉን አሻሽለው ለግንቦቱ ርክበ ካህናት እንዲያቀርቡ ሦስት ብፁዓን አባቶችን ጉባኤው መድቧል፡፡
7. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አፈጻጸምን አስመልክቶ፣ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተወሰኑ የተፈጸሙንና ያልተፈጸሙትን በመለየት፣ ሊፈጸሙ ያልቻሉበት ምክንያት ተገልጾ ለፊታችን ግንቦት ርክበ ካህናት ውጤቱ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
8. የብፁዓን አባቶች የሥራ ምደባ እና ዝውውር በማስፈለጉ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ኹኔታ ከመረመረ በኋላ፣ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ዝውውር እና ዐዲስ የሥራ ምደባ ተካሒዷል፡፡
9. በምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቆጋ ምስካበ ቅዱሳን ኪዳነ ምሕረት ገዳም ተከሥቶ የነበረውን የዶግማ እና የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ፣ ችግሩ በአጣሪ ልዑካን እንዲጣራ ተደርጐ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ፣ “በመንፈስ ቅዱስ ጵጵስና ተሹመናል፤” ያሉት መነኮሳት የፈጸሙት ድርጊት አግባብነት የሌለው፣ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ኾኖ ስለተገኘ፣ መነኮሳቱ በራሳቸው የለበሱት ልብሰ ጵጳስና እና የጵጵስና ቆብ አውልቀው፣ ንስሐ ተሰጥቷቸው በምንኩስናቸው ብቻ ተወስነው በገዳሙ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ ተወስኗል፡፡ ከዚሁ ጋራ፣ ተፈጸመ የተባለው ዳግም ጥምቀት እና ክህነት፣ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የኾነና ቤተ ክርስቲያናችን የማትቀበለው በመኾኑ፣ ይህን ድርጊት የፈጸሙ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
10. “የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ነን” ከሚሉ አባላት ጋራ በተደረገ ውይይት መግባባት ደረጃ ላይ በመደረሱ፣ የተያዘባቸው ክህነት ተለቅቆ፣ በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ የሥራ መደብ ተሰጥቷቸው እንዲያገለግሉ ተወስኗል፡፡
11. የቤተ ክርስቲያን የ2013 ዓ.ም. አጠቃላይ በጀት ላይ የተነጋገረው ምልዓተ ጉባኤው፣ ከበጀት እና ሒሳብ መምሪያ በቀረበው የበጀት ድልድል ላይ ተነጋግሮ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል አጽድቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ከላይ በተጠቀሱት ነጥቦች እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በስፋት ተነጋግሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው የጐርፍ መጥለቅለቅ እና የአንበጣ መንጋ በበርካታ ወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ችግር ከፍተኛ መኾኑን ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ በመኾኑም፣ ኅብረተሰቡ ለተቸገሩ ወገኖቻችን የተለመደ ድጋፉን ከማድረግ ወደኋላ እንዳይል ምልዓተ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በአገራችን በኢትዮጵያ እና በዓለማችን እየታየ ያለው አለመግባባት፣ የጐርፍ መጥለቅለጥ፣ የበሽታ ወረርሽኝ የመሳሰሉት ኹሉ፣ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ ተመልክቶ ሰላሙንና አንድነቱን ለዓለማችንና ለሕዝባችን ይሰጥልን ዘንድ፣ ከኅዳር 1 እስከ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ፣ በመላ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት እና አድባራት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
በመጨረሻም፤
አገራዊ ሰላምንና አንድነትን አስመልክቶ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት፣ የእርቅ ሒደቱን የሚቀጥልበት ኾኖ ከዚኹ ጋራ የፌዴራል መንግሥቱ፣ የየክልል መሪዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊ ኹሉ፣ ለአገራችን አንድነት እና ሰላም፣ ለልማቱ እና ለሕዝባዊ አንድነቱ በጋራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን እያቀረበ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ከጥቅምት 11 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለ13 ቀናት ሲያካሒድ የቆየውን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል፡፡
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይኹን፤
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይጠብቅ፡፡