Connect with us

የአማራ ብልጽግና ሆይ፤ ቢያንስ የገዳይ ስም ባትደብቅስ፤

የአማራ ብልጽግና ሆይ፤ ቢያንስ የገዳይ ስም ባትደብቅስ
The exact death toll remains unknown, with local media reports speaking about 'several dozen deaths' [File: Giulia Paravicini/Reuters]

ወንጀል ነክ

የአማራ ብልጽግና ሆይ፤ ቢያንስ የገዳይ ስም ባትደብቅስ፤

የአማራ ብልጽግና ሆይ፤ ቢያንስ የገዳይ ስም ባትደብቅስ፤
ኦነግ ሸኔ ማለት ሲያስፈራ ወያኔ እያሉ እስከ መቼ?
ከስናፍቅሽ አዲስ

የአማራ ብልጽግና መግለጫን ሰማሁ፤ ያ በጫካ ያለ ሐጢአቱ የታረደው ወገን ፍትሕ ቢያጣ እንኳን ሟቹ ባይቀየርበት ጥሩ ነበር፡፡ ለሁሉም ነገር ወያኔ እያሉ ከዘመን ዘመን መሻገር የፖለቲካ ቁማር ነው፡፡ ከምክንያት ፖለቲካ የምንገላገልበትን ቀን እየናፈቅን የሟች ቁጥር እንደምራለን፡፡

የአማራ ብልጽግና አማራውን አበለጽጋለሁ እያለ ሞቱ ካልጎዳውና የሚመራው ህዝብ ህመም ካላመመው ያሳዝናል፡፡ ህዝቡ ግን ቢያንስ የገዳዩ ስም ባይደበቅበት፤ ህዝቡ እኮ ገዳዩን ያውቀዋል፡፡ ኦነግ ሸኔ ብቻውን አይሳሳትም ለማለት ነጋ ጠባ ወያኔን በየጥፋቱ ላይ መመረቁስ እስከመቼ?

በወለጋ የሆነው ነገር ያሳዝናል፡፡ የመተከልና የጉራ ፈርዳ ድንኳን ሳይነቀል ሌላ የወገን ጭፍጨፋ ዜና ሲመጣ አንድ ጠረጴዛ ከቦ ቃላት በመደርደር ሀገር አይፈርስም እያሉ መፎከር ሀገር ማፍረስ እንጂ ሀገር መስራት አይደለም፡፡ ያልመሯት ሀገርስ እንዴት አትፈርስም፤ ሰው ያለ ሐጢአቱ በዘሩ ምክንያት በየቀኑ የሚገደልባት ሀገርስ ፈርሳለች ነው አለች የሚባለው?

የአማራ ብልጽግናም ሆኖ ወንድሙ የሆነው የኦሮሚያ ብልጽግና አንድ ቋንቋ የሆኑበትና ኦነግ ሸኔ እንዲህ አደረገ ለማለት ህወሃትን ካልመረቁ የማያወሩበት ምክንያትስ ምን ይሆን? ኦነግ ሸኔን አጸዳነው ከተባለ በኋላ ጥፋት ሲመጣ እሱ ነው እያሉ ከተጠያቂነት ማምለጥስ ይቻላል ወይ?

ወለጋም መተከልም ሲተራመስ ህወሃት ናት ብሎ ወያኔን በመጥራት መኖር የሚቻለው እስከ መቼ ነው? ይሄ ህዝብ እውነት እንዲህ የምታደርገው ወያኔ ከሆነችስ ከወያኔ የማያስጥል መንግስት በራሱ ላይ ማንገሱ ጥቅሙ ምንድን ነው?

የአማራ ብልጽግና ኦነግ ሸኔ ማለት የፈራ በሚመስል ድምጽ ዛሬም ህወሃትን መርቋታል፡፡ ከዚያም ሲያልፍ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋውን ማን ማስቆም እንዳለበት የረሳው መንግስት መሆኑ ትዝብት ውስጥ ይከተዋል፡፡ አሁን ያለው የአማራ ብልጽግና ነጻና የማንላላክበት መንግስት መስርተናል ብሎ የሚናገር ነው፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ እየመራ ወገኑ ሲያልቅ በመግለጫ የሚያላግጥ መንግስት መሆኑ ከተጠያቂነት አያድነውም፡፡

በንጹህ ነፍስ የፖለቲካ ቁማሩ ቀጥሏል፡፡ እምነቱ ምንም ቢሆን ዛሬም አማራ በማንነቱ ይገደላል፡፡ በማንነቱ ይታረዳል፡፡ እድሜውና ቁጥሩ፣ ጾታውና ሃይማኖቱ ከቢላ አያድነውም፤ ከጥይት አያስመልጠውም፡፡ ይሄንን ቁማር ማስቆም የማን ድርሻ ነው? ዜጎቹን የማይጠብቅ መንግስት ስራውስ ምንድን ነው? ወገን የተራ ጉዳይ ነው እንጂ ሁላችንም ሟች ነን፡፡

Click to comment

More in ወንጀል ነክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top