Connect with us

እጅጋየሁ ሽባባው/ጂጂ

እጅጋየሁ ሽባባው/ጂጂ
Photo: Social media

መዝናኛ

እጅጋየሁ ሽባባው/ጂጂ

እጅጋየሁ ሽባባው/ጂጂ

(ውድነህ ክፍሌ ~ ፀሐፊ ተውኔት/ደራሲ)

አንዳንዶች የጥበብ ዘሩን በውስጧ የዘሩት እናትየው ናቸው ይላሉ፡፡ ጂጂም/እጅጋየሁ ሽባባው “እናቴ መጽሐፍ ታነብልኝ ነበር፡፡ አብረንም እናነብ ነበር!” ስትል ስለወላጅ እናቷ ወ/ሮ ተናኜ ስዩም ምስክርነት ትሰጣለች፡፡ እናትም ስለልጃቸው ሲናገሩ “ራሷ ነች የምትጽፈው፡፡ ምንም ሳትጨነቀ ነው የምትሰራው፡፡ በጣም ጎበዝ ናት፡፡ 

እንደቤተሰብ እንደዚህ ቢሆን እንዲህ ብታደርጊ የሚል አስተያየት ሊኖር ይችላል!” ሲሉ ልጅነቷ ላይ ስለነበረ ጥንካሬ ጠቆም ያደርጋሉ፡፡ በእርግጥም እናት ዋዛ አይደሉም፡፡ የአንድ ረጅም ልብ ወለድ ደራሲ ናቸው፡፡ ርእሱም “ፍቅር ድንግልና” የሚሰኝ ነው፡፡

ጂጂ በልጅነቷ በቤት ውስጥ ሁሉንም ትሞካክር ነበር፡፡ ትጽፋለች፤ትዘፍናለች ሲላትም ትተውናለች፡፡ እንደውም የሎሬት ጸጋዬ ትርጉም የሆነውን ኦቴሎን ሁሉንም ገጸባህሪ እየወከለች አጥንታ ቤት ውስጥ ታቀርብ ነበር፡፡…ትንሿ ጂጂም በቤት ውስጥ አልቀረችም፡፡ ጥሪዋን በብዙ ውጣ ውረድ ፈልጋ በማግኘት አንቱ የተሰኘች ድምጻዊት ሆና አጃኢብ አሰኝታለች፡፡ 

ሰባት የሙዚቃ አልበሟን ለህዝብ አቅርባም ሙሉነቷን አሳይታናለች፡፡ በስራዋም ጉምቱ የጥበብ ሰዎች ሳይቀሩ አድናቆታቸውን ለመግለጽ ወደኋላ አላሉም፡፡ 

የፎክለር መምህሩን መደመም ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የጻፈውን መግለጽ ግድ ነው፡፡ መምህሩ ገጣሚ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ናቸው፡፡ ወደ ክፍል ሲገቡ ለተማሪዎቻቸው እንደዚህ አሉ፡፡ “ዛሬ እንቅልፍ ሳይወስደኝ ነው ያደርኩት!?” ተማሪዎችም “ምነው!?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ እርሳቸውም “`ፍቅር እየራበኝ` እያለች የምትዘፍን ልጅ እጅግ እየደነቀችኝ ደጋግሜ ስሰማት ነው ያደርኩት! …በኢትዮጵያ ውስጥ ከ26 ዓመት በኋላ በሙዚቃ ነፍሴን የገዛችው ይህቺ ድምጻዊ ናት!” ሲሉ መሰከሩ፡፡ 

የፊልም ባለሙያው ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማም እንዲህ ማለታቸውን ጥቤ ከትቦታል “አሁን ባለው ትውልድ ውስጥ አንድ ነበልባል ትውልድ ብቅ ብሏል፡፡ እነዚህም እጅጋየሁ ሽባባውና ቴዲ አፍሮ ናቸው!” ሲሉ፡፡ 

የሙዚቃ አዋቂው ቢል ላስዌልም ቢሆን ስለልጁ እናት/ስለጂጂ/ ከፍቺ በፊት እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር “ጂጂ ተሰጥኦ ያላት ድምጻዊ ነች፡፡ …ማዜምን የታደለች ተፈጥሯዊ ዘፋኝ ነች፡፡ ለበርካታ ጊዜ ሳትዘፍን ሳትለማመድ ብትቆይም ችሎታዋ አይነጥፍም!” 

ሲ ኤን ኤን/CNN “New Taleneted Ethiopian Singer`” ሲል ያሞካሻት ጂጂ የተወለደችው ቻግኒ ነው፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥቅምት 21/1974ዓ.ም ነው፡፡

ከፍ ያደረገችን ጂጂ ቀና እንድትል አለንልሽ፣ በርቺ ልንላት ይገባል፡፡ እህቷ ዘማሪ ሶፊያ በቅርቡ “ማን ያውቃል እዚሁ ቦታ ላይ ጂጂ ቃለመጠይቅ ታደርግ ይሆናል!” ብላ ለኢቢኤስ ቲቪ ቅዳሜ መዝናኛ ተስፋ እንደሰጠችን ጂጂን በአዲስ መንፈስ እናገኛት ይሆናል፡፡ ለሁሉም መልካም ልደት ከጤና ጋር፡፡

በመጨረሻም ጥበቡ በለጠ፤ ዳንኤል ገዘኸኝና ዳዊት አርአያ ስለጂጂ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን የጻፉትን ብታነቡ ጥሩ መረጃ ታገኛላችሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ክብረት ይስጥልኝ፡፡

 

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top