በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ስለሚጥል እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑን የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው ምርጫውን በተመለከተ የፌደሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት የውሳኔ ሃሳብም አቅርቧል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ እያካሄደ ነው።
የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ወርቁ አዳሙ እንዳሉት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ነው።
በህገ መንግስቱ መሰረት የምርጫ ህግ ማውጣት ለፌደራል መንግስቱ ምርጫውን ማስፈጸም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን ገልጸዋል።
ቦርዱ በሚቋቋምበት ወቅትም ክልሎች ስልጣን ይኑራቸው የሚል አንቀጽ አልሰፈረም ብለዋል።
ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያም የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከላከል ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ተሰጥቶ ምርጫው እንዲራዘም በፌደሬሽን ምክር ቤት የቀረበውን ውሳኔ ሳይቀበል መቅረቱን አስታውሰዋል።
ምክር ቤቱ ክልሉ ምርጫ የሚያደርግበት ስልጣን እንደሌለው ቢያሳውቅም፤ በሕገ መንግስቱ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ የምርጫ ህግ በማውጣትና የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም እንቅስቃሴ ማድረጉን አመልክተዋል።
ከዚህም ባለፈ ምርጫው ህጋዊ መሰረት የሌለውና መቆም እንደሚገባው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ፤ የራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መጠየቃቸው ፀሐፊው ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስገዳጅነት የፌደራልም ሆነ የክልል ምክር ቤትና አስፈጻሚ አካላት ምርጫ ተደርጎ ለአሸናፊው አካል እስከሚያስረክቡ ባሉበት እንዲቀጥሉ የቀረበውን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉ ተገቢ ባለመሆኑ በቀረቡት የውሳኔ ሃሳቦች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ቋሚ ኮሚቴው የትግራይ ክልል የምርጫ ሂደት ሕገ -መንግስታዊ ስርዓቱን ያልጠበቀ፣ በነጻነት ለመወዳደር የማያስችል መሆኑ ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀረበውን ጥያቄ አይቷል ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው የትግራይ ክልል በምርጫ ቦርድ ስልጣን ጣልቃ በመግባትና ሕገ መንግስቱን በመቃረን በሚያደርገው ምርጫ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቋል።
በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸው፣ ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት እንደሌለው ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት አቅርቧል።
ትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸው፣ ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት እንደሌለው ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት አቅርቧል።
ምንጭ:- ኢዜአ