ኑ ባቢሌ እንሂድ፤
****
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ኑ ባቢሌ እንሂድ ሲል የዝኆኖች መጠለያ የኾነውን መስህብ ፍለጋ ተጉዟል፡፡ በኤረር ሸለቆና በጉብሌ ዳርቻዎች ያደረገው ቆይታ እንዲህ ይተርክልናል፡፡)
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
ዛሬ ቅዳሜ ነው፤ ቅዳሜ ባቢሌ ደርሶ የሚያውቀው የእኩለ ቀኑ ድባብ ይገዝፍበታል፡፡ ከአዲስ አበባ ጅግጅጋ የሚጓዝ ሀረርን እንዳለፈ ሞቅ ያለች ከተማ ካገኘ እሷ ባቢሌ ናት፡፡
ባቢሌ ምልክቷ ብዙ ነው፤ የደመ ግቡዎች መዲና ናት፡፡ ደማቅ የንግድ እንቅስቃሴ መገለጫዋ ነው፡፡ ጎዳናዋ ግርግር አያጣም፡፡ መንገደኛው መኪና ሁሉ ጨክኖ አያልፋትም፤ መንገድ ሳትሆን ማረፊያ ናት፡፡
የመጣሁት የዝኆኖችን መጠለያ ፍለጋ ነው፡፡ ብዙ ቋንቋ እሰማለሁ፤ ባቢሌ ላይ የባቢሌን ነዋሪ መለየት አይከብድም ባቢሌዎች በቀላሉ ተግባቢ ናቸው፡፡ ጎዳናዋ ላይ ዓይኑን ለወረወረ የጫት ገበያዎችን ይመለከታል፡፡ ግን ብቻቸውን አይደሉም፤ ጥላ የተዘረጋላቸው የለውዝ ትሪዎች፤ አጠገባቸው ደግሞ የፍራፍሬ ድርድር፤
ባቢሌ የንግድ ከተማ ናት፡፡ እንደ ጂኤፍ የገባ የማይወጣባቸው ደግ ቤቶች ብዙ ናቸው፡፡ ኮረብታውን ታኮ የቆመው መስጂድ የከተማዋ የውበት መገለጫ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከስምንት እስከ አስር አረፍ ትላለች፤ መልሶ መሸት ሲል ግርግሩ ይቀጥላል፡፡
ጥብሳ ጥብሱ ጎዳናዋ ላይ አይጠፋም፡፡ ሰው ባለው የሚቀምስባት ከተማ ናት፡፡ አደምን ብዬ መጥቻለሁ፤ ከቤን ብዬ ደርሻለሁ፡፡ የባቢሌ ዝኆኖችን ፍለጋ፤
ወደ ከተማዋ ዳርቻ ልወጣ ነው፡፡ እነኛን ምትሃተኛ ድንጋዮች ሰው ያፈዛሉ፡፡ የጅግጅጋን መንገድ ይዛችሁ አምስት ኪሎ ሜትር ተጓዙ፤ እዚህ ጋር ነው ባይ አያስፈልግም፤ የዳካታ ድንጋዮች ተንጠራርተው እዚህ ጋር ነን ይላሉ፡፡
አቤት አሰራር፤ ተፈጥሮ ትችልበታለች፡፡ አንዱ ድንጋይ ሌላ የድንጋይ ቆብ አድርጓል፡፡ ደግሞ እዚያ ሌላ ድንጋይ ሱሪውን ያወለቀ ወንድ ቆሞ የማይ እስኪመስለኝ አፍዝዞኛል፡፡ ተደርድረዋል፤ አንዱ ሌላውን አይመስልም፤ የየራሳቸው ውበት፤ የየራሳቸው
አቀማመጥ፤ የየራሳቸው ገጽ አላቸው፤ የዳካታ ትክል ድንጋዮች፡፡ ጉርሱምም ኮምቦልቻም እንዲህ መሰል ድንጋይ ታዮ ይሆናል፡፡ ይሄኛው ግን ብዙ ነው፤ ዓይነቱም ቁጥሩም፡፡ መኪኖቹ በጎዳናው ይከንፋሉ፤ ገና ወደ ኤረር ሸለቆ እንገባለን፡፡ ቅዳሜን በምናብ እንዲህ ያለ ቦታ ማሳለፍ መታደል ነው፡፡