የአበበ በቂላ የሮም የማራቶን ድል 60ኛ ዓመት እንዲዘከር ተወሰነ
—
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትላንትናው እለት ረብዕ ነሃሴ 13 ቀን 2012 ዓ. ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ልዩ ልዩ ወቅታዊ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፤
ከነዚህም መካከል፡-
1ኛ) የጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ 60ኛ አመት የኦሎምፒክ ማራቶን ድል መታሰቢያ በልዩ ፕሮግራም እንዲዘከር ወስኗል፤
እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ. ም. በሮም የኦሎምፒክ አደባባይ ማራቶንን በባዶ እግሩ በመሮጥ የአፍሪካን፣ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነትና ፅናት ለአለም ያሳየበት 60ኛ አመት በሚዘከርበት ፕሮግራም ላይ እ.ኤ.አ ከ1956 ሜልቦርን፣ አውስትራልያ እስከ 2016 ሪዮ ዲ ጄኔሮ፣ ብራዚል ኦሎምፒክ ድረስ ኢትዮጵያን በአትሌቲክሱ ዘርፍ በመወከል የተሣተፉ በህይወት ያሉ በአካል፣ የሌሉት የኦሎምፒክ ጀግኖቻችን ደግሞ በቤተሰቦቻቸው አማካይነት ተወክለው በልዩ ዝክረ-ፕሮግራሙ ላይ እንዲታደሙ ከሚመለከታቸው ባለድርሻና የሚዲያ አካላት ጋር በትብብር እንዲሰራ ተወስኗል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ስኮላርሺፕ በፕሮግራም ተዘጋጅቶ በተለይም ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል አግባብ (Women Empowerment) በሃገራችን ውስጥ በሚገኙ በየትኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚዘጋጀውን መስፈርት የሚያሟሉ 2፣ 2 ብቁ ሴት አትሌቶች ወይም አሰልጣኞች በየአመቱ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወጪ የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተወሰነ ሲሆን ይህ የስኮላርሺፕ መርኃ ግብር በጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ 60ኛ አመት የአሸናፊነት ዝክረ-ፕሮግራም ላይ ይፋ የሚደረግ ተጨማሪ ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
2ኛ) ፌዴሬሽኑ ማህበራዊ የሆኑ ኃላፊነቶቹን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተወስኗል፤
በዚህ መሰረት፡-
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ማቋቋሚያ እንዲሆን የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ ለክልሉ መንግስት በስፍራው በአካል በመገኘት እንዲሰጥ የወሰነ ሲሆን፤
በተያያዘ መረጃ በአፋር ብሄራዊ ክልል ክረምቱን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው ድንገተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖቻችን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ‹‹ለወገን ደራሽ ወገን ነው›› በሚል ተነሣሽነት የብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ ለክልሉ መንግስት በስፍራው በአካል በመገኘት እንዲሰጥ አክሎ ወስኗል፡፡
ይህ የገንዘብ ድጋፍ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተወሰነው የስፖርታችን በተለይም የአትሌቲክሱ መሰረት ህዝብ በመሆኑና ያለህዝባዊ መሰረት አትሌቲክሱን ማስፋፋትና ማሳደግ እንደማይቻል በማመን፣ እንዲሁም ያለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት አኳያ ፌዴሬሽኑ ካለው ውስን ሃብት ቀንሶ ለህዝባችን አለኝታነቱን በተግባር ለመግለፅ ያሳለፈው ውሳኔ ሲሆን ይሄንን ፈር ቀዳጅ ተግባር ሌሎች ተቋማት፣ ማህበራትና የስፖርቱ ቤተሰቦች ይከተሉት ዘንድ አርአያ በመሆን መጀመሩን ያስታውቃል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን!