Connect with us

ኮረናን አብዝተን የናቅነው፤ እኛ ማን ሆነን ነው?

ኮረናን አብዝተን የናቅነው፤ እኛ ማን ሆነን ነው?
Photo: Fortune | The Ministry of Transport has deployed personnel to assess the implementation of COVID-19 safety measures across the transport sector.

ጤና

ኮረናን አብዝተን የናቅነው፤ እኛ ማን ሆነን ነው?

ኮረናን አብዝተን የናቅነው፤ እኛ ማን ሆነን ነው?

(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

እነሆ እንደተፈራው ኮረና ከመንሰራፋቱ የተነሳ ጭንቅላታችን ላይ ጎጆ እየሰራብን ነው፡፡ ትላንት ቁጥር ብቻ ስለነበር እና ብዙዎች የታመሙትን እንኳን በአካል ባለማየታችን ስንዘናጋ የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጠን ነበር፡፡ ዛሬ ቁጥሩ ከመጨመር ባሻገር ቤታችንን ማንኳኳት ቢይዝም አሁንም ምክንያት እየደረደርን በዝንጉነታችን ቀጥለናል፡፡

ትላንት ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ በተደረገ ሪፖርት መሰረት በ24 ሰአታት ብቻለ19 ሺህ 747 ሺህ ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 1 ሺህ 460 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በዕለቱ 16 ሰዎች በኮሮና ሞተዋል፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን ከኮሮና ጋር ተያይዞ የሟቾች ቁጥር እስከትላንት ድረስ ብቻ 544 ደርሷል፡፡ በምርመራም 31 ሺህ 336 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡

ኮሮና ምክንያት ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነን፡፡ አዋጁ ይኑር እንጂ አፈጻጸሙ የወረቀት ላይ ጌጥ ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ ለምን ቢባል አዋጁ የሚከበር አልሆነማ፡፡ በአዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎች በማወቅም ባለማወቅም መጣሳቸው አሳሳቢ ነው፡፡ ባለማወቅ ያልኩት እንዲያው ጨዋ ለመሆን እንጂ ሆን ተብሎ ህግ የሚጣስበት ሁኔታ በስፋት እየታየ ነው፡፡

የአፍና የአፍንጫ ማስክ የማድረግ ግዴታን የዘነጉ ብዙ ሰዎች በዋና ከተማዋ አዲስአበባ ማየት እንግዳነቱ ከቀረ ቆየ፡፡ ከአንድ ወር በፊት ፖሊስ እንዲህ አይነቶችን ግለሰቦች በህግ መጠየቅ ጀምሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ምን እንደሆነ ምክንያቱ ባይታወቅም መጠየቅ ቆሟል፡፡ እንደድሬደዋ ባሉ ከተሞች መዘናጋቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት በጭፈራ ቤቶችና በመጠጥ ቤቶች ማናቸውንም የመጠጥና መዝናኛ አገልግሎት መሰጠት የተከለከለ ነው፡፡ የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ በራሱ መንገድ በሰበሰበው መረጃ በአዲስአበባ ብቻ ከ10 ያላነሱ የጭፈራ ቤቶች መደበኛ ስራቸው ላይ ናቸው፡፡ ጭፈራ ቤቶቹ በፊት ለፊት የመኪና ግርግር በማስቀረት በጓሮ ደንበኞቻቸውን የሚያስተናግዱበት ዘዴ ፈጥረው ስራቸውን እያከናወኑ ነው፡፡ አንዳንድ የጸጥታ ሀይሎች ከእነዚህ ተቋማት ጋር በመሞዳሞድ ባላየ የሚያልፉበት አሳዛኝ ሁኔታ የእለት ክስተት ሆኗል፡፡ አንዳንድ የፖሊስ አባላት እነዚህን ቤቶች አጥምደው በማሰስ ጥሩ የገቢ ምንጭ ማግኛ ወደማድረግ ተሸጋግረዋል፡፡

ሌሎች ቡና ቤቶች፣ ድራፍት ቤቶች ወይንም መጠጥ ቤቶች ወደተለመደ ስራቸው ከተመለሱ ቆዩ፡፡ በአንድ ጠረጼዛ ላይ ከሶስት ሰው በላይ እንዳይስተናገድ የተጣለው ገደብ አሁን አሁን የሚያስታውሰውም የለም፡፡ እጅብ ብሎ መቀመጥ፣ መዝናናት፣ መብላት፣ መጠጣት እንደወትሮው ቀጥሏል፡፡

በታወቁ ስጋ ቤቶች ጭምር ጥሬ ስጋ አሁንም ይቆረጣል፡፡ ቀድሞ ደበቅ የማለት ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

በሚገርም ሁኔታ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች በኮረና በየቀኑ እየተያዙ እና እየሞቱ ያለውን እውነታ ክደው “ውሸት ነው፣ ፖለቲካ ነው…” የሚሉ አዘናጊዎችንም በየመንደሩ በብዛት እያየን ነው፡፡

እንግዲህ ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፤ እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ” ይልሃል ይህ ነው፡፡ ሕዝቤ በጊዜ ነቅተህ ራስህንና ቤተሰብህን መጠበቅ ካልቻልክ በጣም በቅርቡ በራሱ በኮሮና ቁንጥጫ ምክር የሚለገስህ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ያውም ኮሮና በምክር ካለፈህ ነው፡፡ እስከወዲያኛው ሊያሰናብትህ እንደሚችልም አለመዘንጋት ብልህነት ይሆናል፡፡ እናም በአጭሩ “መዘናጋቱ፣ በሕይወት መቆመሩ ይብቃ!..እንንቃ!.. “ለማለት ነው፡፡ ደህና ሰንብትልኝ!

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top