Connect with us

በጠቅላዬ ጉዳይ ተስፋና ቁዘማዬ!

በጠቅላዬ ጉዳይ ተስፋና ቁዘማዬ!
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

በጠቅላዬ ጉዳይ ተስፋና ቁዘማዬ!

በጠቅላዬ ጉዳይ ተስፋና ቁዘማዬ!
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

በእውነቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት ያነበብኩት ሪፖርት አስደንግጦኛል።

በተቃራኒው ማምሻውን በመገናኛ ብዙሃን የተለቀቀው የአዲስአበባ የአረንጓዴ ልማት በውስጤ የለኮሰው ደስታ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሮብኛል።

በአጭሩ ገጣሚ በቀለ ወያ እንዳለው ሆኛለሁ።
“እንዳልቃወመው ፣ በግማሽ ደግፌ
ደግሞ እንዳልደግፈው ፣ ጥርጣሬ አቅፌ
ማቶ ሆኜ ቀረሁ ፣ በመሀል ወፈፌ”

የሰብዓዊ መብት ኮምሽኑ ምንድነው ያለው? በቅርቡ በኦሮሚያ ኢ- ሰብአዊ ጥቃት በተፈፀመባቸው አካባቢዎች ነፍሰ ገዳዮቹ አሁንም ዛቻና ማስፈራሪያቸውን ቀጥለዋል። ዜጎች ተገድለው፣ ተፈናቅለው፣ ንብረታቸው ወድሞ እያነቡ ባሉበት በዚህች አስቸጋሪ ወቅትም “አካባቢያችንን ለቃችሁ ውጡ” እየተባሉ ነው። ሪፖርቱ እንዲህ ይላል።

“…በዶዶላ ከተማ የሚገኙ የጉዳቱ ተጠቂዎች እንዳስረዱት ከግጭቱ በኋላ ማለትም በሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ60 ሰዎች በላይ ስማቸውን በመዘርዘር ከተማውን ለቀው ካልወጡ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ያዘለ ወረቀት መሰራጨቱን፣

● በባቱ ከተማ ተጎጂዎች አሁንም ከተማውን ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስፋራሪያ በስልክና በአካል እየደረሳቸው መሆኑን፣

● ሻሸመኔ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር ካላመጣችሁ አሁንም ንብረታችሁን እናቃጥላለን እንዲሁም እንገላችኋለን በማለት ማስፈራሪያ የሚደርሳቸው ሰዎች እንዳሉ እና፣

● በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በመንግስት የፀጥታ አካላት ሳይቀር ሰዎች እየተደበደቡና ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን (ለምሳሌ፡ በቡራዩ ከተማ በተለይ ከታ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ እንዲሁም በጉና ወረዳ ነገሌ ከተማ) ለማወቅ ተችሏል፡፡..”

እነዚህ ገድለውም፣ አፈናቅለውም፣ የንፁሃን ንብረት አውድመውም ያልረኩ አካላት እነማን ናቸው? ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለዋል እየተባለ የተነገረው ውስጥ እነኚህ ነፍሰ ገዳዮች እንዴት ሳይካተቱ ቀሩ? መንግስት አሁንም ሌላ ዙር ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት እነዚህን ወገኖች ይታደጋቸዋል ወይንስ እንደከዚህ ቀደሙ ውድመት ከደረሰ በኋላ ነጠላ ዘቅዝቆ ሐዘን ይቀመጣል?

በሌላ በኩል በጠ/ሚኒስትር ዐብይ ፊትአውራሪነት በአዲስአበባ በአራት ኪሎ፣ በእንጦጦ አካባቢዎች የተሰሩ የአረንጓዴ ልማቶችና በብሔራዊ ቤተመንግስት ሊሰራ የታቀደው ሙዚየም ስላለው ጠቀሜታ እየተረኩልን ነው። ልማት አይጠላም፤ የተሰራው ብቻ ሳይሆን በጎ ሀሳቡም በራሱ የሚያጠግብ ነው። ግን የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር የሆነው የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ጉዳይ አስተማማኝ መልስ ባላገኘበት በዚህ ወቅት ቁሳዊ ልማቱ ገኖ መውጣቱ ብቻውን ፋይዳው ምንድነው የሚለውን አብሮ መመለስ ይገባል።

በአሁን ሰአት በኦሮሚያ በኮምሽኑ በተለዩ አካባቢዎች የሚታዩና የሚሰሙ አዳዲስ የሽብር ስጋቶችን በአስተማማኝ መልኩ ለመቅረፍም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደአረንጓዴ ልማቱ ሁሉ ክትትላቸውን በማጠናከር ነፍሰገዳዮችን ከየአካባቢው የመጠራረጉን ከባድ ግዳጅ በአቸናፊነት ሊወጡ ይገባል።

ህብረተሱም በየአካባቢው ተደራጅቶ ሰላሙን እንዲያስጠብቅ በማንቃትና በማደራጀት ረገድም የሲቪክ ማህበራት ወደእነዚህ አካባቢዎች ፈጥነው ሊንቀሳቀሱና የበኩላቸውን እገዛ ሊያደርጉ ይገባል።

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top