ቁማርተኛው እድርና በሞት የሚከስረው ሳይኾን በሞትኩ የሚያተርፈው የእድሩ ኮሚቴ
****
ከስናፍቅሽ አዲስ
ጠቅላዩ አልተቻሉም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ቆይታ ያነሷቸው ሀሳቦች ውሃ ያነሳሉ፡፡ ምክራቸውን ለሰማ ፓርቲ ህዝብ አስይዞ ቁማር እንዴት እንደሚቀፈው እገምታለሁ፡፡ አብልጣ ያስገረመቺኝ ግን የጠቅላዩ የህወሃት መሪዎችን የገለጹባት ንግግር ናት፡፡ እድር፤
እድርን አቅልለውታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የወቀሱ ሰዎች አሉ እነሱ ምን ያህል የእነ ጌታቸው ረዳ ተቃራኒ እንደቆሙ አይቻለሁ፡፡ ለእኒያ ጉምቱ ባለስልጣናት የእድር ማእረግ መግፈፍ ጭካኔ መስሎኛል፡፡
እርግጥ ነው እንደ ባህላችን እድር የሚባለው ማህበራዊ ተቋም ይቀብራል፤ ጉድጓድ ይቆፍራል ንፍሮ ያዘግናል ያላቅሳል፡፡ እዚህ ድረስ የፌዴራሊስ ሃይሎች አውራ ነኝ ባይዋ ህወሃት አንጋፋ መሪዎች የእድርን ጠባይ ይይዛሉ፡፡ ግን እድር ደግሞ አይገድልም እንደውም ሟች ባልኖረ ብሎ ሞትን የሚጠላና የሚፈራ በሞት የሚከስርም ነው፡፡ እነኚህ ጉምቱ ባለስልጣናት ግን በሞት አይከስሩም ለማትረፍ ይደክማሉ እንጂ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገባቸው እና እኛ ያልገባን የእድሩ ዳኛ ነገር ነው፡፡ ሌላው ሰው የእድሩ ዳኛ ከእድሩ ኮሚቴ አይለዩም ብሎ ሲያስብ እሳቸው ግን ህዝቡ ዶክተር ደብረ ጽዮንን በማገዝ አብሮ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እንዲያ ከሆነ ደብረጺ ፖለቲካዊ ሀሳባቸው የሚታማ አይደለም ማለት ነው፡፡
የአንጋፋዎቹን ቡድን እድር ብሎ መግለጽ ብቻ ሳይሆን እድሩ እንዴት የሚያሳዝን እድር እንደሆነ በማሳየት በኩል ዶክተር አብይ ሁሌም እንደተሳካላቸው ነው፡፡ መቀሌ የመሸገው ቡድን መከራ ሲመጣ ያስታወሰውን ህዝብ ጉያ ገብቶ እንኳን በሰላም እንዲኖር ብዙ መስዋዕትነት በከፈለላት ሀገር ጥቅሙ እንዲጠበቅና ብሔራዊ ድርሻውን እንዳያጣ በማድረግ በኩል የሚጫወተትን ሚና ያየ ሰዎቹ ከኢትዮጵያ በላይ ትግራይ ላይ እንዴት እንደሚጨክኑ መረዳት ይቻላል፡፡
እንኳን ሞላው ትግራይ ሁሉም የህወሃት አባል የእድሩ መንፈስ ውስጥ የለም እድሩን በሚመለከት ፈንቅሎች እንዳሉት ወርዶ ወርዶ የሰፈር እድር የጎረቤት ስብስብ የመንደር ቡድን ሆኗል፡፡
ብዙው ሰው የሚፈልገው አይጧን ማሳደድ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙትን ነገር ወርውረው አይጧን ግንባሯን እንዲሏት ያልተመኘም ያልመከረም የለም፡፡ ሰውዬው መታገስን መገለጫቸው አድርገዋል፡፡ ምጣዱ ከሚሰበር አይጧን እንዳሻት ብትሆን መልካም ነው በማለታቸው ዛሬም የአይጧ ጉዳይ የመድረክ ማሞቂያ ከመሆን አልዳነም፡፡
የእድሩ መጨረሻ ምን ይሆናል የሚለው የብዙ ሰው ጥያቄ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ እንደ ግል ንብረት ድርሻዬ ነው ብሎ ድርቅ ማለት የፖለቲካ ቀልድ ቢሆንም አሁን እድሩ ጉዱ የፈላበት ይመስላል፡፡ ያ እስኪሆን ደግሞ ለእድርተኞቹ ትቶ ያንን ደግ ህዝብ እየናፈቁ ውጤቱን መጠበቅ ነው