ኦሞን ከቁጣው መልስ፤
የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ አዞዎች ጉጉት
****
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ያደረገውን ቆይታ እየተረከልን ነው፡፡ ወደ ኦሞ ወንዝ ወርዶ የተመለከተውን ድንቅ ነገር ኦሞን ከቁጣው መልስ ሲል እንዲህ ያካፍለናል፡፡)
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
ኦሞ እስክወጣበት ድረስ ዝምታው ገርሞኝ ነበር፡፡ ደርባባ የመሰለው ወንዝ ውስጡ ትንታግ ኾነ፡፡ ጀልባችን ባለ ሞተር አይደለችም፡፡ ሙርሲዎቹ የብሔራዊ ፓርኩ ስካውቶች የወንዙ ዳርቻ ብዝሃ ህይወት ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ቆሞ የከረመውን ጀልባ አስነስተው በእጅቸው እየቀዘፍ፤ ሩቅ ተጓዡን ወንዝ በረዣዥም ብትር ወደ ኋላ እየገፉ ወደ ፊት ወሰዱን፡፡
ኦሞ ሞልቷል፡፡ ኦሞ የአፍላግ ህብረት ነው፡፡ ግቤ ከዋቤ ተደምሮ ጎጀብን በማከል የፈጠረው ግዙፍ ወንዝ፡፡ ኦሞ የስልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ ቅድመ ታሪክ የነበረ የአርኪዎሎጂ ስፍራ፡፡ ኦሞ የብዝሃ ባህል ወዝ ነው፡፡ ከኛንጋቶም፣ ከሙርሲ፣ ከዲዚ የሚቀዳ፡፡ የጉራጌን ደጋ ምድር ከኦሞ ሸለቆ የሚያዋህድ፣ የካፋን ጥቅጥቅ ደኖች ከሜዳማዎቹ የካሮ መንደሮች የሚያስዋውቅ፡፡
አዞዎቹ አሰፍስፈዋል፡፡ የዛሬን አያድርገውና የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ሲመጣ መንገድ አልነበረም፡፡ የኦሞ ስነ ምህዳር ለሁለት ተከፍሎ ወንዙ ድረስ በአንድ መኪና የመጣ ወንዙን ቀዝፎ ተሻግሮ ከወንዙ ማዶ በሌላ መኪና ይጓዛል፡፡ ቀደምቶቹ እንዲህ ባለው ፍቅር የጠበቁትን ብዝሃ ህይወት ሳስብ እገረማለሁ፡፡ ያን የመስዋዕትነት ክብራቸውን ለመዘከር ትናንትናቸውን ፍለጋ መጥቻለሁ፡፡
ኦሞን ስናጋምሰው ቁጣውን አበረታው፡፡ ከሚቀዝፉት ጓዶቻችን ጉልበት በላይ ሆነ፡፡ በረታብን፡፡ ፍርሃቱም በረታ፡፡ አዞው አሰፈሰፈ፡፡ የወንዙ አዙሪት ውስጥ ላለመግባት ትግሉ ቀጠለ፡፡ ያ ዝምተኛ ወንዝ እንደ አንበሳ ተገማሽሮ አገሳ፡፡
ኦሞን ከመቶ ዓመት በፊት ያሰሱት የፈረንሳይ አርኪዎሎጂዎች ብዙ ነገር እንዳለው ተረዱ፡፡ የዛሬ ሃምሳ አመት አካባቢ ግን ከ2.5 ሚሊዮን አመት በሚቀድም እድሜ የሰው ልጅ ቅሪቶች ሲገኙበትና የሸለቆው ዳርቻ የቀደመ ስልጣኔ ምድር መሆኑ ሲረጋገጥ የዓለምን ትኩረት ሳበ፡፡
ትኩረቴን ኦሞ ላይ አደረግሁ፡፡ ጉልበቱ ጨመረ፡፡ መውጣት ወደማይቻልበት ክፉ ስፍራ ሊያግዘን የቆረጠ ይመስላል፡፡ ከሞት ጋር ወንዝ ላይ ተጋፈጥን፡፡ የካሜራ ባለሙያዬ በሪሁን ታደለ ከሞት በፊት ያለ ትዕይንት ለማስቀረት ያሰበ ይመስላል፡፡ እየተንቀጠቀጠ የሚሆነውን አስቀረ፡፡ የመጨረሻ እድላችንን ሞከርን የጀልባዋ ፊት ወደ ዳርቻው ዞረ፡፡ ኦሞን ለመሻገር እድል እንዳለን አመንን፡፡
ፍርሃቱ ተከትሎናል፡፡ ፍጥነት ካልጨመርን ዳግም ወደሚያስፈራው አዙሪት ልንመለስ እንችላለን፡፡ እነኛ ሙርሲዎች ደራሹን ወንዝ ተፋለሙት፡፡ ወደ ዳርቻው ወጣን፡፡ ቀድሞ የወጣው ወጣት ገመድ ወርውረንለት ጀልባዋን ከግንድ ጋር አሰራት፡፡ ተሻግረን ስንወርድ ሁሉን የሚያስረሳ ውበት ገጠመን፡፡ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ሌላ ገጽታ፡፡