ለስልጣን ሲባል ኢትዮጵያዊነታችን ተወስዶ ማንነታችን ብሔር እንዲሆን ተደርጓል ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለጹ ።አሁን መገዳደል ላይ የተደረሰው በውሸት ማንነት እንደሆነም አስታወቁ።
አቶ ኦባንግ ሜቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፣ ጥቂት ሰዎች ተበድለናል ብለው ተነስተው ጫካ ገቡ። ከጫካ ሲወጡ እና ስልጣን ለመያዝ ስትራቴጂ ሲነድፉ ህዝቡን መከፋፋል ላይ አተኮሩ። የጋራ የሚባል ነገር ሁሉ የእነርሱ ጠላት መሆኑን አስቀመጡ። እኩልነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ጥሩዎቹ የአብሮነት ታሪኮች ተሰወሩ። ትልቁን ነገር የኢትዮጵያውያንን ማንነት ከህዝቡ ነጠቁ።
“ፖለቲካ ጨዋታ ነው። ጨዋታው ደግሞ ከማሸነፍ ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን ማሸነፍ ሲታሰብ አገር እና ትውልድን ከመጉዳት አንፃር መሆን አልነበረበትም” ያሉት አቶ ኦባንግ፣ በኢትዮጵያ ግን ለማሸነፍ ሲባል አገር የምትፈርስበት እና ትውልድ የሚጎዳበት መንገድ መመረጡን አስታውቀዋል።
የምንገዳደልበት የተሰጠንን የውሸት ማንነት ተቀብለን ነው። እውነቱ ግን ከዚህ የራቀ ነው ያሉት አቶ ኦባንግ፣ አያቶቻችን ብሔርን ሳያስቡ በፍቅር ተጋብተዋል። የሰውን ብሔር ሳያውቁ ሰው በመሆኑ ብቻ አግብተው ልጅ መውለዳቸውን አመልክተዋል። በፊት ዕቁብ፣ ዕድር፣ ቡና መጣጣት፣ በአንድ ትሪ ያለምንም ድንበር መብላት
ነበር። ሁሉም ከሰውነት አንፃር ይታይ ነበር። አሁን ይሄን ማንነት ተነጥቀናል። እከሌ ያንተ ጠላት ነው። እከሌ ይሄንን በደል ፈፅሞብሃል መባሉ በብዙዎች ውስጥ ገብቶ የአብሮነት ስጋት መፍጠሩን አስታውቀዋል።
“ፈጣሪ ሰውን ፈጥሯል። ሰው ያለሰው መኖር አይችልም። ዝሆን ስትወልድ ብትሞት፤ የተወለደው የዝሆን ግልገል ያለማንም ድጋፍ ወዲያው መሄድ እና ማደግ ይችላል። የተወለደው የዝሆን ልጅ ራሱን ለመመገብ አያዳግተውም። ሰው ግን ተወልዶ ቢጣል ያለሰው ማደግ አይችልም። ቆሞ ከመሄዱ በፊት መታቀፍ አለበት። መብላት እስከሚጀምር የሚያጎርሰው ይፈልጋል። ሰው ያለሰው አይሆንም። ሰው ከእንስሳት የተለየ ፍጥረት ነው። ሰው ዕውቀት፣ ኃይል እና ኃላፊነት ያለው ፍጥረት ነው። ሰው እንደ ሰው ሊታሰብ ይገባል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከህገመንግሥቱ ጀምሮ ሰው የታየው እንደሰው ሳይሆን እንደ ብሔር መሆኑን አመልክተው፣ ህገመንግሥቱ እኛ ኢትዮጵያውያን ሳይሆን “እኛ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች “ይላል። ለዚህ ነው በብሔር ላይ በመንጠልጠል ‹‹ከዚህ ቦታ ውጡልኝ›› ማለት የተጀመረው ብለዋል። ይህ በፈጣሪም የተጠላ ነው። ፈጣሪ ሰውን ሲፈጥር ወንድና ሴት ያደረገው ለአብሮነት ነው። ያለአብሮንት ሰው መኖር አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።
ህገመንግሥቱ እስካለ ድረስ የንብረት ውድመት እና ሞት እንደማይቆም ስጋታቸውን የሚገልጹት አቶ ኦባንግ፣ ትውልዱ ኢትዮጵያ የእርሱ መሆኗን አልተረዳም። ወጣቱ በየቦታው ያለው ሀብት በሙሉ የራሱ መሆኑን አልተገነዘበም ብለዋል። ሁሉን ነገር ለኔብቻ ማለት የመጣው በተረጨው መርዝ ሳቢያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“በኃይለስላሴ ጊዜ ‹‹በህግ አምላክ›› ሲባል ከመሳሪያ በላይ ህግ ይፈራ ነበር። ያ አስተሳሰብ እንዲመጣ እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት መውሰድ አለበት። ብሔርተኞቹ ልጆቻቸውን ስለብሔር ከማስተማር ይልቅ ስለሰውነታቸው እንዲያስተምሩ የድጋሚ ቀረፃ ሥራ መሠራት አለበት። ትውልዱ መታደስ አለበት። የአባይ ግድብ ሲሞላ ራሳችንን በፍቅር፣ በሰብዓዊነት እንሙላ። ውስጣችን የፍቅር ድርቅ፣ የአብሮነት ድርቅ፣ የሰላም ድርቅ ሙሉ ለሙሉ ድርቅ በድርቅ ነን። ችግር መኖሩን ተቀብለን ትምህርት ቤትም፣ የእምነት ተቋም ላይም መሠራት አለበት” ብለዋል።
ችግሮቻችን ቀደም ብሎ የተዘራው ዘር ውጤቶች ናቸው። የተዘራው የእኩልነት፣ የአብሮነት፣ የሰላም እና የአገር መጥቀም ዘር አይደለም። ስለዚህ በፊት የተዘራውን አሁን እያጨድን ነው ያሉት አቶ ኦባንግ፣ ኬኒያ ውስጥ ‹‹ኬኒያ ትፍረስ›› የሚል የለም። በአሜሪካም ሆነ በሌላው አገር ሰዎች የሚናገሩት እና የሚያስቡት ስለአገራቸው ዕድገት፤ ዜጎቻቸውን በደስታ ስለማኖር፤ ስለቀጣዩ ትውልድ እንጂ አገር ስለማፍረስ የሚያስብም ሆነ የሚናገር የለም። ማፍረስ የሚለው ቃል ራሱ በጣም አደገኛ ነው። ይህ ሰዎች ከራሳቸው ጋር የሚነጋገሩት ጥሩ አለመሆኑ የፈጠረው ችግር ነው። ሰዎች የአገር ፍቅር እንዳይኖራቸው ተቀርፀዋል፣ ይህም የችግሮቻችን ምንጭ እንደሆነም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012