– ከ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ውጪ ያሉ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲሸጋገሩ ወሰነ
በዘንድሮው ዓመት ከ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጪ ያሉ መደበኛ ተማሪዎች በሙሉ ወደቀጣዩ የክፍል ደረጃ እንዲሸጋገሩ መወሰኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የቀጣይ ዓመት የትምህርት ምዝገባ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ሳምንት ድረስ እንደማይደረግ ተገለጸ።
የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትናንትና በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ በተማሪዎች ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ የክልል ትምህርት ቢሮ እና የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች ውይይት አድርገዋል። በውይይቱም እስከ 7ኛ ክፍል ያሉ እና ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች በቀጣይ ዓመት ትምህርት ሲጀመር የ45 ቀን ማካካሻ የክለሳ ትምህርት ወስደው ወደቀጣዩ ክፍል እንዲሸጋገሩ ተወስኗል።
የ8ኛ እና የ12 ክፍል ተፈታኞች ደግሞ በ2013 ዓ.ም የማካካሻ ትምህርታቸውን ከወሰዱ በኋላ ለፈተኛ እንደሚቀመጡ አስታውቀው ፣ የ12 ክፍል ፈተናን በኦንላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረጉ መሆኑን ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን አመልክተዋል ።
“የቀጣዩ ትምህርት ዘመን የኮሮና በሽታ ስርጭትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚጀመርበትን ቀን መንግስት ይወስናል። ትምህርት የሚጀመርበት ቀን እንደታወቀም ሁሉም ተማሪዎች ለአንድ ወር ተኩል ያክል በኮሮና ምክንያት የተቋረጡ ትምህርቶች ማካካሻ ተሰጥቷቸው በነጻ ወደቀጣዩ ዓመት እንዲሸጋገሩ ይደረጋል” ብለዋል።
በተለይ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴት ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታ ላይመለሱ የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሚኖር ስጋት መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ስጋቱን ለመቀነስ እና ቅድሚያ ተማሪውን ወደትምህርት ቤት ለማስገባት ሁሉም በነጻ ወደቀጣዩ ክፍል እንዲሸጋገር መደረጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ተማሪው ወደትምህርት ገበታው ከተመለሰ በኋላ ደግሞ ስለጥራቱ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ፤ ወደቀጣይ ዓመት ተማሪዎች በነጻ ያልፋሉ ቢባልም እስከ ነሐሴ መጨረሻዎቹ ድረስ ግን ምንም አይነት የትምህርት ቤት ምዝገባ ማድረግ አይቻልም። በመሆኑም ምዝገባ የሚያደርግ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ቤት ካለ ህገወጥ ተግባር መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ህገወጥ ምዝገባ የሚያካሂዱት ላይ ቁጥጥር በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል።
የቀጣይ ዓመት ትምህርት ምዝገባ ከነሐሴ መጨረሻዎቹ በኋላ የሚደረግ መሆኑ ለኮሮና መስፋፋት ከሚደረግ ጥንቃቄ ጋር ተያይዞ የተወሰደ መሆኑን የገለጹት ሚኒስረትሩ፤ የቀጣዩ ዓመት ምዝገባ ሲጀመር ማንኛውም ትምህርት ቤት በ2012 ዓ.ም ከሚያስከፈለው ዋጋ በላይ መጨመር እንደማይችል ገልጸዋል። የኮሮና በሽታ ወላጆች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሳደረ በመሆኑ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻል አስታውቀዋል።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም)