Connect with us

ታከለ ኡማ ከንቲባነታቸው ለማን ነው?

ታከለ ኡማ ከንቲባነታቸው ለማን ነው?
Photo Facebook

ፓለቲካ

ታከለ ኡማ ከንቲባነታቸው ለማን ነው?

ታከለ ኡማ ከንቲባነታቸው ለማን ነው?
(ጫሊ በላይነህ ~ ድሬቲዩብ)

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። እሰየው ነው።በቅድሚያ የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድን አመሰግናለሁ። ለምን? መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማስታገስ የግዙፍ ኘሮጀክት ዕቅድ ሲልክላቸው እንደባለሀብት፣ እንደነጋዴ የአዋጪነት ጥናት ላካሂድ የሚል የቢዝነስ ስሌት ውስጥ አልገቡም። ያልገቡት ሰርቶ ማትረፍ የነጋዴ ባህርይ ስለሌላቸው አልነበረም። ሼህ ሙሐመድ እንደማንኛውም ነጋዴ ያው ነጋዴ ናቸው። ህዝብ ተቸገረ ሲባሉ ግን ያ ቡቡ ልባቸው ይደነግጣል፤ ነጋዴነታቸውን ይረሱና ከህዝብ የሚቀድም ነገር የለም ብለው ይነሳሉ። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ አነሳስ ይኸው በጎ ፈቃደኝነት ነው። ሩህሩህነት ነው።

የሀሳቡ ጠንሳሾች መሪዎቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እና ኢነኢንጅነር ታከለ ኡማ ህዝብ ቢያንስ በልቶ የሚያድረው ዳቦ እንዳያጣ ማሰባቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። ግን ደግሞ ህዝብ በዳቦ ብቻ አይኖርም። ቆንጆ መናፈሻዎችን መገንባት ብቻ እህል ውሀ አይሆነውም። መጠለያም ይፈልጋል። በዚህ ረገድ መሪዎቻችን አዲስአበባ ላይ ተፈትነው ወድቀዋል።

እጣ የወጣባቸው የ13ኛ ዙር ኮንደምኒየም እና የሁለተኛ ዙር 40 በ60 ቤቶች በሺ የሚቆጠሩ እድለኞች እጣ ከወጣላቸው ከ16 ወራት በኋላም ቤታቸውን መረከብ አልቻሉም። “ኮዬፈጪ የኦሮምያ መሬት ነው፤ ማን አባቱ ይገባበታል” በሚል የፎከሩ ፖለቲከኞች መንግሥት እጁን ጠምዝዘው አፉን እንዲለጉም ማድረጋቸው ብዙዎችን እንዳስገረመ አለ። ባለእድለኞች ቤታቸውን ባልተረከቡበት በዚህ ወቅት ክቡር ምክትል ከንቲባው በህዝብ መዋጮ የተሰሩ የኮንደምኒየም ቤቶችን ወደማደል መሸጋገራቸውን የማህበራዊ ድረገፁ ትኩስ ወሬ ሆኗል። እሳት በሌለበት ጢስ አይኖርምና የተነገረው አሳማኝ በሆነ መልክ ማስተባበያ እስካልተሰጠበት ድረስ ማመን ግድ ይሆናል።

በተጨማሪም በያዝነው አመት መጀመሪያ ገደማ ለመምህራን እና ለመንግስት ሠራተኞች በአነስተኛ ዋጋ ይከራያሉ የተባሉ የአራት ኪሎ ኮንደምኒየም ቤቶች ለለገሀር ኘሮጀክት ተነሺዎች እንዲተላለፉ ተደርጓል። ምስኪኑ መምህር ግን አንድ ቀን ቤቶቹ ተጠናቅቀው አገኝ ይሆናል ብሎ በተስፋ ቤቱ ተቀምጧል። ቃል የእምነት እዳ ነው። መንግሥት ቃሉን ማክበር በተሳነው ቁጥር በቀጣይ ቃሉን የሚሰማ ህዝብ ወደማጣት ሊያሸጋግረው ይችላል። እንዲህ አይነቱ ጥቃቅን መሰል ስህተት ውሎ አድሮ በህዝብ መናቅን ያስከትላል።

ታከለ ኡማ ከንቲባነታቸው ለማን ነው?

 

በእርግጥም ለህዝብ አስቦ ለዳቦ አቅርቦት የተሟሟተ መንግሥት የህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት በሆነው የመኖርያ ቤት ችግር ቁማር ውስጥ ይገባል ብዬ ለማሰብ ይቸግረኛል። ምናልባት ይኸ እሳቤዬ ለጠ/ሚ ዐብይ የለውጥ አመራር ያለኝ በጎ እሳቤ የፈጠረብኝ ግርዶሽም ሊሆን ይችላል። ግን እንደተባለው ህዝብ ሳይተርፈው በየወሩ ቆጥቦ የሰራው ቤት ለግለሰቦች ባልተገባ መንገድ ታድሎ ከሆነ ለለውጥ አመራሩ ትልቅ ኪሳራ ነው። አንድ መንግሥት የህዝብ አመኔታን ከማጣት በላይ ምንም አይነት ኪሳራ ሊደርስበት አይችልምና።

ይኸን ስህተት ደግሞ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ብቻ ማስታቀፍ ተገቢ አይደለም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቀት ውጪ ህገወጥ የቤት እደላ እና የመሬት ወረራ በአዲስአበባ ይፈፀማል ተብሎ አይገመትም። እናም ለልማቱ ብቻ ሳይሆን በጥፋቱም ተጠያቂነቱ የጋራ መሆኑን መሪዎቻችን ሊዘነጉት አይገባም።

እናም መሪዎቻችንን አጥብቄ የምጠይቀው በመሬት ወረራው እንዲሁም ከእጣ ውጪ የቤት እደላ ጉዳይ እየሆነ ያለውን በግልፅ እንዲነግሩን ነው።

በተጨማሪም መሪዎቻችን ከምር ለህዝብ ጥቅም የቆሙ ከሆነ ያለአንዳች ማንገራገር በአዲስአበባ የኮንደምኒየም እጣ ወጥቶላቸው ቤታቸውን መረከብ ላልቻሉ ነዋሪዎች ቤታቸውን በፍጥነት እንዲያስረክቡ ነው። መሪዎቻችን ህዝብ ታግሎ፣ ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ ወደፊት እንዲመጡ ያደረጋቸው ለምን እንደሆነ በሁለት ዓመት የምኒሊክ ቤተመንግሥት ቆይታ ይዘነጉታል አልልም። ህዝብ እድሉን የሰጣቸው የትላንቱን ብልግና በመልካም ሥራ እንዲያድሱ እንጂ አዳዲስ ብልግናዎችን፣ ሕገወጥነትን እንዲያሳዩ አለመሆኑን በግሌ ላስታውሳቸው እወዳለሁ።

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top