Connect with us

ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምርጫ ላካሂድ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምርጫ ላካሂድ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምርጫ ላካሂድ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ምርጫ ላካሂድ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረገ

(ሙሉ መግለጫው እነሆ)

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲፈጸምለት ለቦርዱ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በመላ አገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈፀም ስልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 102 (1) ላይ ተደንግጓል ፡፡ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የቦርዱን ስልጣን እና ሀላፊነት የወሰነው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በአንቀጽ 7.1 ይህ የቦርዱ ስልጣን በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ምርጫዎች እና ህዝበ ውሳኔዎችን በሙሉ እንደሚሸፍን በተብራራ ሁኔታ ገልጾታል።

በተጨማሪም የቦርዱን የስራ ሃላፊነቶች በተለያየ ሁኔታ በዝርዝር በሚገዙት ህጎች ማለትም በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እንደተደነገገው በማንኛውም የምርጫ ዑደት የሚፈጸሙ ዋና ዋና ክንዋኔዎች ማለትም የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ ለምርጫ የሚወዳደሩ የፓለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣የምርጫ አስፈፃሚዎችን መልምሎ ማሰማራት፣ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ ምርጫውን ከተጽእኖ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም በመጨረሻም የውድድሩን ውጤት አረጋግጦ ለህዝብ ይፋ ማድረግ እና የመሳሰሉት ከማንኛውም የመንግስት ተቋም በተለየ ለቦርዱ የተሰጠ እና ከማንም አካል ጋር የማይጋራው ህጋዊ ስልጣኑ ነው፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ እያለ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባገራችንም በመከሰቱ ምርጫውን ለማስፈፀም ሲያካሂዳቸው የነበሩት ስራዎች እንደተስተጓጎሉ ይታወቃል፡፡ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ መከሰቱ እንደተረጋገጠ ሁናቴውን መገምገም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ 6ኛውን አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ሲል ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ የማይቻል በመሆኑን ወስኖ ይህንኑ ውሳኔ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም የቀረበለትን የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ የህገመንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የህዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበት ሁኔታ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ የፌደራልና ክልል ምክርቤቶች የስልጣን ዘመን እንዲቀጥል እንዲሁም አጠቃላይ ምርጫው ስልጣን ያላቸው አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበት ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡

ስለሆነም፤

1. 6ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሄድም፡፡

2. በተጨማሪም ከላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተጽእኖ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ ነው፡፡በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ 6ተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት የለውም።

በመሆኑም ቦርዱ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ እንዲያውቅለትም ሆነ ምርጫ እንዲያስፈፅምለት ያቀረበውን ጥያቄ ያልተቀበለው መሆኑን፣ የተጠየቀውን የሰው ሀይል፣ የሎጄስቲክስ እና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሰጥበት የህግ አግባብ አለመኖሩን ያሳውቃል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top