ባህልና ታሪክ
አምባሳደር ቆንጂት ስነ ጊዮርጊስ – የዲፕሎማሲ እናት
የሙያ አጋሮቻቸው ሁሉ ‹‹ተንቀሳቃሿ የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ (The Walking Encyclopedia of African Affairs) ብለው ይጠሯቸዋል። ለ52 ዓመታት ከ10 ወራት ያህል የኖሩበት የዲፕሎማሲው ዓለም ባለረጅም ዘመን አገልግሎቷ አፍሪካዊት ዲፕሎማት አሰኝቷቸዋል … አምባሳር ቆንጂት ስነ ጊዮርጊስን! እርሳቸው ለዚህ ስኬት የበቁት ግን በቀላሉ አልነበረም። ‹‹ለሴት የሚሆን ሥራ አይደለም›› ከሚለው አስደንጋጭ እሳቤ ጀምሮ ሙሉ የሕይወት ጊዜን ለሙያ (ለሥራ) እስከመሰዋት የደረሱ ፈተናዎችን ተቋቁመው እንጂ።
ቆንጂት በ1932 ዓ.ም ሐረር ውስጥ ተወለደች። አስተዳደጓ በራስ የመተማመንና የነፃነት ስሜት እንዲኖራት ዕድል ሰጥቷታል። ለዚህም የእናቷና የታላቅ ወንድሟ ድርሻ የጎላ ነበር። በተለይ ታላቅ ወንድሟ እንደታላቅነቱ በቆንጂት እንቅስቃሴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ ነፃነትን ከኃላፊነት ጋር ይሰጣት ስለነበር ነፃነቷ ወንድሟ የጣለባትን እምነት እንድታከብር፣ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንድታስብ፣ ውሳኔዎችን ራሷ እንድትወስን፣ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዳትሆንና በኃላፊነት ስሜት እንድትንቀሳቀስ አደረጋት። ይህ የአስተዳደጓ አጋጣሚም ከሕይወት ቁም ነገሮች መካከል አንዱ ለራስ ክብር መስጠት መሆኑንና ይህንንም ለማሳካት ታማኝና ሐቀኛ መሆን እንደሚያስፈልግ አስተማራት።
ቆንጂት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ከእህቷ ጋር ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ በማቅናት ትምህርቷን ተከታተለች። ከዚያ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ለማጥናት ለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገባች። የመጀመሪያ ዲግሪዋንም በዚሁ የትምህርት መስክ አጠናቀቀች። ዓለም አቀፍ ግንኙነት እያጠናች በነበረችበት ጊዜ ስለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (United Nations) የተጻፉ መጻሕፍትን ታነብ ነበር። ይህም ስለድርጅቱ አደረጃጀት፣ አሠራርና ተግባራት በጥልቀት የማወቅ ጉጉት አሳደረባት። በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሠራች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያን ወክሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ ውስጥ የማገልገል ዕድል ሊኖራት እንደሚችል በተነገራት ምክር መሠረት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከቻ አስገባች።
በወቅቱ የሥራ ምደባ ወደሚካሄድበት ቢሮ በመሄድ የተማረችው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስለሆነ መሥራት የምትፈልገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እንደሆነ ተናገረች። ማመልከቻዋን ያቀረበችላቸው የሥራ ኃላፊ ግን ‹‹ … እሱ ለሴት የሚሆን ቦታ አይደለም›› የሚል ምላሽ ሰጧት። ቆንጂት በምላሹ ብትደነግጥም የግድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግባት እንዳለባት ወሰነች። ምላሹ እንደተለመደው ቢሆንም ቆንጂት ግን በየቀኑ ወደ ሚኒስቴሩ እየሄደች ትቀመጥ ነበር። ከዚያም ‹‹ይቺ ልጅ አልለቀቀችንም፤ ደብዳቤ ተጽፎላት ትግባ› ተብሎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) ከመመሥረቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1954 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ልትቀላቀል በቃች።
ቆንጂት የተመደበችው በሚኒስቴሩ የተባበሩት መንግሥታት ክፍል ውስጥ ነበር። ከሦስት ዓመታት በኋላ ዕድገት አግኝታ በሁለተኛ ፀሐፊ ማዕረግ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንድትሠራ ተመደበች። ቆንጂት መሥራት የምትፈልገው ዋና የዲፕሎማሲ ሥራ እንጂ በአስተዳደር ሥራዎች ላይ ባለመሆኑ ሕልሟን ለማሳካት ጥረቷን ቀጠለች። በዚህም በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ቡድን ውስጥ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ጉዳዮች ኦፊሰር ሆና መሥራት ጀመረች። ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ለ10 ዓመታት ያህል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ገለልተኛ አገራት መምሪያ ውስጥ ሠራች። በመቀጠልም በ1970ዎቹ ጀኔቫ፣ ስዊዘርላንድ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ምክትል ተወካይ ሆና ተመደበች፤ ለአስር ዓመታትም አገለገለች።
ከ28 ዓመታት አጠቃላይ የዲፕሎማሲ አገልግሎት በኋላ እዚያው ጀኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ
መልዕክተኛና በኦስትሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ። በመቀጠልም ከመጋቢት 1984 ዓ.ም ጀምሮ በካናዳ፣ በሜክሲኮና በእሥራኤል የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እስከ ነሐሴ 1987 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል። ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመው ነበር።
ከአንድ ዓመት በኋላ በግብጽ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመው ከአራት ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አባባ ተመልሰው ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመው ሠርተዋል።
በ1998 ዓ.ም በኦስትሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክና በቪየና በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ በድጋሚ ተሾሙ። ከመስከረም ወር 2002 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በክብር በጡረታ እስከተሰናበቱበት ድረስ በአፍሪካ ሕብረት (African Union) እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገራቸውን በትጋት አገልግለዋል።
አምባሳደር ቆንጂት በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በነበሩበት ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጣና አወቃቀሩም የተቋሙን ዓላማዎች በሚያሳካ መልኩ እንዲደራጅ (ወደ ‹‹የአፍሪካ ሕብረት›› እንዲለወጥ) ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
አምባሳደር ቆንጂት መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1955 ዓ.ም ሲመሰረት ስለነበራቸው ትውስታ ሲናገሩ ‹‹ … የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ሲመሠረት የአንድ ዓመት የሥራ ልምድ የነበረኝ ወጣት ዲፕሎማት ነበርኩ። እ.ኤ.አ. ከግንቦት 22 እስከ 25 / 1963 በተካሄደው የመጀመሪያው የነፃ አገሮች መሪዎችና መንግሥታት ስብሰባ ላይ ተካፋይ ነበርኩ። ሰላሳ ሁለቱ መሥራች አባቶች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተርን ሲፈርሙ ታድሜያለሁ። በአዳራሹ የነበረውን ስሜት በግልጽ አሁንም አስታውሰዋለሁ። ተሳታፊዎቹ የነበራቸውን ደስታና የተስፈኝነት ስሜት ባሳያችሁ ደስ ይለኝ ነበር … ›› ብለዋል።
‹‹ … ኢትዮጵያ በካዛብላንካና በሞኖሮቪያ ቡድኖች መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ነፃ ሆና በማስታረቅ ብቻ ሳትወሰን፣ አኅጉራዊው ድርጅት የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች … ለአኅጉራዊው ድርጅት ስኬት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል››
በማለት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ስለነበራት ሚና እንዲሁም ተቋሙ ዓላማውን እንዲያሳካ ስላበረከተችው አስተዋጽኦ ያስረዳሉ።
የአፍሪካ ሕብረት ‹‹ጠንካራ አህጉራዊ ተቋም አይደለም›› ተብሎ የሚሰነዘሩ ወቀሳዎችን በተመለከተ አምባሳደር ቆንጂት ‹‹ … የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ከነበሩት ዓላማዎች መካከል አንዱና ዋነኛ የሆነውን ቅኝ አገዛዝን የማስወገድና ነፃነትን የማስፈን ዓላማን አሳክቷል። በአኅጉራዊ መድረክነቱም የአባል አገሮችን የጋራ አጀንዳና ትብብር ለማሳካት በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን ሠርቷል። ‹‹የአኅጉሩ መሪ ድርጅት ሠላምና መረጋጋትን ከማስፈን፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ውህደት ከመፍጠር፣ መልካም አስተዳደር ከማስፈንና ሙስናን ከመዋጋት፣ መፈንቅለ መንግሥትንና የአንድ ሰውን አመራር ከማስወገድ፣ በአገሮች መካከል የሚደረግ ጦርነትንና የእርስ በርስ ጦርነትን ከማስቀረት፣ የኢኮኖሚ መላሸቅንና የብድር ጫናን ከማስወገድ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተጽዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ከመከላከል አኳያ መጠነ ሰፊ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ግልጽ ነው። ይሁንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ሠራተኞች ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ነገሮችን ለመቀየር ጠንክረው ሠርተዋል፤ ለውጡ አዝጋሚ ቢሆንም ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል … በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ መሻሻሎች አሉ፤›› ብለዋል። የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲተካው የተደረገው አንዳንድ ድክመቶቹን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው … ሰፊ የተሳትፎ መሠረት ያልነበረውና የልሂቃኑን ሚና አግዝፎ የሚያይ ነበር … ሕዝባዊ ተሳትፎም የሕብረቱ አንዱ ዋነኛ መርህ ሆኗል …›› ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ከልሂቃን ሚና ይልቅ ለተቋማዊ አደረጃጀቱ ትኩረት መስጠቱ፤ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ ዘላቂነት ላይ የሚያተኩሩ መርሐ ግብሮችን ቀርፆ መተግበሩ፤ የሰላምና ደኅንነት ካውንስል፣ የአፍሪካ በተጠንቀቅ የቆመ ኃይል፣ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የሽማግሌዎች ቡድን፣ የሠላም ፈንድና መሰል አደረጃጀቶችና መርሐ ግብሮች ተቋቁመው ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መጀመራቸው፤ የክፍለ አህጉራዊ ሕብረቶች ዕድገትና መሻሻል፤ በሕብረቱ የሚመሩ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውጤታማ መሆናቸው፤ በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶች መቀነሳቸው፤ ማህበረ-ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸውና አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር ያስተሳሰሩ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች መፈጠራቸው፤ አፍሪካ በአንድ ድምፅ መናገር መጀመሯ እንዲሁም የአፍሪካ መንግሥታት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸው ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ አምባሳደር ቆንጂት የመጪውን ጊዜ ተስፋ ከተግዳሮቶቹ በላይ እንዲያዩት አድርጓቸዋል።
‹‹ … በሂደት ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአፍሪካ ለመገንባት እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች ነው። መጪው 50 ዓመት ካለፈው 50 ዓመት ፈጽሞ የተለየ እንደሚሆን፤ አጀንዳ 2063 የተሰኘው የአፍሪካ ሕብረት ታላቁ ራዕይ ዴሞክራሲ የተረጋገጠባትና ኢኮኖሚው በተፋጠነ ሁኔታ የሚያድግባት አፍሪካን እንደሚፈጥር ተስፋ አለኝ›› ይላሉ።
የአፍሪካ ሕብረት ብሩህ መጪ ጊዜን ለማረጋገጥ በዋነኛነት በገንዘብ ራሱን ሊችል፣ ተቋማዊ አቅሙን ሊያዳብር፣ የሰላምና የፀጥታ ተግዳሮቶችን በሚገባ ሊወጣ፣ በአባል አገሮቹ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ያሉትን የመከፋፈል አደጋዎች ሊያስወግድ፣ በአካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን ተደራራቢ አባልነትን ሊያስወግድ፣ ደካማውን ኢኮኖሚያዊና የመሠረተ ልማት ውህደቶችን ሊያጠናክር እንደሚገባው ይመክራሉ። ወጣቱ ትውልድ ሰላማዊ፣ የበለፀገችና የተባበረች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተሻለ ጊዜ ላይ መሆኑንም በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም ለአምባሳደር ቆንጂት ደማቅ የስንብትና የምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ሽኝት አድርጎላቸዋል፤ አመስግኗቸዋል። በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የነበሩት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በስንብት/ምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ … አምባሳደር ቆንጂት ከአፍሪካ ምርጥ ሴት ልጆች መካከል አንዷ ናቸው። አምባሳደር ቆንጂት አገራቸውንና አህጉራቸውን ከልብ የሚወዱ
ዲፕሎማት ናቸው›› በማለት አምባሳደሯ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር የታገሉ አንጋፋ ባለውለታ እንደሆኑ መስክረዋል። ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ቆንጂት በቀጣይ ጊዜያት ተዝቆ በማያልቀው የካበተ የዲፕሎማሲ ልምዳቸው የአፍሪካ ሕብረትን በምክር እንዲያግዙም ሊቀ መንበሯ ጠይቀዋቸው ነበር።
በጊዜው በአፍሪካ ሕብረት የኡጋንዳ አምባሳደር የነበሩት ሙል ሰቡጃ ካቴንዴ በበኩላቸው፤ አምባሳደር ቆንጂት ለአገራቸው፣ ለአህጉራቸውና ለሙያቸው የተለየ ፍቅር ያላቸውና ልዩ የሆኑ አንጋፋ ባለሙያ እንደሆኑ ተናግረው ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር የነበሩት ብሪዢት ኮሌትም አምባሳደር ቆንጂት ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልፀውላቸዋል።
በሩስያ የዚምባብዌ አምባሳደር ማይክ ኒኮላስ ሳንጎ አምባሳደር ቆንጂትን ‹‹አንጋፋ አርበኛ፣ ዲፕሎማትና ሁለ ገብ ሰው … ሁላችንም ልንደርስበት የምንመኘው አስደናቂ ደረጃ ላይ የደረሱ ጠንካራ ሴት›› በማለት ገልፀዋቸዋል።
አምባሳደር ቆንጂት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እንዲሻሻል በተለይም የአፍሪካ አዳራሽ (Africa House) ተብሎ የሚታወቀው የኮሚሽኑ ክፍል አፍሪካዊ ማንነትን የሚንፀባርቅ ሙዚየም እንዲሆን የተጫወቱት ሚና የሚዘነጋ እንዳልሆነ የኮሚሽኑ የቀድሞው ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ ተናግረዋል።
የቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሁኑ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ ኣድሓኖም ‹‹ … አምባሳደር ቆንጂት ወደ 53 ዓመታት በተጠጋው አገልግሎታቸው ሕዝብን በማገልገል ስለሚገኝ ክብርና ኩራት አስተምረውናል። በረጅም ዓመታት አገልግሎታቸውና በካበተ ልምድ ባለቤትነታቸው ምክንያት ‹የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ (Encyclopedia of African Affairs)› እንላቸዋለን። አፍሪካ በዲፕሎማሲው መስክ ወደፊት እንድትራመድ በትጋት ሲሠሩ የኖሩ ጠንካራና ልዩ ሰው ናቸው …›› በማለት ስለአምባሳደር ቆንጂት አበርክቶ ተናግረዋል።
አምባሳደር ቆንጂት በስንብትና ምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ ‹‹ … ሥራዬ ሕይወቴ ነበር … ሁሉንም ዋጋ የከፈልኩት ለሥራዬ ነው … ከበርካታ ዓመታት አገልግሎት በኋላ ጡረታ ስወጣ ልዩ ስሜት የተሰማኝም ለዚህ ነው … አገርን በትጋትና በሙሉ አቅም ከማገልገል የበለጠ ክብር የለም …›› በማለት ተናግረዋል።
ለ52 ዓመታት ከ10 ወራት ያህል ኢትዮጵያንና አፍሪካን በትጋት ያገለገሉት የዲፕሎማሲዋ እናት አምባሳደር ቆንጂት ይህን ያህል ጊዜ አገልግለው እንኳ አሁንም ለተጨማሪ ዓመታት ቢያገለግሉ ደስታቸው ነው። ለዚህም ነው የአፍሪካ ሕብረት በኅዳር 2008 ዓ.ም ባዘጋጀላቸው የስንብትና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ ‹‹ … ወዳጆቼ ኢትዮጵያና አፍሪካ ታላቅ ግስጋሴ እያደረጉ በሚገኙበት በዚህ ጊዜ በሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ስል የጡረታ ጊዜዬ ባይደርስ ጥሩ ነበር የሚል ምኞት አድሮብኛል … ›› በማለት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረው አገልግሎታቸው ላይ ተጨማሪ ዓመታትን ቢቆዩ ፍላጎታቸው እንደነበር የተናገሩት።
‹‹51 ዓመታት በሠራሁት ሥራና ለአገሬ ብሎም ለአህጉሩ ባደረግኩት አስተዋጽኦ እኮራለሁ። የግል ሕይወቴንና የቤተሰቦቼን ፍላጎት መስዋዕት አድርጌ ነው በሥራው ላይ ይኼን ያህል ዓመታት የቆየሁት። የጎደሉ ነገሮች ነገ ይሞላሉ። ወደ ኋላ ተመልሼ ሥራዎቼን ሳያቸው እርካታ ነው የሚሰማኝ እንጂ ፀፀት የለኝም። ሁሉም አፍሪካዊ የሕብረቱን ሥራ ለማገዝና ለመለወጥ ሚና እንዳለው ሊገነዘብ ይገባል። ሁሉም አፍሪካውያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አፍሪካ ሕብረትን አጀንዳ ሊያደርጉት ይገባል። እኔ ማገዝ የምችለውን ሁሉ ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነኝ›› ብለዋል።
አምባሳደር ቆንጂት ለረጅም ዓመታት አገልግሎታቸው ሽልማቶችን አግኝተዋል። ለአብነት ያህል በጥር ወር 2011 ዓ.ም ለረጅም ዘመናት የዲፕሎማሲ አገልግሎታቸው ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የምስጋናና የእውቅና ሰርተፊኬት ተቀብለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012